የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ተወልደ ገብረማርያም ከኃላፊነታቸው ለቀቁ

አቶ ተወልደ ገ/ማርያም

በአፍሪካ ስመ ጥር የሆነውን የኢትዮጵያ አየር መንገድን በዋና ሥራ አስፈፃሚነት ለረዥም ዓመታት በስኬት የመሩት አቶ ተወልደ ገብረማርያም ከኃላፊነታቸው ለቀቁ::

በኢትዮጵይያ አየር መንገድ ውስጥ በከፍተኛ የኃላፊነት ቦታ ላይ ያሉ ምንጮች ለቢቢሲ እንደገለጹት አቶ ተወልደ መልቀቂያቸው ተቀባይነት አግኝቷል::

ዋና ሥራ አስፈፃሚው ከኃላፊነታቸው ለመልቀቅ እንደምክንያት የቀረበው የጤናቸው ሁኔታ ነው ተብሏል::

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ባወጣው መግለጫም አቶ ተወልደ ባለፉት ስድስት ወራት አሜሪካ ውስጥ ሕክምና ሲከታተሉ መቆየታቸውን አመልክቶ በጤናቸው ላይ ለማተኮር ከጊዜያቸው በፊት ጡረታ ለመውጣት መጠየቃቸውን አረጋግጧል።

በዚህም መሠረት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ቦርድ ረቡዕ መጋቢት 14/2014 ዓ.ም ባካሄደው ስብሰባው የዋና ሥራ አስፈፃሚውን ጥያቄ መቀበሉ ተገልጿል።

ቦርዱ የአቶ ተወልደን የሥራ መልቀቂያ መቀበሉን ተከትሎ በቅርቡም ተተኪ ዋና ሥራ አስፈፃሚ እንደሚሾም አመልክቷል።

አቶ ተወልደ ለበርካታ ወራት አሜሪካ ውስጥ ሕክምናቸውን እየተከታተሉ ሥራቸውን ሲያከናውኑ እንደነበር ተገልጿል::

አቶ ተወልደ ከ35 ዓመታት በላይ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ውስጥ የሠሩ ሲሆን፣ ከ10 ዓመት በላይ ደግሞ በዋና ሥራ አስፈፃሚነት ተቋሙን በስኬት መርተዋል::

ይህ በእንዲህ እንዳለ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦርድ አዲስ የቦርድ ሊቀ መንበር እንደተሾመለት አስታውቋል። በዚህም መሠረት የቀድሞው የአየር መንገዱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ግርማ ዋቄ በአቶ አባዱላ ገመዳ ተይዞ የነበረውን ኃላፊነት ተረክበዋል።

ከአቶ ተወልደ ቀደም ብለው የኢትዮጵያ አየር መንገድን ለሰባት ዓመታት ዋና ሥራ አስፈፃሚ የነበሩትንና በአየር ትራንስፖርት ዘርፍ ዓለም አቀፍ ልምድ ያላቸው አቶ ግርማ ዋቄ አየር መንገዱ አሁን ለደረሰበት ስኬት መሠረት የጣሉ መሆናቸው ይነገርላቸዋል።

የአቶ ተወልደ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አመራር በጨረፍታ

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአፍሪካ ካሉ ተፎካካሪዎቹ በተለየ ከዓመት ዓመት ስኬታማና ትርፋማ በመሆን በተከታታይ የቀዳሚነት ቦታን ለመያዝ ችሏል::

በርካታ የአፍሪካ አየር መንገዶች ባለፉት አስር ዓመታት ውስጥ ከፍተኛ ኪሳራ ሲገጥማቸውና ከመንግሥታትና ከሌሎች አየር መንገዶች ድጋፍን ሲጠይቁ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግን ከፍ ያለ ትርፍ በማግኘት ከአፍሪካ አልፎ በሌሎች አህጉራት ውስጥም ስኬታማ ለመሆን ችሏል::

አየር መንገዱ በ75 ዓመታት ውስጥ ባዳበረው ልምድ በአፍሪካ ቀዳሚ ለመሆን የቻለ ሲሆን ለዚህም አቶ ተወልደ ተጠቃሽ ከሆኑ የተቋሙ መሪዎች መካከል አንዱ እንደሆኑ ባልደረቦቻቸው ለቢቢሲ ገልጸዋል::

በተለይም የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ የአየር ትራንስፖርቱን ዘርፍ ክፉኛ በጎዳበት ባለፉት ሁለት ዓመታት በርካታ ስኬታማ አየር መንገዶች ፈተና ውስጥ ወድቀው ነበር::

ጥቂት የማይባሉ አየር መንገዶች ሠራተኞችን ሲቀንሱና ሲዘጉ አቶ ተወልደ የኢትዮጵያ አየር መንገድን በስኬት በመምራት በአትራፊነቱ እንዲቀጥል አስችለውታል::

አቶ ተወልደ አየር መንገዱን በመሩባቸው ጊዜያት አንድ ቢሊዮን ዶላር የነበረው ዓመታዊ ገቢው ወደ 4.5 ቢሊዮን ዶላር፣ 33 የነበሩት አውሮፕላኖቹ ወደ 130፣ የተጓዦቹም ቁጥር ከ3 ሚሊዮን ወደ 12 ሚሊዮን በከፍተኛ መጠን ማደጉን አየር መንገዱ ጠቅሷል።

በተጨማሪም በአቶ ተወልደ የአመራር ዘመን አየር መንገዱ ግዙፍ ሆቴል፣ የካርጎ ማስተናገጃ፣ የአውሮፕላን ጥገና ማዕከላት፣ የሥልጠና ማዕከል፣ ምስለ በረራና ሌሎች ግዙፍ የአየር ትራንስፖርት መሠረተ ልማቶችን ገንብተዋል፣ አሻሽለዋል።

ጥቂት ስለ አቶ ተወልደ ገብረማርያም

አቶ ተወልደ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈፃሚ የሆኑት እንደ አውሮፓውያኑ በጥር 2011 ነው።

በአየር መንገዱ መሥራት የጀመሩት እአአ በ1985 የትራንስፖርት ኤጀንት ሆነው ነበር።

ከዚያም በተለያዩ የአመራር ቦታዎች አየር መንገዱን አገልግለዋል።

በኢትዮጵያ አየር መንገድ ውስጥ በካርጎ፣ በኤርያ ኦፊስ እንዲሁም በሽያጭና ማስታወቂያ ዘርፎች ነው በከፍተኛ አመራርነት የሠሩት።

አቶ ተወልደ በተባበሩት መንግሥታት ውስጥ ዘላቂነት ባለው ትራንስፖርት ዘርፍ ከፍተኛ የአማካሪዎች ቡድን አባል ሆነው ሠርተዋል።

የስታር አሊያንስ ዋና የቦር አባል በመሆን፣ የዓለም አቀፉ የትራንስፖርተ ማኅበር (አይኤቲኤ) የቦርድ አባል በመሆን በተጨማሪም የአፍሪካ የአየር መንገዶች ማኅበር (ኤኤፍአርኤኤ) የዋና ኮሚቴ አባል በመሆን አገልግለዋል።

አቶ ተወልደ የአፍሪካ የጉዞ ማኅበር (ኤቲኤ) የቦርድ አባል እና የኢትዮጵያ የቱሪዝም ድርጅት (ኢቲኦ) የዳይሬክተሮች ቦርድ አባልም ሆነው ሠርተዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሆነው ባገለገሉባቸው በርካታ ዓመታት ብዙ ሽልማቶች ተበርክቶላቸዋል።

ከሽልማቶቹ መካከል የዓመቱ የአፍሪካ ምርጥ ዋና ሥራ አስፈፃሚ፣ ምርጥ የአፍሪካ የቢዝነስ መሪ፣ ቀጠናዊ የአየር መንገድ አመራር ሽልማት እንዲሁም ምርጥ ጾታን ያማከለ ሥራ አስፈፃሚ የሚሉት ይጠቀሳሉ።

አቶ ተወልደ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ያገኙት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በምጣኔ ሀብት ነው።

ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ዩናይትድ ኪንግደም ከሚገኘው ኦፕን ዩኒቨርስቲ በንግድ አስተዳደር (ቢዝነስ አድምንስትሬሽን) አግኝተዋል።

በተጨማሪም እአአ በሐምሌ 2019 ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የክብር ዶክትሬት ተበርክቶላቸዋል።