የዓለማችን ምርጥ 10 አየር መንገዶች የትኞቹ ናቸው?

የፎቶው ባለመብት, © Marco Bottigelli
ስካይትራክስ ዎርልድ ኤይርላይን አዋርድስ በአሁኑ ወቅት የዓለማችን ምርጥ ናቸው ያላቸውን አየር መንገዶች ይፋ አድርጓል።
በኢቪዬሽን ኢንዱስትሪ ውስጥ ትልቅ ግምት ከሚሰጣቸው ሽልማቶች መካከል አንዱ የሆነው ስካይትራክስ ዎርልድ ኤይርላይን አዋርድስ፤ በ2021 የዓለማችን ምርጡ አየር መንገድ የኳታሩ፤ ኳታር ኤይርዌይስ ነው ብሏል።
ስካይትራክስ ባለፉት 23 ወራት ከ13 ሚሊዮን በላይ ተጓዦች ባሰባስብኩት ባለው መረጃ መሠረት ከኳታር ኤየርዌይስ በመቀጠል፤
- 2ኛ የሲንጋፖር አየር መንገድ፣
- 3ኛ የጃፓኑ ኦል ኒፖን አየር መንገድ፣
- 4ኛ የዱባዩ ኢሚሬትስ እና
- 5ኛ ጃፓን አየር መንገድ ምርጦቹ የዓለማችን አየር መንገዶች ናቸው ብሏል።
ትናንት በይፋ በተገለጸው የስካይትራክስ ዎርልድ ኤይርላይን አዋርድስ ከላይ ከተጠቀሱት በመቀጠል እንደ ቅድመ ተከተላቸው ምርጥ 10 የዓለማችን አየር መንዶች ውስጥ የተካተቱት አየር መንገዶች፤ ካቲ ፓሲፊክ አየር መንገድ፣ ኢቫ ኤይር፣ ካንታስ አየር መንገድ፣ ሃይናን አየር መንድ እና የፈንሳይ አየር መንድ ናቸው።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በዚህ ዓመት ቀድሞ ከነበረበት ደረጃ 7 ደረጃዎችን በማሻሻል ከዓለም 37ኛ ደረጃን ይዟል።
በአፍሪካ ከሚገኙ አየር መንዶች መካከል የኬንያ አየር መንድ 79ኛ፣ የሞሮኮው ሮያል ኤይር ማሮክ 81ኛ እንዲሁም ኤይር ሞሪሺየስ 82 ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።
የአፍሪካ ምርጡ አየር መንገድ
የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአፍሪካ ምርጡ አየር መንገድ ተብሎ በስካይትራክስ ዎርልድ ኤይርላይን አዋርድስ ተሸልሟል።
ከዚህ በተጨማሪም አየር መንገዱ በተጨማሪ ሦስት ዘርፎች አህጉራዊ ምርጥ አየር መንገድ ተብሏል። አየር መንገዱ በአፍሪካ ምርጡ ቢዝነስ እና ኢኮኖሚ ክላስ ተብሎ ተሸልሟል።
በአፍሪካ ምርጡ ካቢን ክሩ (የበረራ ሠራተኞች) የያዘ አየር መንገድ ተብሎ ስካይትሬክስ ዎርልድ ኤየርላይን ሽልማትን ወስዷል።
ሽልማቱን ተከትሎ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ተወልደ ገ/ማርያም፤ ኩባንያቸው የስካይትራክስ ሽልማት ማግኘቱ፤ አየር መንገዱ ለመንገደኞቹ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት እያቀረበ መሆኑን ያረጋገጠ ነው ብለዋል።
ዋና ሥራ አስፈጻሚው ". . . የስካይትራክስ ሽልማት አየር መንገዱ በትክክለኛው አቅጣጫ እያመራ እንደሆነ ያሳያል በዚህም ጥልቅ በሆነ ኩራት እነዚህን ሽልማቶች እንቀበላለን" ብለዋል።
ሌሎች ምርጥ አህጉራዊ አየር መንገዶች
ስካይትራክስ የፈረንሳዩ ኤየር ፍራንስ የአውሮፓ ምርጡ አየር መንገድ ሲል መርጦታል። የእንግሊዙ ብሪቲሽ ኤይርዌየስ እና የጀርመኑ ሉፍታንዛ ደግሞ ከኤይር ፍራንስ ቀጥሎ የአውሮፓ ምርጦቹ አየር መንዶች ተብለው ተመርጠዋል።
በሰሜን አሜሪካ ካሉ አየር መንገዶች ደግሞ የአሜሪካው ዴልታ አየር መንገድ ቀዳሚውን ደረጃ ሲይዝ ጄትብሉ አየር መንገድ እና ኤይር ካናዳ ደግሞ ሁለተኛ እና ሦስተኛ ደረጃን ይዘዋል።
ኳታር አየር መንገድ በመካከለኛው ምሥራቅ ከሚገኙ አየር መንዶች መካከል ምርጡ የተባለ ሲሆን፣ የተባበሩት አረብ ኤሜሬትስ፤ ኢሚሬትስ እና ኢትሃድ አየር መንገድ ሁለተኛ እና ሦስተኛ ደረጃን ይዘዋል።
የዳሰሳ ጥናቱን እንዴት ተከናወነ?
ስካይትሬክስ ዎርልድ ኤይርላይን አዋርድስ በተለያዩ ዘርፎች ይሰጣል። ከእነዚህም መካከል የዓለማችን ምርጡ ንጹህ አየር መንገድ፣ ምርጥ ካቢን ክሩ (የበረራ ሠራተኞች) እና ምርጥ ቢዝነስ ክላስ የሚሰኙ ዘርፎች ይገኙበታል።
ስካይትሬክስ ከመስከረም 2019 እስከ ሐምሌ 2021 ባሉት 23 ወራት 13.42 ሚሊዮን ተጓዦች ላይ የዳሰሳ ጥናት አድርጎ ባገኘው ውጤት መሠረት ምርጥ የሚላቸውን አየር መንዶች በተለያዩ ዘርፎች ይፋ ያደርጋል።
ድርጅቱ እንደሚለው ከ100 በላይ ዜግነት ያላቸው ሰዎች በዳሰሳ ጥናቱ ተሳትፈዋል። ስካይትሬክ በዳሰሳ ጥናቱ ስለታሳተፉ ሰዎች ገንዘብ አይከፍልም።
በዚህ የዳሰሳ ጥናት ላይ ከ350 በላይ አየር መንገዶች መሳተፋቸውንም ስካይትሬክ ገልጿል።












