እንግሊዝ የአፍጋኒስታን ሴት የእግር ኳስ ቡድን አባላትን ከቤተሰቦቻቸው ጋር ልትቀበል ነው

የአፍጋኒስታን ሴቶች እግር ኳስ ተጫዋቾች

የፎቶው ባለመብት, ROKIT FOUNDATION

ከታሊባን ሸሽተው በፓኪስታን የሚገኙ የአፍጋኒስታን ታዳጊ ሴት እግር ኳስ ተጫዋቾች ከቤተሰቦቻቸው ጋር ወደ ዩናይትድ ኪንግደም ሊመጡ እንደሚችሉ ተነገራቸው።

ከ13-19 የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙት 35 አባላት ያሉት ቡድኑ ባለፈው ወር ካቡልን ሸሽቶ ለጥቂት ሳምንታት ፓኪስታን በሚገኝ ሆቴል ቆይቷል። የቡድን አባላቱ የፓኪስታን ጊዜያዊ ቪዛቸው በሰዓታት ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሏል።

የዩናይትድ ኪንግደም መንግስት ቃል አቀባይ "ለአፍጋኒስታን የሴቶች ቡድን ቪዛ ለመስጠት እየሰራን ነው። በቅርቡ ወደ በእንግሊዝ ልንቀበላቸው በጉጉት እየጠበቅን ነው" ብለዋል።

የእግር ኳስ አባላቱ ሌላ ሃገር ካልተቀበላቸው ወደ አፍጋኒስታን የመመለስ ግዴታ ነበረባቸው።

ሴቶቹ እወንዲሸሹ ያገዘው የሮኪት ፋውንዴሽን ዋና ሥራ አስፈፃሚ የሆኑት ሲኡ-አን ማሪ ጂል "ይህ አስደናቂ ዜና ነው። ለዚህ ህይወት አድን ውሳኔያቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰንን እና የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ፕሪቲ ፓቴልን በጣም እናመሰግናል" ብለዋል።

ከአፍጋኒስታን በአውቶቡሶች እንዲወጡ እና በላሆር እንዲቆዩ የገንዘብ ድጋፍ ያደረገው የፋውንዴሽኑ ሊቀመንበር ጆናታን ኬንድሪክ "በህይወት ሁለተኛ ዕድል በማግኘታቸው በጣም ተደስቻለሁ። ይህ ለእነሱ አዲስ ዓለም ነው። የእግር ኳሱ ማህበረሰብ እንደሚደግፋቸው እርግጠኛ ነኝ። ተረጋግተው ሕይወት የሚሰጠውን ደስታ ሁሉ ለመለማመድ ይችላሉ" ብለዋል።

ጂል ለቢቢሲ እንደተናገሩት ሴቶቹ ሊደርስባቸው ስለሚችለው ነገር ተጨንቀው የነበረ ቢሆንም አሁን ግን ከፍተኛ እፎይታ አግኝተዋል ሲሉ ገልጸዋል። ከሁለት እስከ ሦስት ሳምንታት ባለው ጊዜ ውስጥ እንግሊዝ እንደሚገቡ ተናግረዋል።

ሊድስ ዩናይትድ እና ቼልሲ በእንግሊዝ ሲደርሱ እንደሚደግፏቸው ቃል ከገቡ በርካታ የእንግሊዝ የእግር ኳስ ክለቦች መካከል ተጠቃሽ ናቸው።

የወጣቶቹ የቡድን አባላት ሁሉም ባልተለመደ ሁኔታ ውስጥ አልፈዋል።

አብዛኛዎቹ ተጫዋቾች ከምዕራብ አፍጋኒስታኗ ሄራት የመጡ ሲሆን ምዕራባዊያን ሰዎችን በአውሮፕለን ማስወጣት ሲጀምሩ ካቡል ወደሚገኙ እና ጥበቃ ወደሚደረግላቸው ቤቶች ተጉዘው ነበር።

ጂል "70 በመቶዎቹ የግድያ ዛቻ ደርሶባቸዋል። በፍርሃት ተሸብረዋል" ብለዋል።

የአፍጋኒስታን የቀድሞ የሴቶች ቡድን ወደ አውስትራሊያ በአውሮፕላን አቅንቷል። የሴቶቹ ቡድን በኋላ በፖርቱጋል ጥገኝነት ተሰጠው። የታዳጊ ቡድኑ ዕጣ ፈንታ ግን እስካሁን እርግጠኛ አልነበረም።

ሴቶቹ፣ ከአሰልጣኞቻቸው እና ከቤተሰቦቻቸው ጋር በነሐሴ ወር መጨረሻ ወደ ኳታር ሊወሰዱ ነበር። በደህንነት ማስጠንቀቂያ ምክንያት በራራቸው እንዲዘገይ ሆነ። ከሁለት ሰዓታት በኋላ ደግሞ አውሮፕላን ማረፊያው በአጥፍቶ ጠፊ ጥቃት ተሰነዘረበት።

ለ10 ቀናት ተደብቀው ከቆዩ በኋላ ወደ አፍጋኒስታን ድንበር ተጓጓዙ። በጠቅላይ ሚኒስትር ኢምራን ካን የመግቢያ ፈቃድ ከተሰጣቸው በኋላ ወደ ፓኪስታን ተሻገሩ።

ነገር ግን የፓኪስታን ቪዛቸው ሊያልቅ በመሆኑ ወደ አፍጋኒስታን መመለስ ለእነሱ በጣም አደገኛ ነበር ሲሉ ጂል ተናግረዋል።

ታሊባን ስልጣኑን ከተቆጣጠረ በኋላ ሴቶች በማንኛውም ስፖርት መሳተፍ አልቻሉም። የታሊባንን ቅጣት በመፍራት የቀድሞው የሴቶች የእግር ኳስ ቡድን አምበል ካሊዳ ፖፓል ተጫዋቾች ማሊያቸውን እንዲያቃጥሉ እና ማህበራዊ ድር አምባ ላይ የለጠፉትን ምስሎች እንዲያጠፉ አስጠንቅቃ ነበር።