አሜሪካዊያኑ ጥንዶች የኒውክሌር ምስጢሮች ሸጠዋል ተብለው ተከሰሱ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአሜሪካ ባሕር ኃይል ኒውክሌር ኢንጂኔር የሆነው ግለሰብና ባለቤቱ የሰርጓጅ መርከብ ኒውክሌር መሣሪያ ምስጢሮችን ለውጭ ኃይል ሊሸጡ ሞክረዋል ተብለው ተከሰዋል።
ጆናታን ቶቤ እና ባለቤቱ ዳያና ባለፈው ቅዳሜ ምዕራብ ቨርጂኒያ ውስጥ በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን የፍትህ መሥሪያ ቤቱ አስታውቋል።
ጥንዶቹ የባሕር ኃይል ዲዛይን መረጃን የውጭ ኃይል ነው ብለው ላሰቡት አካል ሊሸጡ ዶልተዋል ተብለዋል።
መረጃው በለውዝ ቅቤ ሳንድዊች ውስጥ ተደብቆ እንደነበር ነው ሪፖርቶች የሚጠቁሙት።
ነገር ግን በስተመጨረሻ የሌላ ሃገር ተወካይ ነኝ ብሎ የቀረበው ሰው የኤፍቢአይ ሰላይ ሆኖ ተገኝቷል።
መግለጫው እንደሚጠቁመው የ42 ዓመቱ ቶቤ እና የ45 ዓመቷ ባለቤቱ የአቶሚክ ኢነርጂ በተሰኘው አንቀፅ መሠረት ተከሰዋል።
ኢንጂነሩ በአሜሪካ ባሕር ኃይል የኒውክሌር ፕሮግራም ክፍል ውስጥ ይሠራ የነበረ ሲሆን ምስጢራዊ መረጃዎችን ማግኘት የሚችልበት ፈቃድ አለው።
የፍትህ መሥሪያ ቤቱ እንዳለው ሰውዬው ባለፈው ዓመት ሚያዚያ የውጭ ሃገር ነው ብሎ ላሰበው አካል መረጃ አሳልፎ የሰጠ ሲሆን ሌሎች መረጃዎችንም ከሱ መግዛት እንደሚችሉ ተናግሯል።
ከዚያ በመቀጠል ከአንድ የውጭ ሃገር ሰው ነው ብሎ ካሰበው ግለሰብ ጋር በይለፍ ቃል የታሸገ ኢሜይል ልውውጥ ሲያደርግ ነበር።
ምንም እንኳ ኢንጂነሩ እያወራ ያለው የሌላ ሃገር ተወካይ ከሆነ ሰው ጋር ነው ብሎ ቢያስብም ግለሰቡ ግን የኤፍቢአይ መኮንን ሆኖ ተገኝቷል።
ከበርካታ ወራት በኋላ ጥንዶቹ 100 ሺህ ዶላር በክሪፕቶከረንሲ ከተከፈላቸው የኒውክሌር መረጃ አሳልፈው ለመስጠት ተስማምተዋል ይላል መግለጫው።
ቶቤ እና ባለቤቱ ዳያና ባለፈው ሰኔ ወደ ምዕራብ ቨርጂኒያ መረጃውን ለማስተላለፍ ሄደው ነበር።
ባለቤቱ ዳያና ወጪ ወራጁን ስትመረምር ባለቤቷ ደግሞ በለውዝ ቅቤ ሳንድዊች ውስጥ መረጃውን በሚሞሪ ካርድ አድርጎ አንድ ድብቅ ቦታ አስቀምጦታል ሲል የክስ መዝገቡ ያስነብባል።
ሰላዩ መረጃውን ከተቀበለ በኋላ ገንዘቡን ከፍሎ መረጃውን የቆለፈብትን ቁል መክፈቻ ቃል ተቀብሏል። በሚሞሪ ካርዱ ውስጥም የኒውክሌር መረጃዎችን አግኝቷል ሲል ያክላል።
ኢንጂነሩ ከዚህ በኋላም ለሁለተኛ ጊዜ ሌላ መረጃ በማስቲካ ማሸጊያ ጠቅልሎ አሳልፎ መስጠቱን ክሱ አስነብቧል።
የኤፍቢአይ መኮንኖች ሰውዬውን በቁጥጥር ሥር ያዋሉት ባለፈው ቅዳሜ ለሶስተኛ ጊዜ መረጃ አሳልፎ ለመሰጠት ሲሰናዳ ነው።
ጥንዶቹ ነገ ማክሰኞ ችሎት ፊት ይቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል።












