በአውሮፓ ለመቆየት በዲግሪ ላይ ዲግሪ የሚሰበስቡት ናይጄሪያውያን ተማሪዎች

የፎቶው ባለመብት, MODupe Osunkoya
ናይጄሪያዊቷ ተማሪ ሞዱፔ ኦሱንኮያ በሊንክደን መተግበሪያ ብቻ ከ200 በላይ የሥራ ማመልከቻዎችን ብታስገባም አንዱም ሊሳካላት አልቻለም።
በከፍተኛ ሁኔታ ያስጨነቃት ጉዳይ ደግሞ ቤልጂየም የነበራት ጊዜ እየተጠናቀቀ መሆኑ ነው።
የተማሪ ቪዛዋ ሊጠናቀቅ የቀረው ሦስት ወር ሲሆን በዚህም ወቅት ሥራ ማግኘት አለባት ወይም ከአገር መውጣት ነው።
ነገር ግን ሌላ አማራጭ ነበራት። በአውሮፓውያኑ 2017 ናይጄሪያን ለቅቃ የወጣቸው ሞዱፔ ለፒኤችዲ መመዝገብ አውሮፓ ሊያቆያት እንደሚችል ተረዳች።
"የዶክትሬት ትምህርቴን እቀጥላለሁ ብዬ በጭራሽ አስቤ አላውቅም ነበር። ግን አማራጭ የለም። በአሁኑ ወቅት ወደ አገር ቤት (ናይጄሪያ) ብመለስ ሥራ አላገኝም" ትላለች የ28 ዓመቷ ሞዱፔ።
ከፍተኛ የሥራ አጥነት ባለባት ናይጄሪያ ከሦስት ወጣቶች አንዱ ሥራ አጥ ነው። ይህም ማለት ድህነት በተንሰራፋበት ሁኔታ መኖርን ብዙዎች ስለማይመርጡ ብሩህ ጭንቅላት ያላቸው ናይጄሪያውያን ወደ አገራቸው ከመመለስ ይልቅ ኑሯቸውን በውጭ አገራት አድርገዋል።
ለዚህም ነው ባለፈው ዓመት ሞዱፔ የዶክትሬት ዲግሪዋን ለመማር በኢስቶኒያ የተመዘገበች ሲሆን በቤልጅየም ካላጠናቀቀችው የማስተርስ ዲግሪዋም ጋር ለተወሰኑ ወራት በአንድነት ትማራለች ማለት ነው።
ቤልጂየም ውስጥ ምንም ዓይነት የሥራ ወይም የትምህርት ዕድልን ባለማግኘቷም ነው ወደ ሌላኛዋ አውሮፓዊት አገር ኢስቶኒያ ያማተረችው።
የፒኤችዲ ትምህርቷን ለመማር የወደፊቷ ስማርት ከተማ በምትባለው ታሊን ዩኒቨርስቲ ኦፍ ቴክኖሎጂ ሲሆን ነፃ የትምህርት ዕድል አግኝታለች።
ለአራት ዓመታት የምርምር ሥራዋን ካጠናቀቀች በኋላም ለቋሚ መኖሪያነት ማመልከት ትችላለች።
ልክ እንደ ቤልጅየም ትምህርት በእንግሊዝኛ ቋንቋ ወደሆነባት ምሥራቅ አውሮፓዊት አገር ኢስቶኒያ ለመሄድም አቅዳለች።
ሞዱፔ በባሕር ማዶ ከፍለው ለመማር በጣም ሃብታም ካልሆኑ በርካታ የናይጄሪያ ተማሪዎች መካከል አንዷ ናት።
በዓለም አቀፍ የተማሪዎች እንቅስቃሴ ላይ የሚያተኩረው አይሲኤፍ ሞኒተር መረጃ መሰረት ባለፈው ዓመት ወደ 100 ሺህ የሚጠጉ ናይጄሪያውያን ለትምህርት ወደ ውጭ አገራት ተጉዘዋል።
በርካቶቹ በተማሩባቸው አገራት ቋሚ ነዋሪ ለመሆንም ተስፋን ሰንቀው ነው የሚያቀኑት። እናም ይህንን ግባቸውን ለማሳካት የተለያዩ እርምጃዎችን መውሰዳቸው አልቀረም።
ስለ አፍሪካ ለማጥናት- በቤልጅየም
ቤልጂየም ውስጥ የምትገኝ ሌላኛዋ የናይጄሪያ ተማሪ ቦኑላ በበኩሏ "በርካቶች የማስተርስ ዲግሪቸውን ካጠናቀቁ በኋላ ወደ አገራቸው ላለመለስና በአውሮፓ ለመቆየት ሲሉ ከደረጃቸው በታች የዲፕሎማ ትምህርት ወይም በሰርቲፊኬት ለመመረቅ ተከታታይ ትምህርቶችን ይቀጥላሉ። ይህ ሁሉ ሕጋዊ ሆኖ ለመቆየት ነው " ትላለች።ታሪካዊው የወባ ክትባት ጅማሮ በአፍሪካ
በናይጄሪያ በኢኮኖሚክስ የትምህርት ዘርፍ ዲግሪ ቢኖራትም፣ ቤልጅየም ስትደርስ አንድ ብላ የዲግሪ ትምህርቷን እንደገና በመጀመር በንግድ ሥራ አስተዳደር የሦስት ዓመት ኮርስ አጠናቃለች።
ይሄም በአገሪቷ ውስጥ የሚኖራትን ቆይታ ለማራዘም ሲሆን ከዚያም በማኔጅመንት የትምህርት ዘርፍ ሁለት ዓመታት ያህል የሚወስደውን የማስተርስ ዲግሪ ትምህርቷን ለመቀጠል ወሰነች።
ቋሚ የመኖሪያ ቪዛ እንድታገኝ መንገድ የሚከፍትላት ሥራ ካላገኘች ሁለተኛ የማስተርስ ድግሪም ሆነ ፒኤችዲ ለመማር እያሰበች ነው።
"አፍሪካዊ ሆኜ ቤልጂየም ውስጥ የአፍሪካ ጥናት ትምህርት መማሬ ያናድደኛል" ብላለች ትክክለኛ ስሟ እንዳይጠቀስ የጠየቀችና ኢፎማ ብለን የምንጠራት የሦስተኛ ዲግሪ ተማሪ።
በአውሮፓውያኑ 2019 ቤልጂየም የመጣችው ኢፎማ ሁለተኛ የማስተርስ ዲግሪዋን እየተማረችም ነው።
"ትምህርቱን በቁም ነገር አልወስደውም። ምን ማድረግ እንዳለብኝ እስክወስን ድረስ ጊዜ መግደያ ነው" ትላለች።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በቤልጅየም ያለው የትምህርት ክፍያ በዓመት እስከ 1 ሺህ 200 ዶላር የሚደርስ መሆኑና ኑሮም ከሌሎች የአውሮፓ አገራት ጋር ሲወዳደር በአንፃራዊነት ርካሽ መሆኑ አማካኝ ገቢ ላላቸው በርካታ ናይጄሪያውያን መዳረሻ አድርጓታል።
"ኑሮ በጣም ርካሽ ነው የቤት ኪራይ በወር እስከ 300 ዩሮ ድረስ ይገኛል" ትላለች ሞዱፔ።
ሞዱፔ ልክ እንደ ሌሎች ናይጄሪያውያን ተማሪዎች ሁሉ ለአንድ ሴሚስተር የሚሸፍን የትምህርት ክፍያና የጥቂት ሳምንታት የኪስ ገንዘብ ይዛ ነው ከአገር የወጣችው።
ሕጉ በሚፈቅዳላት መሰረት በሳምንት እስከ 20 ሰዓታት በመስራት በወር እስከ 1 ሺህ ዩሮ ታገኝ የነበረ ሲሆንም ይህም የትምህርት ወጪዋን ይሸፍንላታል።
ነገር ግን በኑሯቸው ሻል ካሉ ወይም ከሃብታም ቤተሰቦች ለመጡ ተማሪዎች ተመራጭ የሆኑት እንግሊዝኛ ተናጋሪ አገራት ካናዳ፣ እንግሊዝ እና አሜሪካ ናቸው። በእነዚህም አገራት ከ13 ሺህ በላይ የናይጄሪያ ተማሪዎች አሉ።
ከዩናይትድ ኪንግደም በላቀ ካናዳን ይመርጣሉ
በአይሲኤፍ ሞኒተር መረጃ መሰረት ወደ ዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) የሚሄዱ የናይጄሪያ ተማሪዎች ቁጥር እያሸቆለቆለ ነው።
ለምሳሌ በአውሮፓውያኑ 2013/14፣ 18 ሺህ 20 የነበረ ሲሆን በ2017/18 ደግሞ ወደ 10 ሺህ 540 ወርዶ 41 በመቶ መቀነስ አሳይቷል።
ለዚህ መቀነስ አንዱ ምክንያት የውጭ ተማሪዎች ትምህርታቸውን ከጨረሱ በኋላ ለሁለት ዓመታት እንዲሠሩ የሚያስችለውን ቪዛ ዩኬ ማስወገዷ ነው።
ከዚህ በተጨማሪ ርካሽ የትምህርት ቤት ክፍያ፣ ውጥረት የሌለበት የቪዛ ሂደት፣ ድህረ ምረቃ እየተማሩ ሥራ መስራት መቻልና እና የነዋሪነት ፍቃድ ማግኘት ካናዳን ለብዙ ተማሪዎች የበለጠ ማራኪ አድርጓታል።
ነገር ግን የእንግሊዝ መንግሥት ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ትርፋማ ከሆነው የዓለም አቀፍ የትምህርት ገበያ ለመጠቀም በማሰብ ፖሊሲውን ቀይሯል።
እንደ አብዛኛዎቹ የውጭ ዜጎች፣ ናይጄሪያውያን ተማሪዎች ከእንግሊዝ ተማሪዎች ወይም ከአውሮፓ ሕብረት አገራት ከመጡ ተማሪዎች ከሦስት እጥፍ በላይ ክፍያዎችን ነው የሚከፍሉት።
ሆኖም ለናይጄሪያውያን በዩናይትድ ኪንግደም ፕሮፌሽናል ሥራዎችን ማግኘት ከባድ ሊሆን ይችላል፤ በበለጠ ደግሞ ቋንቋውን በማይናገሩበት ቤልጂየም ሥራ ማግኘት ፈታኝ ይሆናል።
በቤልጂየም ደች፣ ፈረንሣይኛ እና ጀርመንኛ ብሔራዊ ቋንቋዎች ስለሆኑ አብዛኞቹ አሠሪዎች ቢያንስ ሁለቱን መናገር የሚችሉ ሠራተኞችን ይመርጣሉ።
ሞዱፔም የፍሌሚሽ ቋንቋ መሠረታዊ እውቀት ቢኖራትም እንደ ሌሎቹ የናይጄሪያ ተማሪዎች ሁሉ በደንብ የምትችለው ቋንቋ እንግሊዝኛ ብቻ ነው።
"ምንም እንኳን ከትምህርት በኋላ የመኖሪያ ቪዛ ማግኘት ቢቻልም ከእኔ በተሻለ ቋንቋዎችን ከሚናገሩ የአገሬው ተወላጆች ጋር ለሥራ መወዳደር አለብኝ" ትላለች።
አንዳንድ ተማሪዎች ደግሞ በዘረኝነት ሥራ አጥተናል ብለው የሚያማርሩ ሲሆን ሌሎች ደግሞ ከሚጠበቀው በላይ በመማራቸውና የሥራ ልምድ ባለማግኘታቸው ተቸግረዋል።
ቤልጂየም ባለፈው ሳምንት ተማሪዎች ሥራ ለመፈለግ በጊዜያዊ ቪዛቸው እስከ አንድ ዓመት እንዲቆዩ ለማስቻል የስደተኛ ፖሊሲዋን አሻሽላለች።
ነገር ግን ቦኑላ ይህንን የተሻሻለውን አማራጭ እንደማትወስድ ትናገራለች፣ አንዴ በዚህ መንገድ ከተመዘገበችና ሥራ ካላገኘች ለተጨማሪ ዲግሪ ወደ ትምህርት ቤት መመለስ አትችልም።
"ከፍተኛ አጣብቂኝ ውስጥ እንደ መግባት ነው የሚቆጠረው" ትላለች።












