አማርኛ ቋንቋ፡ በቻይና ቤይጂንግ የውጭ ጥናቶች ዩኒቨርሲቲ አማርኛ ቋንቋ የምታስተምረው ቻይናዊት

የፎቶው ባለመብት, Zhang Chungai
ጃንግ ቹንጋይ ትባላለች። ቻይናዊት ናት። እርሷ ግን "ግማሽ ኢትዮጵያዊ ነኝ" ነው የምትለው። በአባቷ አሊያም በእናቷ ኢትዮጵያዊ ሆና ወይንም የኢትዮጵያ ደም ኖሮባት አይደለም። አማርኛ ቋንቋ በመቻሏ እንጂ።
ንግግራችንን ለመቀጠል 'ቹንጋይ' ስል ጠራኋት። "ፀደይ ብለሽ ጥሪኝ" አለችኝ- ፀደይ ጃንግ።
"ፀደይ ጃንግ እባላለሁ። በቤይጂንግ የውጭ ጥናቶች ዩኒቨርሲቲ የአማርኛ ቋንቋ መምህርት ነኝ" ስትል ራሷን አስተዋወቀች።
ፀደይ የሚለውን ስም ያወጡላት በዩኒቨርሲቲው አብረዋት የሚያስተምሩት ዶ/ር ስንቅነሽ አጣለ ናቸው።
የቻይንኛ ስሟ 'ቹንጋይ' ነው። 'ቹንጋይ' የሚለው ቻይንኛ ቃል ውስጥ 'ቹን' የሚለው ቃል የአማርኛ ትርጉሙ ፀደይ ማለት ነው።
በዚህ ምክንያት ነው ፀደይ ያሏት።
" ፀደይ በኢትዮጵያ ታዋቂ የሴት ስም እንደሆነ አውቃለሁ። ስሜን በጣም እወደዋለሁ" አለችኝ።
በነገራችን ላይ የቻይና ቋንቋ 'ማንዳሪን' ይባላል። በሌላ ስሙ 'ፑቶንኋ' በመባልም ይታወቃል። በተለምዶ ቻይንኛ ስለምንለው ግራ ላለማጋባት 'ቻይንኛ' እያልኩ እቀጥላለሁ።
ፀደይ እንደ ህጻን ልጅ እየተኮላተፈች አማርኛ ስትናገር ደስ የሚል ለዛ አለው። በጽሁፍም ይሁን በንግግር የተስተካከለ ዓረፍተ ነገርና ተገቢ ቃላትን ነው የምትጠቀመው።
በእርግጥ ፀደይ የአማርኛ ቋንቋን ዕውቀት ያገኘችው በልምድ ብቻ አይደለም፤ በትምህርትም ያደገ ነው። ከ2009 እስከ 2012 ዓ.ም ለተከታታይ አራት ዓመታት የአማርኛ ቋንቋ ትምህርቷን ተከታትላ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ዲግሪዋን አግኝታለች። ቋንቋውን ያዳበረችውም በዚሁ የትምህርት ቆይታዋ ነው።
ቀላል ግን አልነበረም። "በተለይ 'አለ' የሚለውን የአማርኛ ቃል ለመልመድ ፈተና ሆኖብኝ ነበር" ትላለች።
'ምኑ ነው ያስቸገረሽ?' አልኳት።
"ቃሉ ቀላል ቢሆንም የተለያዩ ቅርጾች [አልኩ፣ እያልኩ፣ ብዬ፣ እላለሁ፣ አላልኩም. . . ] የሚሉ አገላለጾች ስላሉትና ጠብቆና ላልቶ ስለሚነበብ ነው" አለችኝ።
አሁን ቃሉን አሳምራ ትጠራዋለች፤ በተገቢው አውድም ትጠቀምበታለች። በአማርኛ ቋንቋ የሚታተሙ ጋዜጦችንና መጻሕፍትን አሳምራ ታነባለች። አዲስ ዘመን፣ ዘ-ሐበሻ እና ፌዴራል ነጋሪት አዘውትራ የምታነባቸው ጋዜጦች ነበሩ።

የፎቶው ባለመብት, Zhang Chungai
የአማርኛ ፊልምና ድራማም ቢሆን አያልፋትም። ከተመለከተቻቸው ፊልሞች 'ሜድ ኢን ቻይና'ን ይበልጥ ትወደዋለች። 'በቀናት መካከል' የሚለው ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማም አላመለጣትም።
ፀደይ ለአማርኛ ሥነ ጽሁፍም እንግዳ አይደለች። ከአድማስ ባሻገር፣ ማህሌት፣ ጠይም እንቁ፣ የኦጋዴን ድመቶች እና ከቡስካ በስተጀርባን አንብባለች። ፍቅር እስከ መቃብርንም ቢሆን አትጨርሰው እንጅ የተወሰነ ያህል ኮምኩመዋለች።
ፀደይንና አማርኛ ቋንቋን ምን አገናኛቸው?
አስተማሪ መሆን የልጅነት ህልሟ ነበር። ለመምህርነት ሙያም ጥልቅ ፍቅር አላት።
ሙያውን ከአማርኛ ቋንቋ ጋር ያስተሳሰረላት ግን የኢትዮጵያ እና የቻይና ግንኙነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣት ነው።
ግንኙነታቸው እየተጠናከረ ቢመጣም በቻይና አማርኛ ቋንቋን በደንብ መናገር የሚችል ሰው እምብዛም የለም። ይህ ክፍተት ጎልቶ ታያት።
ፀደይ የሁለቱ አገራት ሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት እንዲጠነክር ቋንቋ ከፍተኛ ሚና መጫወት አለበት የሚል እምነት አላት።
በዚህ ምክንያት ነው አማርኛ ቋንቋን ለማስተማር ከፍተኛ ፍላጎት ያደረባት። ያለመችውን ከማድረግ ያገዳትም አልነበረም።
"ቋንቋ አዲስ እውቀት ለማግኘት የሚያስችል ቁልፍ ነው፤ ይህንን ቁልፍ እየያዝኩ ኢትዮጵያን በጥልቅ ለማወቅ ጉዞ ጀምሬያለሁ" ትላለች ፀደይ።
ለኢትዮ -ቻይና የሁለትዮሽ ግንኙነት በተለይ በባህል ልውውጥ ረገድ አስተዋጽኦ ለማድረግ ተስፋ ሰንቃለች።
ያጋጠማት ተግዳሮት ምንድን ነው?
የአማርኛ ቋንቋ አስተማሪ በመሆኗ በርካታ ተግዳሮቶች ገጥመዋታል።
እየሰራችበት ያለው የአማርኛ ቋንቋ ትምህርት ክፍል በቻይና የመጀመሪያው በመሆኑ ሁሉም ነገር ለእሷ አዲስ ነው። በቻይንኛ ቋንቋ የተጻፉ የአማርኛ መማሪያ መጻሕፍት የሉም።
ብዙ የማስተማር ልምድም የላትም።
እነዚህ ክፍተቶች ለፀደይ ፈታኝ ቢሆኑባትም አልተበገረችም።
"አዲስ ነገር ሲጀመር ተግዳሮት ብቻ ሳይሆን ብዙ ዕድልም ሊያመጣ ይችላል" የምትለው ፀደይ፤ በዩኒቨርሲቲው የትምህርት ክፍሉ ከተጀመረ በኋላ በርካታ የሥራ ጥሪዎች እንደቀረቡላትም ተናግራለች።
"የተለያዩ ተቋማትና ድርጅት ሠራተኞች ድርጅታቸው አማርኛ ቋንቋ የሚችል ቻይናዊ ሠራተኛ እንደሚፈልጉ እና ተማሪዎቹ ከተመረቁ በኋላ በድርጅታቸው መስራት እንደሚችሉ ነግረውኛል" ትላለች ፀደይ።
"የኢትዮጵያ የሥነ ጽሁፍ ትሩፋቶችን ወደ 'ቻይንኛ' ቋንቋ መተርጎም እፈልጋለሁ"
ፀደይ የአማርኛ ቋንቋ ችሎታዋን በትምህርት ማሳደግ ቅድሚያ የምትሰጠው ጉዳይ ነው። በአማርኛ በደንብ መራቀቅ ትፈልጋለች።
እየሰራችበት ያለው የትምህርት ክፍል በቻይንኛ የተጻፈ የአማርኛ ቋንቋ መማሪያ መጻሕፍት፣ መዝገበ ቃላት እና ሌሎች አጋዥ መጻሕፍት ስለሚያስፈልጉት እነዚህን የማዘጋጀት እቅድም አላት።
ፀደይ እቅዷ ይህ ብቻ አይደለም። የኢትዮጵያን የሥነ ጽሁፍ ትሩፋቶች ወደ ቻይንኛ ቋንቋ ለመተርጎም ታስባለች። ምንም እንኳን ይህ ጊዜ የሚያስፈልገው ቢሆንም በሂደት የኢትዮጵያን ባህል ለቻይናውያን ለማስተዋወቅ እሠራለሁም ብላለች። "እንቁላል ቀስ በቀስ በእግሩ ይሄዳል" ይህንኑ ለማጠናከር የተጠቀመችው አባባል ነው።
እርሷ ብቻ ሳትሆን ተማሪዎቿም ከጥቂት ዓመታት በኋላ ተመሳሳይ ሥራ እንዲሰሩ ለማብቃትም እየተጋች ነው። ፀደይ 12 ቻይናውያን ተማሪዎች አሏት።

ባሳለፍነው መስከረም ወር ላይ በቻይና መዲና በሚገኘው የቤይጂንግ የውጪ ጥናት ዩኒቨርስቲ ውስጥ የአማርኛ ትምህርት በመጀመሪያ ዲግሪ ሊሰጥ መሆኑን በቤይጂንግ የኢትዮጵያ ኤምባሲ በሚንስትር ማዕረግ የሕዝብ ዲፕሎማሲ ክፍል ኃላፊ የሆኑት አቶ ሳሙኤል ፍጹምብርሃን ለቢቢሲ መግለጻቸው ይታወሳል።
ዲፕሎማቱ በቻይናውያን ዘንድ አማርኛ ቋንቋን ለመማር ያለው ፍላጎት እየጨመረ በመምጣቱና የሁለቱ አገራት ግንኙነት እየጠነከረ በመሆኑ ቋንቋውን በመጀመሪያ ዲግሪ ለመስጠት መወሰኑንም ተናግረው ነበር።
በዚህም መሠረት የአማርኛ ቋንቋን ለመማር ፍላጎት ያላቸው 30 ቻይናውያን ተመዝግበው 12ቱ ትምህርታቸውን እየተከታተሉ ይገኛሉ።
















