ሠዓሊ እያዩ ገነት፡ ባሕር ዳርን የኢትዮጵያ 'የኪነ ጥበብ መዲና' ለማድረግ የሚተጋው ወጣት

እያዩ ገነት ትውልዱ በዱርቤቴ፣ ዕድገቱ በባሕር ዳር፣ ነዋሪነቱ በአዲስ አበባ ነበር፡፡
ከዕለታት በአንድ ጥበበኛ ቀን እያዩ ቆረጠ፡፡ በፍቅር የሚወዳት ከተማው ጠራችው፡፡ ነገ ዛሬ ሳይል ባሕር ዳር ተሳፈረ፡፡
ጨርቄን ማቄን ሳይል አባይ ማዶ ተገኘ፡፡
ይህ ገና የንዋይ ጡንቻው ላልፈረጠመው ወጣት አርቲስት የዋዛ ውሳኔ አልነበረም፡፡
ምክንያቱም የኪነ ጥበብ ጀማው የተሰበሰበው በሸገር ነው፡፡ ከሊቅ እስከ ደቂቅ፡፡ ከደራሲ እስከ ተደራሲ፡፡
አውደ ርዕዩም፣ መካነ ጥበቡም፣ ጎብኚውም፣ አድናቂውም፣ ገዢውም ሻጩም ኑሮውም ያለው እዚያ ነው፤ ሸገር፡፡
ባሕር ዳር ምን አለ? ባሕር ዳር ምንም የለም፡፡ ውበት ግን አለ፡፡
ከተማዋ ብዙም መኳኳል የምትፈልግ አይደለችም፡፡ ተፈጥሮ የኳላት ናት፡፡ አባይ ያለመለማት፣ ጣና በምርኮ የተነጠፈላት ከተማ ናት፡፡ ባሕር ዳር፡፡
ቢሆንም ግን እያዩ ቡሩሹን ይዞ ሄደ፤ ሊኩላት፡፡
ባሕር ዳር ከሌሎች ከተሞች የሚለያት ልምላሜዋ ብቻ አይደለም፡፡ ግማሽ ምዕተ ዓመት ያስቆጠሩት የአስመራ ዘንባባዎቿ ብቻም አይደሉም፡፡
ሁሉም አደባባዮቿ ማለት ይቻላል ስስ የጥበብ ክንድ ያረፈባቸው ናቸው፡፡
የባሕር ዳር አደባባዮች እንደ አዲስ አበባ አደባባዮች "በብረት ብሬስ" ፈገግታቸው አልታወከም፡፡
ብዙዎቹ ጥበበኛ መዳፍ ነካክቷቸዋል፡፡ ይነስም ይብዛ ዐይነ ግቡ ቅርጻ ቅርጾች ቆመውባቸዋል፡፡
እያዩን ይህ ሳያበረታው አልቀረም፡፡
ደግሞ ከአዲስ አበባ ሲነሳ እንዲህ አለ፡፡
"እኔ ካልጀመርኩት ማን ሊጀምረው ነው?"

ማነው ደግሞ እያዩ ገነት?
እያዩ ገነት ይባላል፡፡ የዕይታ ጥበብ ባለሞያ ነው፡፡ ከዚያ በፊት ግን የምጣኔ ሀብት ምሩቅ ነበር፡፡
አሁን ባሕር ዳር ዩኒቨርስቲ በኪነ ሕንጻ ትምህርት ክፍል ያስተምራል፡፡ ከዚያ በፊት ዩኒቲ ዩኒቨርስቲ መምህር ነበር፡፡
"አለ የሥነ ጥበብና ንድፍ ትምህርት ቤት" ገብቶ 2ኛ ዲግሪውን ተቀብሏል፤ ሊያውም በከፍተኛ ማዕረግ፡፡
እግረ መንገዱን በርካታ አውደ ርዕይ ላይ ተሳትፏል፡፡
ያኔም፣ ዛሬም፡፡ በተማሪነትም በአስተማሪነትም፡፡ በአገር ውስጥም፣ ከአገር ውጭም፡፡
ለምሳሌ የት ከተባለ በጎተ፣ በአሊያንስ፣ በጉራማይሌ፣ በብሔራዊ ሙዚየም፣ በአሜሪካ ኤምባሲ ሥራዎቹን አቅርቧል፡፡
ደግሞም ወደ አውሮጳ አቅንቶ በፈረንሳይ፣ ስዊድንና ስዊዘርላንድ፤ ደግሞም ወደ ደቡብ አሜሪካ ሄዶ በኢኳዶር፤ ደግሞም ወደ ሰሜን አሜሪካ ሄዶ በዩናይትድስቴትስ፤ ደግሞም አፍሪካ ተመልሶ በዩጋንዳ፣ ደግሞም መካከለኛው ምሥራቅ በኳታር በርካታ ሥራዎቹ ለዕይታ አብቅቷል፡፡
እያዩ ገነት የዕይታ ጥበብ ሥራዎቹ የዋዛ አይደሉም፡፡ ብዙዎቹ ይበል የሚያሰኙ ናቸው፡፡
እዚያም እዚህም ባቀረባቸው መራ መውጫ ( Debut) የሥዕል ዐውደ ርዕዮች ተሞካሽቶባቸዋል፡፡
ገሚሶቹ ደርዘኛና አማላይ ናቸው፡፡ ገሚሶቹ ኮርኳሪና ጥልቅ ናቸው፡፡ ለምሳሌ እርቅ ወይም "Reconciliation " ስለተባለው የሸራ ላይ ሥራው እንደ ዋዛ እናውጋ፡፡
ይኽ ሥራው በብሔራዊ ቤተመንግሥት ሁነኛ ሥፍራ ይዞለታል፡፡ እንዴት እዚያ ዘለቀ?
ታሪኩ እንዲህ ነው፡፡
አርቲስት እያዩ የአገሩ ሁኔታ እያስጨነቀው፣ አንዳንዴም እያባነነው ይመጣል፡፡ እንደ ሁላችንም፡፡
ለምን እንጋጫለን? ሲል የማይፈታ ጥያቄ ራሱን ጠየቀ፡፡
ምናልባት ከትናንት ጋር እርቅ ስላልፈጠርን ይሆን? ጥያቄ የሆነ መልስ መለሰ። ለራሱ፡፡
‹አንድ ሕዝብ ከትናንት ጋር ካልታረቀ ነገን ለማየት እንዴት ይቻለዋል?› ሲል አሰላሰለ፡፡
ይህ ማብሰልሰሉ ሐሳብ ጸነሰ፡፡ ሐሳቡ በሸራ ላይ አረፈ፡፡ በመጨረሻም ‹‹እርቅ›› (Reconciliation) የሚለው ሥራው ተወለደ፡፡
ባሕር ዳር ዩኒቨርስቲ ይህን ሥራውን ወደደው፡፡ ለጊዜው እዚህ በማንጠቅሰው ተመን ከፍሎ ገዛው፡፡
በአጋጣሚ ያን ሰሞን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወደ ባሕር ዳር መጥተው ነበር፡፡ ጥበበ ጊዮን ሆስፒታልን ሊመርቁ ነበር አመጣጣቸው፡፡
የእያዩን ሥራ ወደዱት፡፡ ይዘውት ሄዱ፡፡ እንደነገርናችሁ አሁን ይህ ‹እርቅ› የተሰኘው ሥራው በጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ ይገኛል፡፡
የእያዩ ሥራዎች የዋዛ አይደሉም፡፡
ለምሳሌ ውጥረት ወይም ‹Tension› የሚለው ሥራውን እናንሳ፡፡
ይህ ሥራ ስለ እያዩ ገነት አቅም ጮኽ ብሎ መናገር ይችላል፡፡ ‹ከሠራሁት በኋላ ቅርጹን በማየት ድንገቴ ርእስ ነው የሰጠሁት› ቢልም እሱ፣ ሥዕሉ ግን እያዩት ብቻ አንዳች ውጥረት ውስጥ የመክተት አቅም ያለው ነው፡፡
ሦስተኛ አስረጂ አቅርበን የእያዩን ነገር እንቋጨው መሰል፡፡

የፎቶው ባለመብት, Eyayu Art Gallery Facebook Page
40ሺህ ዶላር የተሸጠው ሥዕል
እያዩ አሜሪካን አገር መቀመጫውን ካደረገ ‹ወንፍል› ከሚባል ግብረ ሰናይ ድርጅት ጋር ለአንድ ሥራ ይስማማል፡፡
ሆኖም ድርጅቱ የሚሠራው ሥራ ሲረዳ ተሰማው፡፡ በአማራ ክልል ገጠራማ ቦታዎች ትምህርትን ማዳረስ ነው፡፡ እነሱ ሩቅ ሆነው ይህን ለወገኖቼ እየሠሩ እኔ እንዴት በሞያዬ ማገዝ ያቅተኛል አለ፡፡
ኢትዮጵያን በማዘመን የሚታወቁትን አፄ ምንሊክን በሸራ ወጠራቸው፡፡ ይህ ሥራው እጅግ ተወደደለት፡፡ ‹እምዬ› የሚለውን ስም ሰጠው፡፡
ግብረ ሰናይ ድርጅቱ ይህን ሥራውን ለጨረታ አቀረበው፡፡ 40ሺህ ዶላር ተሸጠ፡፡ የእያዩ ደስታ እጥፍ ድርብ ሆነ፡፡
በነገራችሁ ላይ እያዩ እያዩ ፍቅርና ሰላምን በመስበክ የጣና ማኅበራዊ ሚዲያ ሽልማት አሸናፊ ነው፡፡
እያዩ በባህሪው ቀና፣ ልስልስና ትሁት ይሆን ይሆናል፡፡ በሥራው ትጋት ግን ሸብረክ አያውቅም ይሉታል የሥራ አጋሮቹ፡፡
አሁን አሁን ይህ ባተሌነቱ እየከፈለው ይመስላል፡፡
ይህ ትጋቱ ወስዶ ወስዶ የት አደረሰው ካልን? ‹የአማራ ብልጽግና ፓርቲ አጥር ላይ› ይሆናል አንዱ ምላሻችን፡፡

አማራ ብልጽግናና ሞዛይክን ምን አገናኛቸው?
አርቲስት እያዩ ገነት ባሕር ዳር ሲመጣ ምን ይዞ መጣ? ሕልም ብቻ፡፡
ውቧን ከተማ በኢትዮጵያ ዋነኛ የጥበብ መዳረሻ የማድረግ ሕልም፡፡
እያዩ ይህን ህልም አጥርቶ ያለመው በአሜሪካ ላስቬጋስ፣ በፈረንሳይ ሉቨር ሳለ ነው፡፡ ሕልሙ አዲስ አበባ ቢጀመርም የዳበረው በፈረንጅ አገር ነው፡፡
የሆነ ጊዜ ፓሪስን ሲያይ መንፈሳዊ ቅናት ወረረው፡፡
የሉቨርን ግዙፍ መካነ ቅርስን ሲያይ ባሕር ዳር ምነው ሙዚየም በኖረ ሲል ተመኘ፡፡
ነገር ግን ያን ጊዜ ባሕር ዳር ገብቶ ሕልሙን ለማሳካት ቤሳ ቤስቲን አልበረውም፡፡
‹‹እኔ ሸማኔ ነኝ፤ መወርወሪያውን ብቻ ይዤ ነበር ባሕር ዳር የገባሁት›› ይላል እያዩ፡፡
ቀስ በቀስ በጨረታ መሳተፍ ጀመረ፡፡ የሚወዱት ሰዎች ቤታቸውን ጭምር በመያዣነት ሰጡት፡፡
ቀናነቱን፣ ተስፈኝነቱን፣ ትጉህነቱን ያዩ ሰዎች አበረቱት፡፡
ተበረታታ፡፡ ከዕለታት አንድ ቀን ደግሞ ለጥበብ ሩቅ የሚመስለው አማራ ብልጽግና ፓርቲ ጋበዘው፡፡

ፖለቲካን በሞዛይክ
ባሕር ዳር፣ አባይ ማዶ፣ ከሰማእታት መዘክር ባሻገር የቀድሞው ብአዴን ጽሕፈት ቤት አለ፡፡ ባለ 5 ፎቅ ሕንጻ ነው፡፡
ሲጠጉት ክብድ ይላል፡፡ ምናልባት በወታደሮች መከበቡ ይሆን? ምናልባት ፖለቲካ ተቦክቶ የሚጋገርበት ቤት ስለሆነ ይሆን?
ለመሆኑ ኪነ ጥበብና ፖለቲካ ጥለትና ሸማ ሊሆኑ ይችላሉ?
እያዩ "አዎና!" ይላል፡፡
የፖለቲካ አሉታዊ አውድን በኪነ ጥበብ ማስከን ይቻላል ብሎ ያምናል፡፡
ይህንኑ በተግባር ለማረጋገጥ የጥበበብ ጓዶቹን ቡሩሽና ጠጠር አስታጥቆ አሰማራ፡፡ በአማራ ብልጽግና ጽሕፈት ቤት ደጅ፡፡
በደጁ ሁሌም ወታደሮች አሉ፡፡ እያዩና ጓደኞቹ ግን ጠጠር ለቀማ ገቡ፣ ጠጠር ገጠማ ተሰማሩ፡፡ ቀን ተሌት ተጉ፡፡
ለእያዩ ዋናው የጥበብ አጋሩ አርቲስት ለይህኩን ወንዲፍራው የሚባል ዕውቅ ሰዓሊ ነው፡፡
በመጨረሻ 200 ካሬ ሜትር የሚሰፋ ‹ጥበበኛ› የፖለቲካ አጥር ገነቡ፡፡ አጥር ገነቡ ከሚባል አጥር አፈረሱ ቢባል ይቀላል፡፡
የአካባቢውን መንፈስ በአንድ ጊዜ ለወጡት፡፡
ወትሮ ለተራ ዜጋ ከብዶ የሚታየውን የፖለቲካ ጽሕፈት ቤት የውበት መቅደስ አስመሰሉት፡፡
"እንዳየኸው 'የፖለቲካ ስፔስ' አይመስልም፤ መለመድ ያለበት ነገር ነው፡፡" ይላል፡፡
"ብዙ ጊዜ በኛ አገር 'የፖለቲካ ስፔስ ማለት ኮስተር ያሉ ወታደሮች ያሉበት፣ መቅረብ እንኳ የምትፈራበት ፣ ቀና ለማለት የምትሰጋበት ስፍራ ነው፡፡ ይህን ለመለውጥ ነው የተነሳነው፡፡"
የሆነስ ሆኖ የፖለቲካ ፓርቲው ለኪነ ጥበብ እንዴት ቀናኢ ኾነ?
"እዚህ ውስጥ ያለ ፖለቲከኛ ነገ ሐሳቡን ሽጦ ሕዝብ ሲደግፈው የሚቆይ፣ ካልደገፈው ደግሞ የሚሄድ እንደሆነ መታሰብ አለበት" ይላል እያዩ፡፡
ይህን ቀለል ያለ ስሜት በአላፊ አግዳሚው ለመፍጠር፣ በአባይ ማዶ ነዋሪ ላይ ለማጋባት ይህ የርሱና ጓደኞቹ የሞዛይክ ጥበብ ሥራ ቢያንስ እምራዊ ጉልኽነት (Symbolic significance) እንዳለው መረዳት አይከብድም፡፡
እነ አርቲስት እያዩ 200 ካሬ ሞዛይክ አንጥፎ ለመጨረስ የወሰደባቸው ጊዜ ለመታመን ስቅ የሚል ነው፡፡
ወር ከ15 ቀናት ብቻ፡፡
ይህ ድንክ ጊዜ ሞዛይክ ጥበብ ከሚፈልገው ትዕግስትና ጥንቃቄ ጋር አብሮ አይገጥምም፡፡ ምናልባት በስኬት ማጠናቀቃቸው ለትጋታቸው ሌላ ምሥክር ይሆን ይሆናል፡፡
ለእያዩ ይህ በአማራ ብልጽግና አጥር ላይ የሠራውና ጎልቶ የተሞካሸለት የአደበባይ ጥበብ ሥራው ቢሆንም ከዚህ ባሻገር በርካታ ሥራ ሠርቷል፡፡
ለምሳሌ ጨጨሆ ባሕል ቤትን፣ ለምሳሌ አቫንቲ ሆቴልን፣ ቤንማስን፣ በራህ ናይልን፣ አዲስ አምባን ወዘተ፡፡
የእያዩ አሻራ በባሕር ዳር ከጊዜ ወደ ጊዜ ግዛቱን እያሰፋ ነው፡፡
ሕልሙን በሸራና በግድግዳ፣ በአደባባይና በወለል እያሳየ መምጣቱ ግለሰቦች ብቻ ሳይሆን ከጥበብ ጋር ሩቅ የሚመስሉ ድርጅቶችም እያመኑት እንዲመጡ አድርጓል፡፡
አማራ ሕንጻ ሥራዎች ኮንስትራክሽን ድርጅት ከነዚህ አንዱ ነው፡፡ እያዩ እዚያም አሻራውን አሳርፏል፡፡
‹‹በተለይ በተለይ አማራ ብልጽግና ሙያዊ ነጻነቴን ስላልነፈጉኝ አመሰግናቸዋለሁ" ይላል፡፡

የፎቶው ባለመብት, Eyayu Genet art Gallery Facebook page
‹ቀ› ፊደልና እያዩ፤ መሳ ለመሳ
ይህ ‹ትናንት፣ ዛሬና ነገ› የተሰኘው ሞዛይክ በስፋቱም በይዘቱም በግዝፈቱም በባሕር ዳር ትልቁ ነው፡፡
የሕዝቡን ሥነልቡና በመሸከም ማለፊያ ሥራ እንደሆነ መገመት ይቻላል፡፡
እርግጥ ሞዛይክ የሕዝብን ሥነልቦና፣ ታሪክና ማንነት ለማጉላት የተመቸ ሁነኛ የጥበብ ዘርፍ ነው፡፡
እያዩ የሠራው ሞዛይክ ግራና ቀኙ በፊደል ጀምሮ በፊደል የሚጨርስ ነው፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ምን ይሆን?
እያዩ እንዲህ ይላል፡-
"የማኅበረሰብ ትልቅነት የሚለካው፣ አስተዋይነቱ የሚመዘነው፣ ለሐሳቡ ውክልና ሰጥቶ ሲያልፍ ነው፡፡"
ምን ማለቱ ይሆን?
"አንድ ሕዝብ ሐሳቡን የሚወክልበት ፊደል ከፈጠረ፣ ያ ሕዝብ ትልቅ ሕዝብ እንለዋለን፡፡ ኢትዮጵያ የምትታወቅበትን ፊደል በዚህ ሞዛይክ ሥራ ለመወከል የፈለግነውም ለዚሁ ነው፡፡"
የአማራ ብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት የተሠራው ሞዛይክ በነጠላ ፊደላት የተሞሸረውም ለዚሁ ነው፡፡
‹‹ፊደላት ስናገናኘቸው ቃላትን ይመሰርታሉ፡፡ ቃላት ተዋቅረው ዐረፍተ ነገርን፣ ዐረፍተ ነገሮች አንቀጽን በኋላም የተደራጀ ሐሳብን ይሸከማሉ፡፡ ስለዚህ…››
ስለዚህ ምን?
‹‹ የሰው ልጅ ጽሑፍ ከመጻፉ በፊት ሥዕል ሣለ፡፡ የዋሻ ጥበብ እንለዋለን፡፡ ተግባቦት የተጀመረው በምልክት ነው፡፡ ምልክቶችን በተዋቀረ መልክ የሠሩት አባት እናቶቻችን ደግሞ ክብር ይገባቸዋል፡፡ ስለዚህ እነሱን ለማስታወስ ነው ሞዛይኩ በፊደላት የታጀበው››
ፊደላትን ለብቻ መገንዘብና ማድነቅ ይቻላል?
ፊደላት በቃላት ውስጥ ሲሆን ትርጉም ይሰጣሉ፤ ሆኖም ከቃላት ውጭ ምንም ይመስላሉ፤ ይዘነጋሉ፡፡ ፊደላት በቃላት ውስጥ ሲጎድሉ ግን ቃሉ ትርጉም ያጣል፡፡ ብርታታቸውን ለብቻ ማድነቅ እምብዛምም የማናዘወትረው ተግባር ነው፡፡
አንድ ፊደል ብቻዋን ምን ስሜት ትሰጣለች? ለምሳሌ ‹ቀ› ፊደል፡፡
‹ቀ› ብቻዋን ወገቧን ይዛ የቆመች ባልቴት ሆና ትታያለች፡፡ በእያዩ ሞዛይክ ሥራ ላይም ጎልታ ትታያለች፡፡
አርቲስት እያዩም በባሕር ዳር ከተማ እንደ ፊደሏ ይሆን? እንደ ‹ቀ› ፊደል፡፡
ልዩነቱ እሱ ወገቡን ይዞ አልቆመም፡፡ ሌሎች ‹ፊደላትን› አሰባስቦ ይተጋል፡፡ ትርጉም ለመስጠት፡፡
ለራሱም ለሚወዳት ባሕር ዳርም ጭምር፡፡
















