ፊልም፡ ባለሙያዎችን የማክሰር እኩይ ዓላማ ያለው የፊልም ‘ዝርፊያ’

ፕሮዲውሰሩ እስካሁን በአገር ውስጥ ከተሰሩ ፊልሞች በይዘትና ፕሮዳክሽን የተለየ ያለውን ፊልም ለመስራት ከረጅም ጊዜ ውጥን በኋላ ወደ ሥራ ገባ።
የቀረጻው ቦታ ላይ ባለሙያዎች ለ40 ቀናት 'ከትመው' የተሰራውን እና ሁለት ሚሊዮን ብር እንደወጣበት የተነገረለት ፊልሙ 'እንሳሮ' የሚል ስያሜ ተሰጥቶት ተመረቀ። በሲኒማ ቤት መቆየት የቻለው ግን ለሦስት ቀናት ብቻ ነው። ተሰረቀ።
ፊልሙ 'ከጅምሩ የነበረው ተቀባይነት' ተስፋ ለሰጣቸው ባለሙያዎች የመሰረቁ ዜና ልብ የሚሰብር ነበር። ዳይሬክተሩ ምስጋና አጥናፉ ክስተቱን "የሠርግ ቀን የመሞት ያህል ነው" ሲል ነው የገለጸው።
እንደ ኢትዮጵያ ፊልም ፕሮዲውሰሮች ማኅበር መረጃ ይህ ዕጣ በወራት ውስጥ ለሰባት ፊልሞችም የደረሰ ነው። 3ተኛው ዓይን፣ ኪያ፣ ሼምደፈር፣ ለኔ ካለሽ፣ እርሜን ብዝና፣ በሕግ አምላክ እና ወሬ ነጋሪ የሚል ርዕስ የተሰጣቸው ፊልሞች ተሰርቀዋል።
ፊልሞች እንዴት ይሰረቃሉ?
የእንሳሮ ፊልም ፕሮዲውስር የኔነህ እንግዳወርቅ ለዚህ ክስተት አዲስ አይደለም 'ሱማሌው ቫንዳም' የተሰኘ ፊለሙ በሲኒማ ቤቶች ለ15 ቀናት ብቻ ከታየ በኋላ ተሰርቆበታል። ታዲያ ፕሮዲውሰሩ ፊልሞቹ የተሰረቁት ሲኒማ ቤቶች ውስጥ እንደሆነ ይገልጻል።
"ምንም ጥርጥር የሌለው ነገር ምንድነው ፊልሙ [እንሳሮ] የተሰረቀው ሲኒማ ቤት ነው። ወደ 30 ሲኒማ ቤቶች አሉ አዲስ አበባ ውስጥ -የትኛው ጋር እንደወጣ ማወቅ ነው ከባድ የሆነው እንጂ የወጣው ከሲኒማ ቤት ነው" ሲል ያስረዳል።
የኢትዮጵያ ፊልም ፕሮዲውሰሮች ማኅበር ምክትል ፕሬዝዳንት የሆነው ኤርሚያስ ታደሰም የተመሳሳይ ችግር ሰለባ ነው። 'ሦስተኛው ዓይን' የተሰኘው ፊልሙ ለአንድ ወር ከታየ በኋላ ተሰርቆ ወጥቷል። ራሱ ለጻፈውና ላዘጋጀው ለዚህ ፊልም 700ሺህ ብር እንዳወጣበትም ይገልጻል።
ፊልሞች በተለያየ መንገድ እንደሚሰረቁ የሚናገረው ኤርሚያስ "ወይ ሲኒማ ቤት የሚተባበር ሰው ይኖራል፤ ወይ ፊልም የሚላከው ሰው እንዝህላል ሆኖ ፋይል ይጥላል" ብሏል።
የእንሳሮ ፊልም ዳይሬክተር ምስጋና አጥናፉም ወደ 30 ሲኒማ ቤቶች ቅጂ መላክ ለመቆጣጠር አስቸጋሪ እንደሚያደርገው ይገልጻል። "ከእነዚህ ሲኒማ ቤቶች ከየት ጋር እንዴት ወጣ የሚለውን እርግጠኛ መሆን አይቻልም" ሲል ገልጻል።
እንደ የኢትዮጵያ ፊልም ሰሪዎች ማኅበር ፕሬዝዳንትና የኢትዮጵያ የቅጂና ተዛማች መብቶች የጋራ አስተዳደር ማኅበር የቦርድ አባሉ ደሳለኝ ኃይሉ ግምት ፊልሞች 'ኤዲት' ከሚደረጉበት የፕሮዳክሽን ቦታ፤ ወደ ሲኒማ ቤት በማጓጓዝ ሂደትና ከሲኒማ ቤቶች ውስጥ ሊሰረቁ ይችላል።
የፊልሞችን ስርቆት ለመከላከል የተዘረጋ የቴክኖሎጂ ሥርዓት መኖሩን ኤርሚያስ ይጠቅሳል። ይህም ፊልሞችን በዲቪዲ ወይም በቪሲዲ ከማጫዎት ይልቅ በተዘረጋው ሥርዓት አማካኝነት በሲኒማ ቤቶች እንዲታይ ያስችላል። ሆኖም 'ሌቦቹ' ከቴክኖሎጂ እኩል እየተጓዙ ዝርፊያውን መቀጠላቸውን' ያስረዳል።
ፊልሞችን ማነው የሚሰርቀው? ለምንስ አላማ?
ለፊልሞች መሰረቅ በሲኒማው ላይ ያሉ የ'አንዳንድ ሰዎች' እኩይ ሀሳብ ዋነኛ ምክንያት ነው የሚለው ኤርሚያስ "በመስረቅ የሚደሰቱ ሰዎች አሉ። የተሻሉ የሚባሉ ነገሮችን ይመጣባቸዋል የሚባሉ መንገዶች ሁሉ ማጥፋት ይፈልጋሉ" ሲል ገልጿል።
"እገሌ እገሌ ብዬ ስም መጥቀስ ባልፈልግም የሰረቁት [ሦስተኛው ዓይንን] ግለሰቦች ናቸው። ሆን ተብሎ ነው የተሰረቀው። ሕግ ይዞታል።"
አሁን ላይ ፊልሞችን በመስረቅ ወደ ኪስ የሚገባ የረባ ጥቅም እንደሌለ የሚያስረዳው ደግሞ ምስጋና ነው።
"ይሄንን አድራጊው አካል አላማው ባለሙያዎችን መጉዳትን ነው። እሱ አይጠቀምም። ጥቅሙ ማበላሸት የሰዎችን ሞራል መንካት ነው፤... ኢንተርኔት ላይ ማሰራጨት አይችልም። በየቪዲዮ ቤቱ አንዴ ከተሰራጨ በኋላ እያንዳንዱ ሰው ይቀባበላል እንጂ ገዝቶ አያይም። የሚያገኘው ጥቅም የለም። እንደበፊቱ በሲዲ አሳትሞ ወደ ክፍለ አገር አያሰራጩም፤ እኛን ግን በገንዘብም በሞራልም ይጎዳናል"።
የምስጋናን ሀሳብ ፕርዲውስሩ የኔነህም ይጋራዋል። እንደ እርሱ ገለጻ ለፊልሙ ኢንደስትሪ ማደግ ግድ የማይላቸው ሰዎች በዚህ እኩይ ተግባር መሰማራታቸውን ያስረዳል።
"ኢንዱስትሪው አንድም እየሞተ የመጣው በዚህ ምክንያት ነው። የሚሰሩ ሰዎች ከፊልሙ መውጣታቸው ነው" እነዚህ አካላት ወይም ሰዎች ማናቸው ብለን ለባለሙያዎች ላቀረብንላቸው ጥያቄ ሰዎች በውል እንደማይታወቁና አላማቸው ግን "ማጥፋት" ብቻ እንደሆነ አስረድተዋል።
በሌላ በኩል ደሳለኝ ኃይሉ "በውስጣችን ያለው ችግር" ለፊልም መሰረቅ አንዱ ምክንያት ሊሆን ይችላል ሲል ያስቀምጣል።
"ለምሳሌ፣ ፕሮዲውሰሮች ራሳቸው ቀላል የማይባል ቁጥር ያላቸው ለፊልም ተዋንያን ወይ ክፋያውን በጊዜ አይከፍሉም ወይ ክፍያ ሳያጠናቅቁ የተለያዩ የተጭበረበሩ ምክንያቶችን እና ውሸቶችን እየሰጡ ብዙ ቅሬታ ይቀርባል። ውስጣችንም ጤነኛ ነገር የለም።...
"የዚህ አይነት እምነት ከሌለ በፕሮዲውሰሮችና በኤዲተሮች መካከል ጤነኛ ግንኙነት ከሌለ፣ በክፍያ ጭቅጭቅ ካለ ፊልሙን ተላልፎ ሊሰጥ ይችላል። ይህ አንድ ምክንያት ሊሆን ይችላል። መጀመሪያ ሌላውን ሌባ ከማለታችን በፊት ራሳችን ቤት ያለውን መፈተሽ አለብን" ሲል ተናግሯል።
የፊልም ስርቆት ምን አይነት ችግርና ስጋትን ፈጠረ?
ፊልሞች ላይ የሚፈጸመው 'ዝርፊያ' ከፊልም ዳይሬክተሩ እስከ ሲኒማ ቤት ባለሙያዎች የሚዘልቅ ጉዳት እንደሚያደርስ የሚጠቅሰው ደሳለኝ በዓመት እስከ 120 ፊልሞች ይሰሩ እንደነበር አስታውሶ በስርቆቱ ምክንያት ግን ይህ ቁጥር እጅግ እያሽቆለቀለ መጥቷል ይላል።
በሌላ በኩል የፊልም ፕሮዲውሰሮችና ሌሎች ባለሙያዎች ዘርፍ በመቀየር ወደ ሌሎች ሥራዎች እየተሰማሩ ሰለመሆኑም ያስረዳል።
"በፊልሙ ሥራ የእሴት ሰንሰለት ውስጥ ያሉ ሰዎች ከፍተኛ ኪሳራ እየገጠማቸው ነው።"
እንደ ምስጋና ገለጻ የፊልም ስርቆት በዚህ የሚቀጥል ከሆነ የተለያዩ ችግሮችን ያስከትላል።
"ፊልም ታሪክ ይሰንዳል። ፊልም ማኅበረሰብን ይቀርጻል። ፊልም የገቢ ምንጭ ነው። መንግሥት ግብር ያገኝበታል። ብዙ ጥቅሞች ያስገኛል። ስርቆቱ በዚህ ከቀጠለ ሰዎች ፊልም መሰራት ያቆማሉ። ስለዚህ በሥራው የሚተዳደሩ ሰዎች አይኖሩም ማለት ነው። ፊልም ለማስተማር የተከፈቱ ትምህርት ቤቶች አሉ፤...እነዚህ ሁሉ ይቆማሉ። ማን የሚያከስር ሙያ ይማራል?" ሲል ይጠይቃል።
ነገሩ "ለጊዜውም ቢሆን ተስፋ ያስቆርጣል" የሚለው ደግሞ ኤርሚያስ ነው።
ይህ ድርጊት ከሙያው እንዲገታ ባያደርገውም የሥራ ፍጥነቱንና ዕቅዱን እንዳዛባበት ገልጿል። በዕቅዱ መሰረት የተሰረቀው ፊልም ሁለተኛ ክፍል የሚወጣበት ወቅት ላይ ቢሆንም አሁን ላይ ግን ምንም እንቅስቃሴ እንደሌለ ገልጿል።
በስርቆቱ ምክንያት "እንደ አገር ተጎጂ ነን" ሲል የሚናገረው ባለሙያው "ሂሳቡ ሲሰራ ሰውዬው [የፊልሙ ባለቤት/ፕሮዲውሰር] ብቻ አይደለም ተጎጂው። በዚያ ሥራ የሚተዳደሩ ሰዎች፣ ሲኒማ ቤቶች፣ መንግሥትም የጉዳቱ ሰለባ ይሆናሉ" ብሏል።
የኔነህ እንሳሮ ፊልም ከመሰራቱና ከመሰረቁ በፊት የገዛው የፊልም ጽሁፍ እንደነበረ አስታውሶ፣ አንድም ስርቆቱ ባደረሰበት ኪሳራ ሌላም 'ሰርቼው ብሰረቅስ' በሚል ስጋት ወደ ሥራ አለመግባቱን አንስቷል።
እናም እንደ ባለሙያዎቹ አስተያየት ይህ ድርጊት የተወሳሰበ ችግር ከመፍጠሩ በፊት መፍትሄ ሊበጅለት ይገባል። እንዴት?
የፊልም ስርቆትን እንዴት መከላከል ይችላል?
የምስጋና የመፍትሄ ሀሳብ ባለሙያዎች ጠንካራ ማኅበር ሊኖራቸው ይገባል የሚል ነው።
"ባለሙያው ራሱን በደንብ አደራጀቶ እነዚህን ሰዎች ራሱ ጉያ ውስጥም ካሉ፣ ከውጪም ካሉ ከመንግሥት ጋር ተባብሮ ነቅሎ ማውጣት ነው።"
እንደ ደሳለኝ ገለጻ ችግሩን ከመሰረቱ ለመፍታት ሥራው 'ከውስጥ' መጀመር አለበት። "ስንጮህ መጀመሪያ ራሳችን ጋር ያለውን ልክ ያልሆኑ፣ ከሥነ ምግባር ያፈነገጡ አሰራሮችን መፈተሽ ያስፈልጋል። ከሌላው ብቻ መብት መጠየቅ አይደለም" ሲል ገልጿል።
"ስንት ባለሙያ ነው የማኅበሩ አባል?" ሲል የሚጠይቀው ፕሬዝዳንቱ የባለሙያዎች ተሳትፎ መቀዛቀዝ ማኅበሩ ጠንካራ ድምጽ እንዳይኖረውና የባለሙያውን መብት እንዳያስከብር እንቅፋት ሆኗል ሲል ያስረዳል።
መንግሥትም ሕግ ማስከበር ይገባዋል ሲል የሚያነሳው ደሳለኝ ከሲኒማ ቤት ባለቤቶች፣ ከባለሙያዎችና ከመንግሥት ጋር በመምከር ጠንካራ መፍትሄ ላይ መድረስ ይቻላል ሲል ጠቁሟል።
ደሳለኝ የእምሮ ንብረት ጥበቃ ጽ/ቤት የፊልም ዝርፊያን ለመከለከል የሚጠበቅበትን አልተወጣም ሲልም ወቅሷል።
በኢትዮጵያ የአእምሮአዊ ንብረት ጥበቃ ጽህፈት ቤት የቅጂ መብት ጥበቃና ልማት የሥራ ሂደት ኃላፊው አቶ ናስር ኑሩ ተቋማቸው በቅጂ መብት ዙሪያ ግንዛቤን ማስጨበጥ ይህም የአእምሮአዊ ንብረቶች ሲዘርፉ መወሰድ ያለባቸውን ርምጃ ማስተማር፤ ዜጎችን ስለለቅጂ መብት ማስተማር እንዲሁም ለአእምሮአዊ ንብረቶች የምዝገባ ምስክር ወረቀት መስጠት ከዋና ዋና ሥራዎቹ መካከል የሚጠቀሱ ናቸው ብለዋል።
'ፊልሞች ተሰረቁ የሚል' አቤቱታ ለጽህፈት ቤቱ እንደሚቀርብ የሚገልጹት ኃላፊው "ወደኛ ሲመጡ ማድረግ ያለባቸውን ነገር ነው የምንነግረው። ግንዛቤ ወይም ትምህርት እንሰጣለን" ብለዋል። ሆኖም የቅጂ መብት የግለሰብ በመሆኑ ጉዳዩን ወደ ሕግ የሚወስደው ባለመብቱ ነው ሲሉ አስረድተዋል።
"እኛ እንደንብረት ነው ምንቆጥረው ንብረት ሲሰረቅ መደረግ ያለበት ነገር ነው የሚደረገው። የተመዘገበ መሆኑን ፍርድ ቤት ከጠየቀን ማስረጃ እንሰጣለን። ባለንብረቱ ራሱ ነው መረጃዎችን አስባስቦ ክሱን የሚመሰርተው" ብለዋል።
"እኛ ከምንሰራው ውጪ ሰው ሌቦችን አጥፊዎችን መጸየፍ አለበት። ሰርቆ የሚመጣን ሰው የሚቀበል ከሌለ የሚሰርቀው ውጤታማ አይሆንም። ሰው ኮፒ [የተሰረቀ] እንዳያይ እኛም ሥራ መስራት አለብን" ሲል የሚገልጸው ደግሞ የፊልም ባለሙያው ኤርሚያስ ነው።

















