እንዳለጌታ ከበደ፡ "የተዳከመውን የንባብ መንፈስ የማነቃቃት" ዓላማ ያለው ዛጎል የመጽሐፍት ባንክ

እንዳለ ጌታ ከበደ

የፎቶው ባለመብት, Walia books

የብዕሩ ማህፀን የወለዳቸው በርካታ ሥራዎችን ለአንባቢያን አድርሷል። ያለስስት ይጽፋል። ያለ ድካም ጥናትና ምርምር ያደርጋል።

13 ረጅምና አጫጭር ልብወልድ፣ ኢ ልብወለድና የግጥም መጽሐፍትን አሳትሞ ለንባብ አብቅቷል።

ጥናትና ምርምርን መሠረት አድርጎ ያዘጋጃቸው መጽሐፍቱ እንደተደከመባቸው የሚያስታውቁ ናቸው ተብሎ ተመስግኗል።

በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩሩ ጽሑፎችንም ለተለያዩ የህትመት መገናኛ ብዙኃን በየወቅቱ ያጋራል።

በቅርቡ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በፎክሎር ሦስተኛ ዲግሪውንም አግኝቷል።

አሁን ደግሞ በኢትዮጵያ ባልተለመደ መልኩ ዛጎል የተሰኘ የመጽሐፋት ባንክን መስርቷል - ደራሲ እንዳለጌታ ከበደ (ዶ/ር)።

የመጽፍት ባንክ ለምን?

ይህ ባንክ ከተመሰረተ ከ6 ወራትን የሚልቅ ጊዜን ያስቆጠረ ሲሆን፣ በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች መጽሐፍት ቤቶችን በማጠናከር የንባብ ባህልን ማሳደግ ዋነኛ ዓላማው ነው።

እስካሁንም ወደ 8 ሺህ ገደማ መጽሐፍትን ወደተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች አሰራጭቷል።

ዛጎል የመጽሐፍት ባንክ ከተለያዩ አካላት የሚያሰባስባቸው መጽሐፍት ወይም የሚበረከትለትን ገንዘብ መጽሐፍትን በመግዛት በግለሰቦች ከተቋቋሙ ቤተ መጽሐፍት እስከ ከፍተኛ የመንግሥት የትምህርት ተቋማት ያሰራጫል።

እንዳለጌታ መጽሐፍትን ሰብስቦ ለማረሚያ ቤቶችና ትምህርት ቤቶች ማሰራጨት የሚታወቅበት ተግባሩ ነው።

"ልዩነቱ ይሄ [የመጽሐፍት ባንኩ] የተደራጀ የተቀናጀ ቋሚ ቢሮ፣ ቋሚ ሠራተኛ ያለው ወጪ የሚጠይቅ ጉልበት የሚጠይቅ መሆኑ ነው። .... ያነበቡ እንዴት እንደሚፈወሱ አይቻለሁ። ያነበቡ የሚያደርጉትን ያውቃሉ። የሚያደርጉትን ካወቁ ደግሞ ኃላፊነት ይሰማቸዋል። ኃላፊነት የሚሰማው ደግሞ ለራሱም ለአገሩም መድኃኒት ለመሆን እንጂ ችግር ውስጥ ለመክተት የሚተጋ አይሆንም " ሲል ለዛጎል የመጽሐፍት ባንክ መመስረት ምክንያት የሆነውን ጉዳይ አስረድቷል።

'የአእምሮ ልማት' - የዛጎል የመጽህፍት ባንክ ዓላማ

ደራሲው 'ዛጎል' ከተሰኘው የረጅም ልቦለድ መጽሐፉ የተገኘውን ገቢ በርዕሱ የተሰየሙ መጽሐፍት ቤት ከፍቶ በአነስተኛ ክፍያ የንባብ አገልግሎት ይሰጥ ነበር።

ታዲያ ይህ ተግባሩ ከተለያዩ አካባቢዎች "እኛ ጋ መቼ ነው የምትከፍቱት?" የሚሉ ጥያቄዎችን ማስከተሉን ይገልጻል።

እናም መጽሐፍትን በማሰባሰብ ማረሚያ ቤቶችን ጨምሮ ወደ ተለያዩ አካባቢዎች ይልክ እንደነበር አስታውሶ፣ ይህንን ተግባር ቋሚ በሆነ መንገድ የመስራት ሃሳብ እንዳደረበት ይገልጻል።

እንዳለጌታ (ዶ/ር) "የወደቀን የሚያነሳ፣ የታመመን የሚያሳክም፣ አረጋውያንን የሚንከባከብ፣ አሳዳጊ የሌላቸውን ልጆች አሳድጎ ለቁም ነገር የሚያበቃ ብዙ ድርጅት እንዳለ ሁሉ የአእምሮ ልማት ላይ የሚሰራ ያስፈልጋል" ይላል።

በዚህ እሳቤ "የተዘጉ ላይብረሪዎችን ለማስከፈት፤ ላይብረሪ ያልነበረባቸውን ቦታዎች እንዲኖሩ ለማድረግ እና የተዳከመውን የንባብ መንፈስ ለማነቃቃት" የሚሰራ የንባብ ባህል ላይ የሚያተኩር የበጎ አድራጎት ድርጅት ለመክፈት መወሰኑን ገልጿል።

በዚህም መነሻ ዛጎል የመጽሐፍት ባንክ ተቋቋመ።

እንደ ባንኩ መስራች ገለጻ በራሳቸው ተነሳሽነት የንባብ አገልግሎት የሚሰጡ ግለሰቦችን መደገፍ የባንኩ መነሻ እሳቤ ነበር። ሆኖም በመደበኛም ይሁን በከፍተኛ የመንግሥት ትምህርት ተቋማት ማጣቀሻዎችን ጨምሮ የመጽሐፍት እጥረት መኖሩን በማስተዋል ሀሳቡ ከፍ ብሏል።

በዚህም መነሻ በገጠርና በከተማ በትምህርት ተቋማት ውስጥ ለሚገኙ ቤተ መጽሐፍት ድጋፍ መደረጉን ገልጿል።

እስካሁን ባንኩ ከለጋሾች ያገኘውን መጽሐፍት ጅማ፣ አዋሽ መልካሳ፣ ደብረ ብርሃንን ጨምሮ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች አሰራጭቷል።

ባንኩ ቤተ መጽሐፍት በሌለበት መጽሐፍት ቤት እንዲቋቋምና ዜጎችን፣ መንግሥትን፣ ባለሀብቶችንና ሌሎች አካላት "የማነሳሳት እና የመወትወት" ዓላማም ያነገበ ነው።

የሚገነቡትም አቢያተ መጽሓፍትም በታዋቂ መጽሐፍት ርዕስ የሚሰየሙ ሲሆን ስያሜው የደራሲዎቹ የትውልድ ስፍራን መሰረት የማያደርግ ነው።

እናም የመጽሐፍት ባንኩ በሚያልፍበት ሂደት ዋነኛ ግብ ምክንያታዊ የሆነ ዜጋ መቅረጽ ነው።

"ድንጋይ ለመወርወር የሚቸኩል ሳይሆን ምን እየተባለ እንደሆነ የሚጠይቅ፤ በምክንያት የተደገፈ ሀሳብ ይዞ ማብራራት የሚችል ትውልድ እናምጣ። አለበለዚያ አስቸጋሪ አዘቅት ውስጥ እንገባለን ብለን አምነን ነው" ሲል አስረድቷል።

ለውጤታማ ቤተ መጽፍት እውቅና የሚሰጠው የባንኩ አሰራር

ዛጎል የመጽሐፍት ባንክ ከምስረታው ጀምሮ ባሉት ስድስት ወራት በአገሪቱ ለሚገኙ 40 ቤተ መጽሐፍት ለእያንዳንዳቸው ከ200 እስከ 300 የሚሆኑ የመጽሐፍት ድጋፍ የማድረግ ውጥን አለው። እስከ ነሐሴ ወር የመጀመሪያ ሳምንት ባንኩ ለ32 ቤተ መጽሐፍት የመጽሐፍ ስጦታ እንደተደረገ እንዳለጌታ (ዶ/ር) ጠቅሷል።

ታዲያ ባንኩ ድጋፍ ያደረገላቸውን ቤተ መጽሐፍት ላይ ክትትል እንደሚያደርግም ጠቁሟል። "ለእያንዳንዱ ድጋፍ የሰጠነው ክፍል ምን የተለየ ነገር አደረገ? ምን ለውጥ አመጣ? ብለን እናጠናለን። አንባቢ እንዲበዛ የሚያደረጉት ጥረት አለ ወይ? ልጆች እንዲያነቡ አድርገዋል ነው ወይስ ዝም ብለው መደርደሪያ ላይ ደርድረዋቸዋል? እናወዳድራቸዋለን ማለት ነው።"

ከአርባዎች ምርጥ የተባሉትን 12ቱን መርጠን ሕዝብ በተሰበሰበበት፣ የከተማው ማኅበረሰብ በተሰባሰበበት...ምስጋናችንን ለመግለጽ ነው የመጣነው ብለን 981 መጽሐፍትን ስጦታ እንሰጣለን " ሲል አስረድቷል።

ከደራሲ እንዳለ ጌታ ከበደ ሥራዎች መካከል ከፊሎቹ

የፎቶው ባለመብት, Zagol Telegeram

981 መጽፍት ለምን?

ደራሲው በዚህ ቁጥር መጽሐፍት መለገስ የታሰበበትን መነሻ ሲመልስ ታሪክን መሰረት አድርጎ ነው።

"በታሪክ ሳነብ አጼ ቴዎድሮስ መቅደላ ላይ የሰበሰቡት መጽሐፍት 981 ነበሩ። መጽሐፍቶቹ ፈረንሳይ፣ እንግሊዝ የተለዩ አገራት ተበታትነዋል። ስለዚህ በዚህ አጋጣሚ መጽሐፍት ላይ ሲሰሩ የነበሩ ነገሥታትን ማክበር ተገቢ ስለሆነ" ቁጥሩ ለዚህ መታሰቢያ እንዲሆን የተመረጠ መሆኑን አስረድቷል።

ከተመረጡት 12 ቤተ መጽሐፍት ልቀው ለተገኙ አቢያተ መጽሐፍት ተጨማሪ 2000 መጽሐፍት ይበረከትላቸዋል። ለዚህም ስኬት ቤተ መጽሐፍቱ የሥነ ጽሑፍ ምሽት ማዘጋጀትን ጨምሮ የንባብ ባህል ለማስፋፋት የሚረዱ ተግባራትን ማከናወን ይጠበቅባቸዋል።

በሌላ በኩል ለመጽሐፍት ባንኩ የሚለገሱ መጽሐፍትን ወደ ተለያዩ አካባቢዎች በምክንያት እንደሚሰራጩ እንዳለጌታ (ዶ/ር) ይናገራል። "አንዱ መርሃችን ያላነበብነውን አናስነብብም" ነው።

ሰዎች በተለያዩ መንገዶች የሚለግሱንን መጽሐፍት የትኛው መጽሐፍ የት ቢሄድ እንደሚሻል አይተን፣ ለይተን፣ መርጠን ነው እንጂ ስለተሰጥን አንሰጥም። በሌላ ቋንቋ የተጻፈ እንኳን ቢሆን ለሚያውቁ ሰዎች አስነብበን፣ ስለምንድን ነው የሚያወራው ብለን" እናከፋፍላለን ብሏል።

ለባንኩ መጽሐፍት የሚያበርክቱ ሁሉም ሰዎች ዛጎል የመጽሐፍት ባንክ በተሰኘው የቴሌግራም አማካኝነት ምስጋና የሚቀርብላቸው ሲሆን እስካሁን ከፍተኛ መጽሐፍት ያበረከተችው ራማ ሰይፉ የተባለች ሴት ነች።

ራማ ያነበበችውንና ታከራያቸው የነበሩ 400 መጽሐፍት ለባንኩ ገቢ አድርጋለች።

"እያንዳንዱ መጽሐፍ ላይ ሦስት አራት ጊዜ ከራማ ሰይፉ በዛጎል የመጽሐፍት ባንክ አማካኝነት ለኢትዮጵያውያን አንባቢዎች የተለገሰ" የሚል ማህተም ማረፉን ያስረዳው እንዳለጌታ (ዶ/ር) ይህም ከ50 በላይ መጽሐፍ ለሚያቀርቡ ለጋሾች በሙሉ የሚደረግ ነው ብሏል።

በሌላ በኩል ለጋሾች የሰጧቸው መጽሐፍት የት እንደደረሱ ማወቅ ቢፈልጉ እንኳን ዝርዝር መረጃ ባንኩ የሚያቀርብበትም ሥርዓት አለው።

8 ሺህ መጽፍት የተሰባሰበበት የባንኩ የስካሁን ሂደት

ባንኩ እስከ ሐምሌ ወር መገባደጃ 5 ሺህ መጽሐፍትን አሰባስቦ ወደ ተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ያሰራጨ ሲሆን በነሐሴ ወር የመጀመሪያ ሳምንት ላይ ደግሞ 3 ሺህ መጽሐፍትን ያጓጉዛል ብሏል። በተያዘው ክረምት እስከ 10 ሺህ መጽሐፍት ማሰባሰብ የባንኩ ዕቅድ ነው።

'የመጽሐፍ ድጋፍ አድርጉልን' በርካታ ጥያቄዎች ለባንኩ እየቀረበ እንደሆነ የገለጸው ደራሲው "ገጠር ከዋናው አስፓልት ስንትና ስንት ኪሎ ርቀው የሚገኙት ሁሉ ጥያቄ እያቀረቡ ነው። ይሄ በጣም ደስ ያሰኛል" ብሏል።

በሌላ በኩል አዳዲስ መጽሐፍት የሚያወጡ፣ የቀድሞ መጻሕፍታቸውንና ያሰባሰቧቸውን መጽሐፍት "እንደተጠበቀው" እያበረከቱ ይገኛል።

የቢሮ ኪራይ በነጻ ከማቅረብ ጀምሮ "ሥራ እዘዙኝ እስከሚል" ድረስ ባንኩን በተለያየ መንገድ እያገዙት የሚገኙ ወጣቶች አሉ።

ከአገር ውጪ የሚገኙ ጓደኞቹን በማስተባበር እና ገንዘብ በማሰባሰብ መጽሐፍትን ገዝቶ የሚያበረክት መኖሩንም እንዳለ ጌታ ለቢቢሲ ተናግሯል።

"የቤት ኪራዩም ራሱ እድሜ ለህንጻው ባለቤቶች እንጂ የሚቻል አይደለም" የሚለው ደራሲ እንዳለ ጌታ፣ የሠራተኞች ክፍያና የመጽሐፍት ማጓጓዣን ጨምሮ የባንኩን ሌሎች ወጪዎች 'አታስቡ እኔ እሸፍናለሁ!' የሚሉ ሰዎች ይመጣሉ" የሚል ተስፋ የነበረው ቢሆንም ውጤቱ በተቃራኒው እንደሆነበትና በእራሱ የገንዘብ ድጋፍ ላይ ብቻ ባንኩ መንጠልጠሉን ይናገራል።

እስካሁን የባንኩ የገንዘብ ምንጭ የዛጎል ረጅም ልብወለድ የመጨረሻ ዕትም ገቢ ነው። ከዚህ በኋላ ባንኩን በገንዘብ የሚደግፉ ሰዎች ይመጣሉ የሚል ተስፋም አለው።

በሌላ በኩል ደራሲው ከዋልያ መጽሐፍ ጋር በመሆን ደራሲያንን ከአንባቢዎች የሚገናኙበት ሳምንታዊ መርሃ ግብር እያስተባበር ይገኛል።

አንባቢዎች በነጻ የሚታደሙበት መርሃ ግበሩ ደራሲዎች ስለ መጽሐፋቸው ገለጻ የሚያደርጉበትና ከተደራሲያን ጋር የሚወያዩበት፣ ፊርማቸው ያረፈበትን መጽሐፍ የሚያቀርቡበት ነው።

እስካሁንም ከ25 በላይ ደራሲዎች ተጋብዘው በሥራዎቻቸው ዙሪያ ውይይት መደረጉን እንዳለ ጌታ ይገልጻል።