የኢትዮጵያ ቡና በስኒ 65 ዶላር በኪሎ እስከ 330 ዶላር እንዲሸጥ ያደረገው ውድድር

የፎቶው ባለመብት, TAMIRU
እንደ መግቢያ
ካፕ ኦፍ ኤክሰለንስ [በግርድፉ የጥራት ሲኒ እንበለው ይሆን] የቡና የጥራት ውድድር ነው።
ባለፉት 20 ዓመታት የጥራት ውድድር በዋና ዋና የቡና አብቃይ አገራት ውስጥ ይካሄድ ነበር።
በኢትዮጵያ ውድድሩ የተጀመረው ካለፈው ዓመት ጀምሮ ነው።
ዓላማው ከተመረቱት ቡናዎች መካከል የተሻለውን ቡና መርጦ በዓለም አቀፍ ጨረታ ለታላላቅ ገዢዎች መሸጥ ነው።
በተጨማሪም ትልቁ ዓላማው ገበሬዎችን ማስተዋወቅ እንዲሁም በአንድ አገር ያሉትን ልዩ ጣዕም ያላቸውን ቡናዎች እና አምራቾችን ማስተዋወቅ ነው።
"ሲዳማ ውስጥ ያደገ ማንም ሰው ስለ ቡና በደንብ ያውቃል"
ታምሩ ታደሠ ውልደቱ እና ዕድገቱ በሲዳማ ክልል በምትገኘው ቀጠና ቀበሌ ነው።
ታምሩ ከቡና ጋር የተዛመደ ሥራ የጀመረው በቅርቡ ነው።
ግን ቡናን ያውቃል። በደንብ ያውቃል።
"ሲዳማ ውስጥ ያደገ ማንም ሰው ስለ ቡና በደንብ ያውቃል። ይሰማል። አብዛኛው የአካባቢው ነጋዴ ቡና ነው የሚነገደው" ይላል።
ትምህርቱን በኤሌክትሪካል ምህንድስና ካጠናቀቀ በኋላ ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ማስተማር ጀመረ።
ለሁለተኛ ዲግሪ ትምህርቱ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ '5 ኪሎ' ገባ።
ከትምህርቱ ጎን ለጎን ቡና ኤክስፖርት በሚያደርግ ድርጅት ውስጥ ተቀጠረ።
"ማስተርስ (ሁለተኛ ዲግሪ) 5 ኪሎ እየተማርኩ ዱካለ ዋቀዮ የሚባል ድርጅት ተቀጥሬ 6 ዓመት ሰርቻለሁ። ስለቡና ያወኩት ያኔ ነው" ብሏል ለቢቢሲ።
ስለቡና ሥራ ዕውቀቱ ሲያገኝ ቀጣዩ እርምጃ ደግሞ የራሱን ድርጅት አቋቁሞ መሥራት ነበር።
ከዓመት በፊት ዓላማው ተሳክቶ ድርጅቱን አቋቋመ።
"ሲዳማ መፈጠር ስለቡና እንድታስብ ያደርጋል። ቡናው በዕውቀት ሳይሆን በልምድ ስለነበር በፊት ቁጭት ነበረኝ። ቡና ላይ ብሠራ ስለምል ልምዱም ጠቀመኝ።"
የግድ ግን ወደ እርሻ መግባት አልነበረበትም። "የቡና እርሻ እኔ የለኝም። እርሻ ካላቸው ገበሬዎች ነው የምንሰበሰብው። የተለያየ መጠን ያለው የቡና እርሻ ካላቸው ወደ 400 ከሚጠጉ ገበሬዎች ነው ቡና የምንሰበስበው" ብሏል።
"ባለፈው ዓመት አንድ ኪሎ ቡና 407 ዶላር ተሽጧል።"
ካፕ ኦፍ ኤክሰለንስ ባለፈው ዓመት ነው ኢትዮጵያ ውስጥ የተጀመረው።
ኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ሂደቱን አስቸጋሪ አድርጎት የነበረ ቢሆንም ብዙ ገዢዎች ግን ተሳትፈውበታል።
ውድድሩ በጣም ጥብቅ እና የምርጦች ምርጥ የሚወጣበት ነው።
በመረጃ እናስቀምጠው። በዘንድሮው ካፕ ኦፍ ኤክሰለንስ 1864 የቡናዎች ለውድድር ቀርበው ነበር።
"ከመላው ቡና አምራች አካባቢዎች የመጡት ሁሉ ተቀምሰው የተሻሉ የተባሉት 40ዎቹን ወደ ስምንት አገር ልከናል" ይላሉ ቅድስት።
ቀጣዩ ገዢዎች እነዚህን 40 ቡናዎች ገዢዎች በጨረታ መግዛት ነው።
"እነዚህ ልዩ ጣዕም ያላቸው ቡናዎች የኢትዮጵያ ቡና ናቸው። ገዢዎቹ ልዩነታቸውን እና ጣዕማቸው ስለሚፈልጉ ነው ተጫርተው የሚገዙት" ይላሉ የካፕ ኦፍ ኤክሰለንስ ኢትዮጵያ አማካሪ ወ/ት ቅድስት ሙሉጌታ።
"ባለፈው ዓመት 407 ዶላር በኪሎ የተሸጠው ለኢትዮጵያ ቡና የተከፈለ ትልቁ ዋጋ ነው። አቶ ንጉሤ ገመዳ ቡና አምራች ከሲዳማ ክልል ናቸው በዚህ ዋጋ የሸጡት።"
ባለፈው ዓመት አንደኛ የወጣው ሰባት ኬሻ ቡና ነው የተሸጠው።
አንዱ ኬሻ 60 ኪሎ ነው።
የዘንድሮ አሸናፊም ከሲዳማ ክልል አልወጣም። ተረኛው ታምሩ ታደሠ ነው።

የፎቶው ባለመብት, Fintrac Inc.
"24 ኬሻ ነው ከፍተኛው ማቅረብ የሚቻለው"
ስለ ካፕ ኦፍ ኤክሰለንስ በአጋጣሚ ሰምቶ ለውድድሩ እንዲዘጋጅ ገፋፋው።
"ባለፈው ዓመት ያሸነፈው ጓደኛዬ ነው። የማውቀው ሰው ነው። ያም አስተዋጽኦ ነበረው። በዚያው ቡና ለማዘጋጀት ወሰንኩ። ለውድድር ብቻ ሳይሆን ኤክስፖርት የሚሆነም ነው ያዘጋጀሁት። ማስታወቂያ ሲወጣ አቀረብኩ" ብሏል።
ታምሩ ሁለት ዓይነት ቡና ይዞ ቀረበ። ሁለቱም ቡናዎች ተሳካላቸው። አንደኛው ቀዳሚውን ደረጃ ሲይዝ ሁለተኛው ደግሞ አምስተኛ።
"24 ኬሻ ነው ከፍተኛው ማቅረብ የሚቻለው። እኔም አንደኛ ከወጣው ቡና 24 ኬሻ ነው ያቀረብኩት። አንድ ኬሻ በ60 ኪሎ ነው። ስለዚህ አንደኛ የወጣው 1440 ኪሎ ነው። አምሰተኛ የወጣውም ብዛቱ ተመሳሳይ ነው።"
ቡናዎቹ ደረጃቸው ብቻ ሳይሆን ዋጋቸውም ጭምር ነው እጅን በአፍ ላይ የሚያስጭነው።
አንደኛው የወጣው ቡና በኪሎ 330 ዶላር ነው የተሸጠው።
"ለጨረታ የቀረበው 1440 ኪሎው አይደለም። ለናሙናም ብዙ አገር ሲላክ፣ ዝግጅት ሲደረግም የሚወጣ ስላለ 1140 ኪሎ ብቻ ነው ለጨረታ የቀረበው። አንደኛ የወጣው ወደ 364 ሺህ ዶላር ነው የተሸጠ።"
አምስተኛ የወጣው ወደ 67 ሺህ ዶላር ተሽጧል።
"አጠቃላይ ሁለቱም በድምር 431 ሺህ ዶላር ገደማ ነው የተሸጠው። አሁን ባለው የዶላር ምንዛሪ ወደ 19 ሚሊየን ብር ነው በአጠቃላይ የተሸጠው" እንደ ታምሩ ከሆነ።
"ገዢዎቹ በጣም የተለየ ቡና ለመግዛት ነው የሚወዳደሩት"
ለምን ይሆን ቡናዎቹ በዚህ ዋጋ የሚሸጡት?
ይህ የቡና ግብይት መድረክ የተለየ ገበያ መሆኑን የሚገልጹት ወ/ት ቅድስት "ሁሉም ቡና በዚህ ዋጋ አይሸጥም" ይላሉ።
"ስፔሻሊቲም (ባለ ልዩ ጣዕም ቡና) እንደዚህ አይሸጥም። ይህ ውድድር ነው። ገዢዎቹ በጣም የተለየ ቡና ለመግዛት ነው የሚወዳደሩት። በዚያ ላይ ቡናው በአራት ደረጃ በስምንት አገር ተቀምሶ ስለተሸጠ እና በአንድ አምራች ሊሸጥ ሲሞከር አንድ አይደለም።"
"ሌላው ካፕ ኦፈ ኤክሰለንስ ብዙ አባላት አሉት። እነሱ በሚያምኑት ምንም መጭበርበር ሳይኖር የሚቀርበውን ቡና ስለሆነ ነው" ብለዋል።
የታምሩ ቡናስ ምን ቢሆን ነው እንደዚህ ተወዳጅ እና ተመራጭ የሆነው? ዋጋስ ያወጣለት?
"ቡናው ከሌላው ቡና የሚለየው፤ ከሚበቅልበት ቦታ ነው ዋናው ልዩነቱ ። አየሩ፣ ከአፈሩ ቡናው የሚያገፈኘው ሚኒራል አካባቢው ሁሉ ተደምሮ ልዩ ያደርገዋል። ከበቀለበት ቦታ እንጂ የእኛን ልዩ ያደረግነው ነገር የለም። የቡናው ዝርያ ችግኙ 74158 እና 74165 የሚባል ዝርያ እኛ ጋር ብቻ አይደለም ሌላም ቦታ አለ። በጣም ከፍታ ቦታ ላይ የሚበቅል ነው። ቦታው ነው ልዩ የሚያደርገው።"

የፎቶው ባለመብት, Fintrac Inc.
ውድድሩ የአንድ ጊዜ ገንዘብ ማግኛ ብቻ አይደለም። ታምሩም ሁሌም ቡናውን በዚህ ዋጋ ይሸጣልም ማለት አይደለም።
"በውድድሩ መሳተፉ ብዙ ጥቅሞች አሉት። ተቆጥሮም የሚያልቅ አይደለም። አንደኛው እና ትልቁ ለየትኛውም ሰው የሚመከረው ዕውቅናን ይሰጣል። ቡና ላይ ያለ ሰውና ገዢዎችን ለማወቅ ያግዛል። ለአገርም ለግለሰብም ትልቅ ጥቅም ነው የሚያመጣው። [በዘርፉ] ታዋቂ እንድትሆን ያደርጋል። ለዓለም ገበያ ኤክስፖርት እንዲኖርህ ያደርጋል። በገንዘብ ረገድም በጣም ይረዳል።"
"ጥሩ መነቃቃት ነው ለእኛ ካምፓኒ የፈጠረው። በኢትዮጵያ ደረጃም ካየነው 'ካፕ ኦፍ ኤክሰለንስ' ትልቅ ዕድል ነው ይዞ የመጣው። በረከት ይዞ እንደመጣ ቁጠረው። ለአገራችንም መነቃቃቱ ደስ የሚል ነው። ገበሬው ሁሉ ከፍ ያለ ዋጋ ነው የሚያገኘው። እንዲህ ነው ብለህ የምትጨርሰው አይደለም" ብሏል።
ጥቅሙ ታምሩ ከገለጸው ቢበልጥ እንጂ የሚያንስ አይደለም የሚሉት ወ/ት ቅድስት ናቸው።
"ሽልማቱም ለሁሉም ነው"
"ውድደሩ ተጽዕኖ አለው። ካለፈው ዓመት አሸናፊዎች እንዳየነው አካባቢው በመተዋወቁ በሦስት እጥፍ ከመደበኛው ዋጋ በላይ እየሸጡ ነው። አንዱ አምራች ካሸነፈ ሌሎችም በአካባቢው ቡና የሚያመርቱት ይጠቀማሉ።"
"መነቃቃት ተጀምሯል። አምራቾችም ገቢ እያገኙ ነው። በውድድሩ እየቀጠሉ ሲሄዱ እየተሻሻለ ይሄዳል" ብለዋል።
ገንዘቡ ጠቀም ያለ ነውና ብሩን ምን ላይ ታውለዋለህ ሲል ቢቢሲ ታምሩን ጠየቀ።
"ቡና ውስጥ ነው ያለሁት። 100 ፐርሰንት ኤክስፖርት አደረጋለሁ። የቡና ሥራዬን ሰፋ አድርጌ ለመሥራት ነው ዕቅዴ። በዚህ ብቻ ሳይሆን ከባንክም ጨምሬ ሰፋ አድርጌ ለመሥራት ነው የምፈልገው" ታምሩ መለሰ።
መቼም ውጤቱ የታምሩ ብቻ አይደለም። ብዙዎችም ተሳትፈዋል። "ሽልማቱም ለሁሉም ነው" የሚለውም ለዚህ ነው።
"ገበሬዎች አሉ ቡና የሚያቀርቡ እነሱ ላይ የተሻለ ነገር እንዲኖራቸው እንደሽልማትም ለመስጠት አስበናል። እነሱንም ማበረታታት ነው። ቀጣይነት እንዲኖረው ከግብርና ባለሙያዎች ጋር በመተባበር ችግኝ በማቅረብ ምርታማነት በመጨመር ህይወታቸውን የሚያሻሻል ነገር ለመሥራት አስበናል በብሩ።"
ታምሩ የአሁኑ ውድድር ለመጀመሪያ ጊዜ ተሳተፈበት ነው። ለዚህም ነው "በቀጣይ እወዳደራለሁ ያው ብዙ ቡና ላልሰጥ እችላለሁ ግን እወዳደራለሁ በየዓመቱ ቡና እያዘጋጀሁ" የሚለው።

የፎቶው ባለመብት, Fintrac Inc.
"የቡና ሱሰኛ አይደለሁም"
ለመሆኑ ዘንድሮ ምርጥ ቡና ከኢትዮጵጵያ ማቅረብ የቻለው ታምሩ ቡና ይጠጣል?
ቡና ይጠጣል። ግን ካገኘ ነው። "አልጠጣም" ብሎ ፈልጎ ግን አይደለም።
በአጭሩ ሱሰኛ አይደለም።
ካገኘ ግን "አራትም አምስትም ሲኒ" በቀን ሊጠጣ ይችላል። ካጣ ደግሞ አንድም ላይጠጣ ይችላል።
የጀበና ቡና ብዙም አይመስጠውም።
ምክንያቱም ታምሩ ቡና መቅመስ ተምሯል። "በጣም ልምድ ባይኖረኝም እቀምሳለሁ" ሲል ራሱን ይገልጻል።
ቡና መቅመስ መቻሉ ደግሞ "ቡና ለመለየትም ለማድነቅም ጥሩ ነው" ይላል።
"የጀበና ቡና ብዙ ጊዜ ስለሚያር ብዙም አይደለም። በትክከል የሚፈላውን እጠጣለሁ እሱን እመርጣለሁ" ብሏል።
ለዚህ አማራጩ ራሱ ማፍላት ነው።
"ጥሩ ጥሩ ቡና ቢሮዬ አፍልቼ እጠጣለሁ። ሱሰኛ ግን አይደለሁም" ብሏል።
እንደ መውጫ
ብዙዎቹ የካፕ ኦፍ ኤክሰለንስ ተጫራቾች እና ገዢዎች ቡናን ከመቁላት ጀምሮ በተለያዩ ደረጃ እሴት ጨምረው የሚሸጡ ናቸው።
ሲሸጡም 'ካፕ ኦፍ ኤክሰለንስ' ብለው በከፍተኛ ዋጋ ነው የሚሸጡት።
ሌሎች ደግሞ በጣም ትልልቅ የሆኑ ካፌዎች ውስጥ ይሸጣሉ።
"ያለፈውን ዓመት አንደኛ [የሆነውን ቡና የገዛው] ለንደን ውስጥ በ65 ዶላር ነው አንድ ሲኒ የሸጠው። እሱም በማስታወቂያ ከዚህ እስከዚህ ቀን ተብሎ በግል ባሬስታ ነው የቀረበው" ብለዋል ወ/ት ቅድስት።
"እነዚህ እንግዲህ ሃይ ኢንድ [ከፍተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙ] ካፌዎች ናቸው። በጣም ውድ ውድድር ነው። ለብዙ ሰዎች የሚደርስ ሳይሆን የቅንጦት ነው" ሲሉ ገልጸዋል።
ለዚህም ነው ታምሩ በቡና ዘርፍ ከተሰማራችሁ ተሳተፉ የሚለው።
"እየተወዳደርኩ እሄዳለሁ። መወዳደሩ ጥሩ ነው ለእኔ ብቻ ሳይሆን ለሁሉም ሰው። ሁሉም ቡና ላይ የተሠማራ ሰው መወዳደር አለበት ብዬ ነው የምመክረው" ብሏል።
ውድድሩ ለማንም ክፍት ነው፤ ቡና ላይ ለተሠማራ አምራችም ሆነ ወደ ውጪ ላኪ።
መስፈርት ግን አለ። "ቡናው ትሬሰብል (ከየት ተነስቶ የት እንደደረሰ የሚያሳይ ማስረጃ የሚቀርብበት) መሆን አለበት። በትክክል ቡናው የተመረተበትን ቦታ መረጃ እንፈልጋለለን፤ የይዞታ ማረጋገጫ እንፈልጋለን። ይህን ማሟላት የሚችል መሳተፍ ይችላል" ብለዋል ወ/ት ቅድስት።
ስለዚህ ለሚቀጥለው ዓመት ተዘጋጁ ተብላችኋል።















