የስዊዘርላንድ መንግሥት ቡና ለህይወት አስፈላጊ እንዳልሆነ ገለፀ

የተቆላ ቡና

የስዊዘርላንድ መንግሥት ችግሮች በሚያጋጥሙ ጊዜ ያስፈልገኛል በማለት የሚያከማቸውን ቡና ሊያቆም ነው፤ ምክንያቱ ደግሞ ቡና ለሰው ልጅ ህልውና የግድ አስፈላጊ አይደለም በሚል ነው።

ስዊዘርላንድ በመጀመሪያውና ሁለተኛው የአለም ጦርነት የቡና ምርት ይቋረጥብኛል በሚል ስጋት መጠባበቂያ ቡና ታከማች ነበር።

ከዚያም በኋላ ለበርካታ አመታት ተፈጥሯዊም ሆነ ሰው ሰራሽ ችግሮች ሲፈጠሩ "የምጠቀምበት" በማለት ቡናን ማከማቸቷን ቀጥላበት ነበር።

ይህ አይነቱ ሃገራዊ አሰራር ግን ከጎርጎሳውያኑ 2022 በኋላ እንደማይቀጥል መንግሥት አስታውቋል። መንግሥት ይህንን ቢልም በርግጥ መሆን የለበትም በማለት ተቃዋሚዎች ድምጻቸውን እያሰሙ ነው።

በአሁኑ ወቅት ስዊዘርላንድ 15 ሺ 300 ቶን የቡና ክምችት አላት። ይህም ለሶስት ወራት በቂ ነው።

ለምን ማቆም አስፈለገ?

መንግሥት እንዳስታወቀው ቡና ለህይወት አስፈላጊ ባለመሆኑ ለአደጋ ጊዜ መጠባበቂያ ከሚያስፈልጋቸው የምርት ዝርዝሮች ውስጥ መውጣት እንዳለበት አስረድቷል።

"ቡና ምንም በሚባል ደረጃ ኃይል የሚሰጥ ንጥረ ነገር ያለው ባለመሆኑ ለሥነ ምግብ አስተዋጽኦ የለውም።" ብሏል የፌደራል ጽ/ቤት የምጣኔ ሃብት አቅርቦት።

ውሳኔው ሊጸና ይችል ይሆን?

እቅዱ የህዝብ አስተያየት እንዲሰጥበት ይፋ የተደረገ ሲሆን የመጨረሻው ውሳኔም በሚቀጥለው ህዳር ይሰጣል። ነገር ግን በጉዳዩ ላይ አብዛኛው ስዊዘርላንዳውያን ደስተኛ የሆኑ አይመስሉም።

የቡና መጠባበቂያውን ከሚያዘጋጁ 15 ኩባንያዎች መካከል 12 የሚሆኑት መጠባበቂያ የማከማቸት ሂደቱ መቀጠል አለበት ብለዋል።

ሮይተርስ የዜና አገልግሎት ይዞት የወጣው ደብዳቤ ደግሞ እንደሚያሳየው የካሎሪ መጠንን ለቡና መስፈርትነት መጠቀም ፍትሃዊ አይደለም፤ ሊሆንም አይገባም ይላል።

ለመሆኑ ስዊዘርላንዳዊያን ምን ያክል ቡና ይጠጣሉ?

በአለም አቀፉ የቡና ድርጅት መረጃ መሰረት ስዊዘርላንዳዉያን የቡና አፍቃሪዎች ናቸው።

በአመትም በነፍስ ወከፍ 9 ኪሎ ግራም ቡና ይጠጣሉ። ይህም በነፍስ ወከፍ 3.3 ኪሎ ግራም ቡና በአመት ከሚጠጡት እንግሊዛውያን ጋር ሲነጻጸር ሶስት እጥፍ እንደማለት ነው።