ታሪካዊው የወባ ክትባት ጅማሮ በአፍሪካ

የፎቶው ባለመብት, BRIAN ONGORO
በመላው አፍሪካ ያሉ ልጆችን ገዳይ ከሆነው በሽታ ለመከላከል ታሪካዊ በተባለው ሁኔታ የወባ በሽታ ክትባት ሊወስዱ ነው።
በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ለብዙ ሺህ ዓመታት ከቆዩ ዋነኛ መቅሰፍቶች አንዱ ነው የተባለው የወባ በሽታ በርካታ ህፃናትንና ጨቅላዎችን ቀጥፏል።
ለመቶ ዓመታት ያህል ሙከራ ከተደረገበት በኋላ በህክምና ታሪክ ታላቅ ስኬት በሚባል ሁኔታ ክትባቱ ተገኝቷል።
አርቲኤስ፣ ኤስ የሚል መጠሪያ የተሰጠው ይህ ክትባቱ ፍቱንነቱ የተረጋገጠው ከስድስት ዓመታት በፊት ነው።
በጋና፣ በኬንያ እና በማላዊ የሙከራ ክትባት መርሃ ግብሮች ተደርጎ ስኬታማነቱ መረጋገጡን ተከትሎ የዓለም ጤና ድርጅት ክትባቱ ከመካከለኛ እስከ ከፍተኛ የወባ ስርጭት ባለባቸው ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ አገራት እና በሌሎች ክልሎች መጀመር አለበት ብሏል።
"ስራዬን የጀመርኩት በወባ ተመራማሪነት ነው። በዚህ ጥንታዊ እና አስከፊ በሽታ ላይ ውጤታማ ክትባት የምናገኝበትን ቀን ለማየት እጓጓ ነበር። ይህች ቀን ያ ነች" በማለት የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም ገብረእየሱስ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።
አክለውም "ታሪካዊ ወቅት" ነው ብለዋል።
ለረጅም ዘመናት ሲጠበቅ የነበረው የወባ ክትባት የተዘጋጀው በአህጉሪቷ፣ በአፍሪካውያን ሳይንቲስቶች ጋር መሆኑንም ጠቅሰው "ለረጅም ጊዜ ሲጠበቅ የነበረው የህጻናት የወባ ክትባት ለሳይንስ፣ ለልጆች ጤና እና ለወባ ቁጥጥር ታላቅ ግኝት ነው" በማለት "በየዓመቱ በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ
ወባን ለመከላከል ከዚህ ቀደም የሰው ልጅ ይጠቀምባቸው ከነበሩ እንደ አጎበርና ሌሎች መከላከያዎች በተጨማሪ ይህንን ክትባት መጠቀም በየዓመቱ በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ወጣቶችን ሕይወት ሊታደግ ይችላል ብለዋል።
ይህ ክትባት ለዓለም ስጦታ ቢሆንም የበሽታው ከፍተኛ ሸክም አፍሪካ ውስጥ ከመሆኑም ጋር ተያይዞ ያለው ቦታ ከፍተኛ ነው ብለዋል።
ገዳዩ በሽታ
ደም በሚጠጡ ትንኞች ንክሻ የሚተላለፈው የወባ በሽታ የደም ሴሎችን በመውረር ከጥቅም ውጪ ያደርጋቸዋል።
የወባ ጥገኛ ተህዋስያንን ለመግደል መድኃኒቶችን፣ ንክሻዎችን ለመከላከል እና ትንኞችን ለመግደል ፀረ ተባይ መድኃኒቶች ለዘመናት ያገለገሉ ሲሆን ሁሉም የወባ በሽታን ለመቀነስ ረድተዋል።
ነገር ግን አሁንም በዓመት ወደ 230 ሚሊዮን የሚጠጉ የወባ ታማሚዎች የሚገኙ ሲሆን ከነዚህም ውስጥ 400 ሺህ ሰዎች ይሞታሉ ።
ከዚህ አሃዝ ውስጥ 95 በመቶ የሚሆነው የወባ በሽታ በአፍሪካ ውስጥ የሚከሰት ሲሆን ከሁለት ዓመት በፊትም ከ260 ሺህ በላይ ሕፃናት ሞተዋል።
ሰውነት የበሽታውን የመከላከል አቅም እንዲያዳብር በተደጋጋሚ ለዓመታት በበሽታው መያዝ የሚያስፈልግ ሲሆን ይህም በጠና በወባ የመታመም አጋጣሚን ይቀንሳል።
ዶክተር ክዋሜ አምፖንሳ-አቺያኖ የጅምላ ክትባት ተግባራዊ እና ውጤታማ መሆን አለመሆኑን ለመገምገም ጋና ውስጥ ክትባቱን ሞክረዋል።
"ለእኛ በጣም አስደሳች ጊዜ ነው፣ በሰፊው ክትባት በማካሄድ የወባ በሽታ መጠኑ በትንሹ እንደሚቀንስ አምናለሁ" ብለዋል።

የፎቶው ባለመብት, CRISTINA ALDEHUELA
በልጅነታቸው በተደጋጋሚ በወባ በሽታ መጠቃታቸው በጋና ሐኪም ለመሆን ዶክተር አምፖንሳ-አቺያኖን አነሳስቷቸዋል።
"እሱ ሁኔታ አሳዛኝ ነበር፣ በየሳምንቱ ማለት ይቻላል እየታመምኩ ከትምህርት ቤት እቀር ነበር፣ ወባ ለረጅም ጊዜ በእኛ ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሶብናል" ይላሉ።
የልጆችን ሕይወት መታደግ
ከ100 በላይ የወባ ተውሳኮች (ፓራሳይት) አሉ። አዲሱ የአርቲኤስ፣ ኤስ ክትባት በአፍሪካ ውስጥ በጣም ገዳይ የሆነውንና የተለመደው ፕላስሞዲየም ፋልሲፖረም የሚል ስያሜ ያለው ላይ ያነጣጠረ ነው።
በአውሮፓውያኑ 2015 የተደረገው የክትባት ሙከራ ሪፖርት እንደሚያሳየው ከአስር በሽተኞች አራቱን እንዲሁም 10 በጠና ከታመሙ ሦስቱን መከላከል ያስችላል።
ከዚህም በተጨማሪ የደም ልገሳ የሚያስፈልጋቸው ህፃናት ቁጥርንም በሲሶ እንደሚቀንስ ተነግሯል።
ሆኖም ክትባቱ ውጤታማ እንዲሆን አራት መጠን (ዶዝ) መውሰድ የሚያስፈልግ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ፍቱንነቱ ላይ ጥርጣሬዎች ተፈጥረው ነበር።
የመጀመሪያዎቹ ሦስቱ ክትባቶች በአምስት፣ በስድስት እና በሰባት ወር ልዩነት የሚሰጥ ሲሆን የመጨረሻው ማጠናከሪያው ደግሞ በ18ኛ ወራት አካባቢ ይሰጣል ተብሏል።

የፎቶው ባለመብት, PATH
የሙከራ ክትባቱ ግኝቶች በሁለት የዓለም ጤና ድርጅት ልሂቃን አማካሪ ቡድኖች አማካኝነት ማብራሪያ ተሰጥቷል።
ከ2.3 ሚሊዮን በላይ ክትባቶች ተሞክረው ያሳዩት ውጤትም ሲገመገም
• ክትባቱ ደኅንነቱ የተጠበቀ እና አሁንም የጠና የወባ በሽታ በ30 በመቶ እንዲቀንስ አድርጓል
• ለመተኛት የወባ አጎበር የሌላቸው ልጆች ከሁለት ሦስተኛ በላይ ለሚሆኑት ክትባቱ ተዳርሷል
• በሌሎች መደበኛ ክትባቶች ወይም ወባን ለመከላከል በሚወሰዱ ሌሎች እርምጃዎች ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ አልፈጠረም
• ክትባቱ ወጪ ቆጣቢ ነበር
"ከሳይንሳዊ እይታ አንፃር ይህ ትልቅ ግኝት ነው፣ ከሕዝብ ጤና አንፃር ይህ ታሪካዊ ስኬት ነው" በማለት የዓለም ጤና ድርጅት የወባ ፕሮግራም ዳይሬክተር ዶክተር ፔድሮ አሎንሶ ተናግረዋል።
አክለውም "የሰው ልጅ ከ100 ዓመታት በላይ የወባ ክትባት ሲፈልግ ቆይቷል። እናም በአሁኑ ወቅት መገኘቱ ህይወትን ያድናል እና በአፍሪካ የሕፃናት በሽታን ይከላከላል" ብለዋል።












