የአውስትራሊያ ሴት እግር ኳስ ተጫዋቾች በስፖርቱ ውስጥ ጾታዊ ጥቃት መኖሩን ተናገሩ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የቀድሞዋ የአውስትራሊያ ሴት የእግር ኳስ ተጫዋች ሊሳ ዴ ቫና በስፖርቱ ውስጥ ስላለው የጾታዊ ጥቃት ባህል ለአንድ ጋዜጣ የሰጠችው ቃለ ምልልስ አነጋጋሪ ሆኗል።
የ36 ዓመቷ የቀድሞ የማቲልዳስ የእግር ኳስ ቡድን አጥቂ በይፋ መናገሯን ተከትሎም ሌሎች የሃገሪቱ ሴት ተጫዋቾች ተመሳሳይ ሃሳቦችን ማንጸባረቅ ጀምረዋል።
የአውስትራሊያ የእግር ኳስ ባለስልጣን እንዲህ ያሉ ቅሬታዎች ቀርበውለት እንደማያውቁ በመግለጽ እነዚህን ክሶች ተከትሎ ግን ሊሳን ጨምሮ ሌሎች ተጫዋቾች የሚያሰሙትን አቤቱታ ተቀብሎ ገለልተኛ አጣሪ ቡድን ለመመስረት ዝግጁ መሆኑን አስታውቋል።
"በእግር ኳስ ጨዋታ ከሚሳተፉ ሰዎች የሚጠበቁ ስነምግባሮችን ለሚጥስ ማንኛውም ዓይነት ተግባርም ሆነ ጾታዊ ጥቃት ምንም አይነት ትዕግስት የለንም" ሲል ባለስልጣኑ ተናግሯል።
ሊሳ ባለፈው ወር ጫማዋን እስከምትሰቅል ድረስ ለሃገሯ 150 ጊዜ ተሰልፋ ተጫውታለች።
ለማቲልዳስ በምትጫወትበት ወቅት በአንድ የቡድን አጋሯ ወሲባዊ ጥቃት እንደተፈጸመባት በአውስትራሊያ ለሚታተመው ሲድኒ ቴሌግራፍ ተናግራለች።
"ወሲባዊ ጥቃት ደርሶብኝ ነበር ወይ? አዎ። የማሸማቀቅ ድርጊቶች ተፈጽመውብኝ ነበር ወይ? አዎ። ተገልያለሁ? አዎ። ምቾት የሚነሱ ነገሮችን ተመልክቼ ነበር ወይ? አዎ" ስትል ተናግራለች።
በየትኛውም ስፖርታዊ ጨዋታዎች ውስጥ ያሉ ስነምግባር የጎደላቸው ተግባራት በሙሉ እንደሚረብሿትም አክላለች።
ሊሳን የሚደግፉ ምስክርነቶች በቀድሞ የቡድን አጋሯ ኤሊሲያ ካርናቫስ እና በቀድሞ ማናጀሯ ሮዝ ጋሮፋኖ መሰጠታቸውን ጋዜጣው ዘግቧል።
ራሄል ዶብሶን የተሰኘች የቀድሞ የቡድን አጋሯም መጀመሪያ ቡድኑን ስትቀላቀል ጥቃት ለመፈጸም የታሰቡ ግንኙነቶች ውስጥ ማለፏን ተናግራለች።
"ይህ አሁንም በከፍተኛዎቹ ሰዎች ደረጃም የቀጠለ ነገር ነው። ይህንን ለመግታት አንዳች ነገር ካልተደረገ ምንም የሚቀየር ነገር የለም" ስትል ለጋዜጣው ተናግራለች።
የአሜሪካ ሴት የእግር ኳስ ተጫዋቾች ተመሳሳይ መልዕክቶችን ካስተላለፉ በኋላ ነው የአውስትራሊያ ተጫዋቾችም ጥቃቶቹን ማጋለጥ የጀመሩት።
ይህ በጂምናስቲክ ብሎም በዋና ስፖርት ውስጥ ያሉ ሴት ስፖርተኞችም በተለያየ ወቅት ይፋ እያወጡት ያለ ክስተት ሆኗል።












