የአዲሱ ካቢኔ አምስቱ ቁልፍ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች

የምክር ቤት አባላት

የፎቶው ባለመብት, HOPR

ስድስተኛውን ዙር ብሔራዊ ምርጫን ተከትሎ ብልጽግና ፓርቲ አብዛኛውን የፌደራል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን መቀመጫዎች ካሸነፈ በኋላ ሰኞ መስከረም 24/2014 ዓ.ም አዲስ መንግሥት መስርቷል።

በምክር ቤቱ የመጀመሪያ ቀን ስበሰባ የብልጽግና ፓርቲ ሊቀመንበርና ባለፉት ሦስት ዓመታት አገሪቱን በጠቅላይ ሚኒስትርነት የመሩት ዐቢይ አሕመድ፣ ለቀጣይ አምስት ዓመት በመሪነት መንበር ላይ እንዲቆዩ መርጧቸዋል።

የአስተዳደራቸውን ሥራ አስፈጻሚ ከፍተኛ ባለሥልጣንትን ይፋ ማድረግ ደግሞ ቀጣዩ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሥራ ነው።

በዚህም በእሳቸው በሚመራውን የሚኒስትሮች ምክር ቤት ውስጥ አባል የሚሆኑና በቁልፍ የሚኒስትርነት ቦታዎች ላይ የሚሰየሙ ግለሰቦችን በመምረጥ ለምክር ቤቱ አቅርበው እንዲሾሙ አድርገዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩና ፓርቲያቸው ቀደም ሲል እንደገለጹት በተለያዩ የመንግሥት ኃላፊነት ቦታዎች ከብልጽግና ፓርቲ ባሻገር ከተፎካካሪ ፓርቲ አባላት መካከል እንዲካተቱ አድርገዋል።

እስካሁን በነበሩት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ላይ የአወቃቀርና የስያሜ ለውጥ የተደረገባቸው ያሉ ሲሆን ነባርና አዳዲስ ሚኒስትሮች ተካተዋል።

አዲሱ መንግሥት መዋቅር ውስጥ የሚኖሩት ሁሉም የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች በሚመደቡባቸው መስኮች የየራሳቸው ቁልፍ ሚና ቢኖራቸውም አንዳንዶቹ ግን የሚኖራቸው ኃላፊነትና ተጽዕኗቸው የጎላ ነው።

አገሪቱ ካለችበት ወቅታዊ ሁኔታ አንጻር ይኖራቸዋል ከሚባለው ከፍተኛ የሥራ ኃላፊነት አኳያ አምስት የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶችን ቃኝተናል።

መስመር

የገንዘብ ሚኒስቴር፡ ከጥቅምት 24/2013 ዓ.ም ጀምሮ ከህወሓት አማጺያን ጋር አገሪቱ የገባችበትን ጦርነት ተከትሎ የአገሪቱ ምጣኔ ሀብት ክፉኛ እየተፈተነ ይገኛል። ይህ ጦርነት በርካታ የምጣኔ ሀብት አውታሮች እና መሰረተ ልማቶች ላይ ውድመትን አድርሷል። ይህንን ጦርነት ተከትሎ ዋነኛ የአገሪቱ ድጋፍ ሰጪ ምዕራባውያን እጃቸውን የመሰብሰብ አዝማሚያ እያሳዩ ነው።

በተጨማሪም በአገሪቱ ያለው የውጭ ምንዛሪ ዋጋ በተከታታይ እየጨመረ በመሄዱ ከዚህ በፊት ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ በጥቁር ገበያውና በመደበኛው የምንዛሪ ገበያ ያለው የምንዛሪ ተመን ልዩነቱ እጅጉን የሰፋ ሆኗል።

ከዚህ በተጨማሪም በአገሪቱ ያለው የኑሮ ውድነት ባለፉት ወራት በመናሩ የሸቀጦችና አገልግሎቶች ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል።

የምዕራባውያን አገራትና የዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት ለአገሪቱ በሚያቀርቡት ድጋፍ ላይ ለውጥ የሚኖር ከሆነ አሁን ባለው የዶላር እጥረት፣ የመሠረታዊ ፍጆታ እቃዎች ዋጋ መናር ጋር ተያይዞ የአገሪቱን ምጣኔ ሀብት ሊፈትነው ይችላል ተብሎ ያሰጋል።

ሰላም ሚኒስቴር፡ በአገሪቱ ሠሜናዊ ክፍል ያለው ጦርነት፣ በምዕራብ እና ደቡብ ያለው አለመረጋጋት የአገሪቱን ሰላም እና ደኅንነትን አደጋ ውስጥ ከከተቱት ጉዳዮች መካከል ናቸው።

ለውጥ ይደረግባቸዋል ከሚባሉት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች አንዱ የሆነው ይህ ተቋም ያጋጠሙ የሰላም መደፍረሶችን ለመፍታት እና ዘላቂ መፍትሔ ለመስጠት መሥራት እንዳለበት፣ ይህም የአዲሱ መንግሥት ቁልፍ አጀንዳ ሊሆን እንደሚገባ ባለሙያዎች ይናገራሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በመስቀል አደባባይ በተካሄደው የአዲስ መንግሥት ምስረታና በዓለ ሲመት ላይ ባደረጉት ንግግር፤ በአገሪቱ የፖለቲካ ኃይሎች መካከል መግባባትን ለመፍጠር ሁሉን አካታች ውይይት እንደሚካሄድ ተናግረዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፡ ትግራይ ውስጥ ከተከሰተው ግጭትና ከታላቁ የሕዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘ አገሪቱ ከፍተኛ የውጭ ግንኙነትና የዲፕሎማሲ ሥራ ይጠብቃታል።

በትግራይ ያለውን ጦርነት ተከትሎ ምዕራባውያንና ዓለም አቀፍ ተቋማት የተለያዩ ዲፕሎማሲያዊ ግፊቶችን እያደረጉ ይገኛሉ።

በትግራይ ያለውን ጦርነት ተከትሎ ምዕራባውያንና ዓለም አቀፍ ተቋማት የተለያዩ ዲፕሎማሲያዊ ግፊቶችን እያደረጉ ይገኛሉ።

የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት ትግራይ ባለው የሰብአዊ ቀውስ እንዲሁም በሕዳሴው ግድብ ዙሪያ ኢትዮጵያን ርዕስ በማድረግ ውይይት አድርጓል።

በቅርቡ በአገሪቱ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ገብተዋል በሚል ከኢትዮጵያ ለቀው እንዲወጡ የተደረጉት የተባበሩት መንግሥታት ኃላፊዎች ጉዳይ ከመንግሥታቱ ድርጅት፣ ከምዕራባውያን በኩል ተቃውሞን አስከትሏል።

ይህም ኢትዮጵያ ከተባበሩት መንግሥታት ጋር ባላት ግንኙነት ላይ አሉታዊ ውጤት ሊኖረው የሚችል ሲሆን በዚህ በኩልም አገሪቱ ዋነኛ ሥራ ይጠብቃታል።

በዚህ መካከል ኢትዮጵያ በመላው ዓለም ካሏት ከ60 በላይ ቆንስላዎች እና ኤምባሲዎች ገሚሱን ለመቀነስ ያላትን እቅድ ይፋ አድርጋ ወደ እርምጃ ገብታለች።

ዐቃቤ ሕግ፡ በኢትዮጵያ በተደጋጋሚ በሚነሱ ብሔር ተኮር ግጭቶች፣ ፖለቲካዊ ተቃውሞዎች የተነሳ በቁጥጥር ስር የሚውሉ ግለሰቦች በፍትህ ሥርዓቱ ላይ ሲያማርሩ ይሰማል።

በተደጋጋሚ በኢትዮጵያ ያለው የፍትህ አካል ገለልተኛ፣ ታማኝ እና ብቁ አይደለም የሚል የሰላ ትችት ሲቀርብ ይደመጣል።

ከዚህ በተጨማሪም የተፋጠነ ፍትህ የሚሹ በርካታ ዜጎች ፍትህ እየተጠባበቁ ይገኛሉ።

ከዚህ አንጻር የስያሜ ለውጥ ሊደረግበት ይችላል የተባለው የአገሪቱ ዋነኛ የፍትህ ተቋም ዐቃቤ ሕግ በርካታ ሥራዎች ይጠበቁበታል።

ገቢዎች ሚኒስቴር፡ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በዓለም በመንሰራፋቱ ምክንያት የተከሰተው የንግድ እንቅስቃሴ በኢትዮጵያ ገቢ ላይ ቀላል የማይባል ተጽእኖን አሳድሯል።

የአወቃቀር ለውጥ እንደሚደረግባቸው ከተነገረካቸው ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች መካከል አንዱ የሆነው የገቢዎች ሚኒስቴር በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ጉልህ ሚና ካላቸው ተቋማት መካከል አንዱ ነው።

አገሪቱ ለተለያዩ ሥራዎቿ የምታውለውን መዋዕለ ነዋይ ከልዩ ልዩ ምንጮች የሚያሰባስበው ይህ ተቋም በተለያዩ ምክንያቶች ጫና ውስጥ ለወደቀው የአገሪቱ ምጣኔ ሀብት ወሳኝ ሚና ይኖረዋል።

የአገሪቱን የታክስና የገቢ መሠረት የማስፋቱ ሥራን የሚያከናውነው ይህተ ተቋም በምጣኔ ሀብቱ ላይ ሊደርስ የሚችለውን ጫና ለመቋቋም የሚያስችሉ ተግባራትን የማከናወን ኃላፊነት ተጥሎበታል።

መስመር

በተለያዩ ወቅቶች በአገሪቱ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ብዛት፣ መዋቅርና ስያሜዎች ላይ በየጊዜው ለውጦች ሲካሄዱ የነበረ ሲሆን፤ ይፋ ይደረጋል ተብሎ በሚጠበቀው የካቢኔ ሚኒስቴሮች ዝርዝር ላይም ይኸው ለውጥ እንደሚኖር በስፋት እየተነገረ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከላይ የተጠቀሱትንና ሌሎችንም የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች የሚመሩ ዕጩዎችን በማቅረብ እንዲሾሙላቸው ይጠይቃሉ።