የአፍሪካ አገራት መሪዎች በመንግሥት ምስረታ በዓለ ሲመት ላይ ምን አሉ?

ዛሬ መስከረም 24/2014 ዓ.ም እየተካሄደ ባለው የኢትዮጵያ አዲስ መንግሥት መስረታ በዓለ ሲመት ላይ የተገኙ የአፍሪካ አገራት መሪዎች ንግግር አድርገው ለኢትዮጵያና ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።
በመስቀል አደባባይ እየተካሄደ ባለው የጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ በዓለ ሲመት ሥነ ሥርዓት ላይ የተጋበዙት የኡጋንዳው ፕሬዘዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ፤ በኡጋንዳ ሕዝብ ስም የኢትዮጵያን ሕዝብ እና ጠቅላይ ሚንስትሩን "እንኳን ደስ አላችሁ" ብለዋል።
በኡጋንዳ የጎሳ እና የሃይማኖት ክፍፍል ከፍተኛ ችግር እንደፈጠረ ገልጸው፤ የማንነት ፖለቲካ የሚፈጥረውን ልዩነት መቅረፍ ወደ ለውጥ ጎዳና እንደሚያሻግር ተናግረዋል።
የደቡብ ሱዳኑ ሳልቫ ኪር በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያን ሕዝብ ሰላም ለማለት እና እንኳን ደስ አላችሁ ለማለት ነው የመጣሁት።
"ያለ እናንተ ድምጽ ወንድሜ ዐብይ ወደ ሥልጣን አይመጣም ነበር። ከጎኑ ቆማችሁ ወደ ሰላም ተሻገሩ" ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
ኢትዮጵያን "ታላቋ እናታችን" ሲሉ አንቆለጳጵሰዋል። በደቡብ ሱዳን የተፈጠረው ቀውስ በኢትዮጵያ እንዲደገም እንደማይሹ እና ግጭቱ በሰላማዊ ውይይት እንዲፈታ ጠይቀዋል።
በደቡብ ሱዳን እና ሱዳን መካከል ሰላም እንዲወርድ ኢትዮጵያ ያደረገችውን ጥረት ከታሪክ አጣቅሰዋል።
በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ፣ በኮ/ል መንግሥቱ ኃይለማርያም፣ በአቶ መለስ ዜናዊ ዘመነ መንግሥትም ኢትዮጵያ በደቡብ ሱዳን ላይ ፊቷን እንዳላዞረችም ሳልቫ ኪር ሳይጠቅሱ አላለፉም።
የጂቡቲው ፕሬዘዳንት እስማኤል ጊሌ በበዓለ ሲመቱ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ የኢትዮጵያን ዴሞክራሲያዊ ሽግግር ማየት አስደስቶኛል ብለዋል።
ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይን "ከጂቡቲ ሕዝብ የተላከ የሚያበረታታ እና ተስፋ ሰጪ መልዕክት ይዤ ነው የመጣሁት" ብለዋቸዋል።
ኢትዮጵያን የፓን አፍሪካኒዝም ተምሳሌት ብለው ካሞገሱ በኋላ፤ በምጣኔ ሀብት ረገድ በቀጠናው ያላትን ሚና ጠቅሰው "ኢትዮጵያ ከራሷ ጋር ሰላም እንድታወርድ፣ የቀድሞ ትልቅነቷን ዳግም እንድታድስ" ጠይቀዋል።
ጦርነት በቀጠናው ያስከተለውን አስከፊ ገጽታ ከታሪክ አጣቅሰው፤ ኢትዮጵያም "ከልጆቿ ጋር እንድትታረቅ" እና ወደ ሰላም እንድትመለስ አሳስበዋል።
እንኳን ለአዲሱ ዓመት አደረሳችሁ፣ እንኳን ለኢሬቻ አደረሳችሁ፣ ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር ሲሉም በአማርኛ ንግግራቸውን አጠናቀዋል።
የኬንያው ፕሬዘዳንት ኡሁሩ ኬንያታ በመስቀል አደባባይ ባደረጉት ንግግር፤ "ወንድሜ ጠቅላይ ሚንስትር ሆነህ ስለተመረጥክ እንኳን ደስ አለህ" ብለዋል።
ኬንያ የኢትዮጵያን እድገት እና ሰላም ለመደገፍ ዝግጁ ናት ሲሉም ድጋፋቸውን ገልጸዋል።
"ወንድሜ ዛሬ የኢትዮጵያ ሕዝብ እንድትመራ፣ ሰላም እንድታመጣ፣ መረጋጋትን እንድታረጋግጥ፣ የኢትዮጵያን ሕዝብ አንድ እንድታደርግ ሥልጣን ሰጥተውሀል። የመረጡህም ያልመረጡህም ያንተ ሕዝቦች ናቸው" ሲሉ ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።
የአፍሪካ ሕዝቦች ከቅኝ ግዛት ነጻ እንዲሆኑ የረዳችው ኢትዮጵያ "እናታችን ናት" ካሉ በኋላ "እናት ሰላም ካጣች ቤተሰቧም ይታወካል" ሲሉ ኢትዮጵያ ወደ ሰላም እንድትመጣ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የናይጄሪያው ፕሬዝደንት ሙሐመዱ ቡሀሪ፤ በበዓለ ሲመቱ ላይ በመገኘቴ ኩራት ይሰማኛል ብለዋል።
በሰኔ ወር የተካሄደው ምርጫ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ "በጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ እንደሚያምን አሳይቶኛል" ሲሉም ተናግረዋል።
አይይዘውም በኢትዮጵያ ሰላም እንዲሰፍን ጠቅላይ ሚንስትሩ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።
ናይጄሪያ የኢትዮጵያን አንድነት እና ሉዓላዊነት መከበር እንደምትደግፍም ቡሀሪ ገልጸዋል።
የሶማሊያ ፕሬዝዳንት መሐመድ አብዱላሂ ፈርማጆ በበዓለ ሲመቱ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ ኢትዮጵያውያን ፍላጎታቸውን የሚያስጠብቅ አስተዳደር በመምረጣችሁ እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል።
የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ጨምሮ ሌሎችም ፈተናዎችን ለማለፍ አስተዳደሩ ኃላፊነቱን እንዲወጣ አሳስባል።
አያይዘውም የኢትዮጵያ ሕዝብ ሁሉን አቀፍ እድገት እንዲጎናጸፍ ጠቅላይ ሚንስትሩ ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡ እምነቴ ነው ብለዋል።












