የተመሠረተው አዲሱ መንግሥት ከከዚህ ቀደሞቹ በምን ይለያል?

የፎቶው ባለመብት, Addis Ababa City Press Secretary
ዛሬ ሰኞ መስከረም 24/2014 ዓ.ም አዲሱ የኢትዮጵያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሥራውን በመጀመር ለቀጣይ አምስት ዓመታት አገሪቱን በጠቅላይ ሚኒስትርነት የሚመራውን ግለሰብ ይሰይማል።
ይህንንም ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራው የሥራ አስፈጻሚ መዋቅርና በካቢኔው ውስጥ ሆነው በሚኒስትርነት የሚያገለግሉ ዕጩዎችን በምክር ቤቱ አስሹሞ በይፋ ሥራውን ይጀምራል ተብሎ ይጠበቃል።
ባለፈው ዓመት ሰኔ 14 በተካሄደው ምርጫ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሊቀመንበርነት የሚመራው የብልጽግና ፓርቲ ምርጫው በተካሄደባቸው አከባቢዎች ከፍተኛ የበላይነትን በፌደራልና በክልል ምክር ቤቶች ውስጥ ለማግኘት ችሏል።
ይህም ለጠቅላይ ሚኒስትሩና ለፓርቲያቸው ተጨማሪ አምስት የሥልጣን ዘመናትን የሚጨምር ሲሆን፤ ዛሬ ሥራውን በሚጀምረው ምክር ቤት ውስጥም ይኸው ይንጸባረቃል ተብሎ ይጠበቃል።
በሁለት ዙር ተከፍሎ በተካሄደው ምርጫ ውስጥ ሰኔ 14/2013 ዓ.ም የተደረገው የመጀመሪያው ዙር በአብዛኞቹ የአገሪቱ ከፍሎች ድምጽ የተሰጠበትና ውጤቱም የታውቆ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት አዲሱን አስተዳደር ዛሬ ይመሰርታሉ።
ባለፈው ሳምንት የተካሄደው ሁለተኛው ዙር የምርጫ ውጤት በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጸድቆ ይፋ ባይደረግም፤ ቀደም ባለው ምርጫ አብዛኞቹ የምክር ቤት መቀመጫዎች ውጤት በመታወቁ በሕጉ መሠረት በመስከረም ወር የመጨረሻ ሳምንት አዲሱ መንግሥት ይመሰረታል።
ዛሬ የመጀመሪያ ጉባኤውን የሚያካሂደው ስደስተኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ካሉት 547 መቀመጫዎች ውስጥ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ፓርቲ 410 ወንበሮችን እንዳሸነፈ ይፋ መደረጉ ይታወሳል።
ባለፉት ሁለት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዘመናት ገዢው ኢህአዴግ ከ547ቱ መቀመጫዎች ሙሉ ለሙሉ በሚባል ሁኔታ ፓርላመውን ተቆጣጥሮት እንደነበር ይታወሳል። ምርጫው ዘግይቶ በተካሄደባቸው ክልሎችና አካባቢዎች የሚገኘው ውጤት ገና የሚታወቅ ቢሆንም፤ ምንም እንኳን የተጠበቀውን ያህል ባይሆንም በተወሰነ ደረጃ ተቃዋሚዎችና የግል ዕጩዎች ምክር ቤቱን ተቀላቅለዋል።
በአዲሱ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውስጥ ብልጽግና ፓርቲ ግልጽ የበላይነትን በመያዝ አብዛኛውን መቀመጫ ይያዝ እንጂ፤ አሁን ባለው መረጃ መሠረት 11 መቀመጫዎችን የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት ሲያሸንፉ፣ አራት መቀመጫዎች ደግሞ በግል በተወዳደሩ ዕጩዎች ተይዘዋል።
በምርጫው ከተሳተፉት 47 ተቃዋሚ ፓርቲዎች መካከል ሦስቱ አስራ አንድ መቀመጫዎችን ያገኙ ሲሆን እነሱም የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) 5፣ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) 4 እና የጌዲዮ ሕዝብ ዴሞክራሲኣዊ ድርጅት (ጌህዴድ) 2 መቀመጫዎችን አግኝተዋል።
በተጨማሪም በግል ቀርበው ከተወዳደሩት 125 በዕጩነት መካከል አራቱ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውክልናን አግኝተዋል። እነዚህም የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ ዲያቆን ዳንኤል ክብረት፣ የኦነግ ቀደምት መስራቾችና አባላት የነበሩት አቶ ዲማ ነገዎና አቶ ገላሳ ዲልቦ እንዲሁም ኡስታዝ ካሚል ሸምሱ ናቸው።
ምርጫው ዘግይቶ በተደረገባቸው የሶማሌና የሐረሪ ክልሎች አጠቃላይ ውጤት ገና ባለመታወቁ በአዲሱ ምክር ቤት ምስረታ ላይ እንደራሴዎቻቸው አይገኙም። እንዲሁም ባለፈው ዓመት ጥቅምት ወር ጦርነት በተቀሰቀሰበት ትግራይ ክልል ውስጥ ምርጫው ባለመካሄዱ የክልሉ 38 ውክልናዎች ባዷቸውን ይቆያሉ።
ዛሬ በሚመሰረተው ምክር ቤት ውስጥ ከፍተኛውን የበላይነት የያዘው የብልጽግና ፓርቲ ሊቀመንበር ጠቅላይ ሚኒስትሩን ይሰይማል። በዚህም መሠረት ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በጠቅላይ ሚኒስትርነት ሥልጣን ላይ እንደሚቆዩ ይጠበቃል።
ከዚህ በተጨማሪ ባለፈው ሳምንት አስተዳደራቸውን የመሰረቱት ክልሎች ላይ እንደተስተዋለው በአዲሱ የፌደራል መንግሥቱ ካቢኔ ውስጥ ተቃዋሚዎች ቦታ እንደሚያገኙ ይጠበቃል።
በኦሮሚያ፣ በአዲስ አበባ፣ በአማራና በደቡብ ምክር ቤቶች ምስረታ ወቅት እንደታየው በተወሰነ ደረጃ ተቃዋሚዎች ሥልጣን እንዲጋሩ ተደርገዋል።
ቀደም ሲል ብልጽግና ፓርቲ ሲል እንደነበረው አዲስ በሚመሰረተው ካቢኔ ውስጥ ተቃዋሚዎች ሊካተቱ ይችላሉ። አንዳንዶች እንደሚገምትቱም ብልጽግና ከተቃዋሚ ፓርቲዎችም ሆነ በግል ከሚሳተፉ ግለሰቦች መካከል ጉልህ የሚባሉ የሥልጣን ቦታዎችን ሊያጋራ ይችላል።
ከእነዚህ መካከልም በምርጫው ከፍ ያለ ውጤትን ያገኛል ተብሎ የተጠበቀው የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ ፓርቲ (ኢዜማ) ከፍተኛ ግምት ተሰጠው ተቃዋሚ ነው።
ከመንግሥት ምስረታው ቀናት ቀደም ብሎ ጉባኤውን ያካሄደው ኢዜማ ከብልጽግና ፓርቲ አብሮ የመስራት ጥያቄ እንደቀረበለት የገለጸ ሲሆን፤ ይህንንም ጥያቄ ተወያይቶበት መቀበሉን አሳውቋል።
ምናልባትም ይህ ጥያቄ በፓርቲው ውስጥ ካሉ ፖለቲከኞች መካከል መሪውን ጨምሮ አንዳንዶቹን በፌደራል መንግሥቱ የተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ ለመሾም ዕድል ሳይፈጥር እንደማይቀር ተገምቷል።
በተመሳሳይም በግል ተወዳድረው የምክር ቤት መቀመጫዎችን ካገኙት እንደራሴዎች መካከልም በአዲሱ መንግሥት ካቢኔ እና በሌሎች የሥልጣን ቦታዎች ላይ ሊመደቡ የሚችሉበት ዕድልም አለ።
ይህ ሁሉ የሚሆነው ዛሬ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተሰብስቦ ከአባላቱ መካከል ቀጣዩን ጠቅላይ ሚኒስትር ከሰየመ በኋላ የተለያዩ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶችን የሚመሩ ሚኒስትሮችን አቅርቦ ይሁንታን ሲያገኝ ነው።
በምክር ቤቱ የሚመረጠው ጠቅላይ ሚኒስትር አገሪቱ አሁን ያለችበትን ሁኔታ እንዲሁም በቀጣይ አምስት ዓመታት የሚያከናውናቸውን ዋነኛ ተግባራቱን በተመለከተ ንግግር ያደርጋል።
ዛሬ የሚመሰረተው አዲሱ የፌደራል አስተዳደር ከዚህ ቀደም ከነበሩት የተለየ የሚያደርገው ሥነ ሥርዓት እንደሚኖር እየተነገረ ነው።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውስጥ ከሚካሄደው የመጀመሪያው የእንደራወሴዎች ስብሰባ፣ የጠቅላይ ሚኒስትር መሰየምና የካቢኔ ሚኒስትሮች ሹመት በኋላ በመስቀል አደባባይ ሌላ ዝግጅት እንዳለ የአገር ውስጥ መገኛኛ ብዙኃን እየዘገቡ ነው።
ከዚሁ ጋር ተያይዞም በአዲሱ መንግሥት ምስረታ ላይ ለመታደም የውጪ አገራት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ወደ አዲስ አበባ እየገቡ መሆናቸውን ከቅዳሜ ጀምሮ እየተነገረ ነው።














