ምርጫ 2013፡የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ብልፅግና ፓርቲ በከፍተኛ ድምፅ ማሸነፉ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የሚመሩት ብልፅግና ፓርቲ በከፍተኛ ድምፅ ማሸነፉን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በትናንትናው ዕለት አስታውቋል።
ቦርዱ እንዳመለከተው ብልፅግና ፓርቲ ከ436 መቀመጫዎች ውስጥ 410 ያሸነፈ ሲሆን ለቀጣዩ አምስት አመታትም መንግሥት መመስረት የሚያስችለውን ወንበር አግኝቷል።
የኖቤል የሰላም ሽልማት አሸናፊ የሆኑት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ "በታሪክ ሁሉን ያካተተ ምርጫ" በማለት በትዊተር ገፃቸው የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክታቸው አስፍረዋል።
ነገር ግን ከአገሪቱ የፀጥታና ሎጅስቲክ ችግሮች ጋር በተያያዘ በተወሰኑ አካባቢዎች ድምፅ መስጠት አልተቻለም።
በሺዎች የሚቆጠሩ በረሃብ በተጋለጡባትና በጦርነት በተጎዳችው የትግራይ ክልል ምርጫ አልተካሄደም።
ሰኔ 14፣ 2013 ዓ.ም ድምፅ መስጠት ባልተቻለባቸው አካባቢዎች በሌላኛው ዙር ጳጉሜ 1፣ 2013 ዓ.ም ምርጫው እንዲካሄድ ቢወሰንም በትግራይ እስካሁን የታወቀ ነገር የለም።
የዘንድሮው ብሔራዊ ምርጫ ከተያዘለት ቀን በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት እንዲራዘም መደረጉ የሚታወስ ነው።
አዲስ መንግሥት በጥቅምት ወር ይመሰረታል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን ሆኖም በምርጫው ትክክለኛነት ላይ አንዳንድ ጥያቄዎች መነሳታቸው አልቀረም።
አንዳንድ የተቃዋሚ ፓርቲዎች አመራሮቻቸው ለእስር በመዳረጋቸው ከምርጫው ራሳቸውን ያገለሉ እንዲሁም ለምርጫው ዝግጅት አስተጓጉሎናል ያሉ አሉ።
በበርካታ ክልሎች ታዛቢዎቻችን በአካባቢው ባለስልጣናት እና ሚሊሺያዎች ታግደዋል በሚል ፓርቲያቸው የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ከ200 በላይ ቅሬታዎች ማቅረባቸውን ብርሃኑ ነጋ (ዶ/ር) ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በበኩሉ በምልከታው "ከበድ ያለ ወይም የተስፋፋ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች አለመኖሩን" አስታውቋል።
ነገር ግን ኢሰመኮ በቅድመ ሪፖርቱ በአንዳንድ የምርጫ ጣቢያዎች ላይ ተገቢ ያልሆነ እስራት፣ የመራጮች ማስፈራሪያ እና ታዛቢዎቸና ጋዜጠኞች መዋከብ ደርሶባቸዋል ብሏል።
ከዚህም በተጨማሪ በኦሮሚያ ክልል እስከ ምርጫው ባሉ ቀናት በርካታ ግድያዎች መፈፃማቸውን መታዘቡን አስታውቋል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በግንቦት ወር የአውሮፓ ህብረት ኢትዮጵያ ምርጫውን ነፃ እንደምታደርገው ማረጋገጥ አልቻለችም በማለት ተችቷል።
ከሶስት አመት በፊት ወደ ስልጣን የመጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ በብልፅግና ፓርቲ ስር ለመጀመሪያ ጊዜ የተወዳደሩበት ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሙስናን በመግታት፣ ፖለቲካ እስረኞችን በመፍታት፣ በርካታ ሴቶችን በሚኒስትርነት በመሾምና ደም አፋሳሽ የሚባለውና በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ግለሰቦች የሞቱበትን የድንበር ግጭት መቋጪያ አግኝተዋል።
ከኤርትራ ጋር ሰላም በመፍጠር በነበራቸው ሚና የኖቤል ሽልማት ቢያሸንፉም ከአንድ አመት በኋላ በአገራቸው ትግራይ ክልል ወታደራዊ ዘመቻ ጀምረዋል።
የክልሉ አስተዳዳሪ የሆነው ህወሃት የወታደራዊ እዝ መቆጣጠሩ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ዘንድ ከስልጣናቸው ለመገልበጥ የተቃጣ ነው በሚል የታየ ሲሆን ዘመቻውም በዚያ ነው የተጀመረው።
የትግራይ ጦርነት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ህይወት መጥፋት ምክንያት ሲሆን በክልሉ ውስጥም በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ለረሃብ ተጋልጠዋል።
የተባበሩት መንግሥታት የዓለም ምግብ ፕሮግራም ከሁለት ሳምንት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ቅዳሜ እለት ወደ ትግራይ እርዳታ ይዞ መዘዋወር እንደጀመረ አስታውቋል።
የጦርነቱ ተሳታፊ አካላት አስፈላጊውን እርዳታ በማገድ እርስ በእርስ ሲካሰሱ ቆይተዋል።
ነዳጅ፣ ቴሌኮሙዩኒኬሽን፣ መብራትና ሌሎች መሰረታዊ አገልግሎቶች በክልሉ ባለመኖራቸው የሰብዓዊ እርዳታ ስራዎች እየተገደቡ መሆናቸውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አርብ እለት አስታውቋል።

ምርጫ 2013 በጨረፍታ
- 37,408,600 መራጮች ተመዝግበዋል ከዚህ ውስጥ 20,317,472 ወንዶችና 17, 091, 128 ሴቶች ናቸው
- 47 ፓርቲዎች 8,209 እጩዎችን አቅርበዋል 125 የግል ተወዳዳሪዎችም
- 634 የምርጫ ክልሎችና 49, 407 የምርጫ ጣቢያዎች
- 52,700 የምርጫ አስፈጻሚዎች፤ በእያንዳንዱ የምርጫ ጣቢያ 5 አስፈጻሚና 1 የኮቪድ-19 ቁጥጥር ባለሙያ
- ሰኔ 14/2013 ዓ.ም በተደረገው ምርጫ ለ445 የፓርላማ መቀመጫዎች ድምጽ ተሰጥቷል
- ጳጉሜ 01/2013 ደግሞ ለቀሪዎቹ 64 ወንበሮች ድምጽ ይሰጣል













