ምርጫ 2013፡ ብልጽግና ፓርቲ በአዲስ አበባ እና በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የበላይነት አገኘ

ድምጽ የሚሰጥ ግለሰብ

ገዢው ብልጽግና ፓርቲ የፌደራሉን መንግሥት ለመመስረት የሚያስችለውን የተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫ ማሸነፉ ተገለጸ።

ፓርቲው ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ቅዳሜ ሐምሌ 03/2013 ዓ.ም ይፋ ካደረጋቸው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫዎች መካከል ከፍተኛውን ማሸነፉ ታውቋል።

በቦርዱ ተጣርተው ይፋ ከተደረጉት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 425 መቀመጫዎች ውስጥ 410ሩን በማሸነፍ የበላይነቱን አረጋግጧል።

በዚህም መሠረት ብልጽግና ፓርቲ ቀጣዩን መንግሥት ለመመስረት ከሚያስፈልገው 274 መቀመጫዎች በላይ በማሸነፉ 410 መቀመጫዎችን አግኝቷል።

ይህ የመቀመጫዎች አሃዝም ድጋሚ ቆጠራና ምርጫ የሚደረግባቸው እንዲሁም በሁለተኛ ዙር የሚካሄደውን ምርጫ ውጤትን ሳይጨምር የተገኘ ነው።

ገዢው ብልጽግና ፓርቲ የአዲስ አበባ ከተማን ምክር ቤት ሙሉ ለሙሉ ሲቆጣጠር የከተማዋን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫ ከአንዱ በስተቀር 22ቱን አሸንፏል።

ሰኔ 14/2013 ዓ.ም በተካሄደው የመጀመሪያው ዙር ጠቅላላ ምርጫ የተረጋገጡ የምርጫ ውጤቶች በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ይፋ ተደርጓል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት ያሉት 138 መቀመጫዎችን በሙሉ ገዢው ብልጽግና ፓርቲ ያሸነፈ ሲሆን በከተማዋ ውስጥ በመራጭነት ለመሳተፍ ከተመዘገበው ነዋሪ 99 በመቶ ያህሉ ድምጽ ሰጥተዋል።

ስለዚህም ከፍተኛ ፉክክር ይደረግበታል የተባለውና ከዚህ ቀደሙ በተለየ በርካታ ፓርቲዎች በአገሪቱ ዋና ከተማ ምክር ቤት ውስጥ መቀመጫን ሊይዙ ይችላል ተብሎ የተጠበቀ ቢሆንም አንዳቸውም አልተሳካላቸውም።

ገዢው ፓርቲ ብልጽግና ሙሉውን የከተማዋን መስተዳደር ምክር ቤትን መቀመጫዎችን በማሸነፍ የበላይነቱን ተቆጣጥሮታል።

ከዚህ በተጨማሪም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውስጥ አዲስ አበባ ካላት 23 የውክልና መቀመጫዎች መካከልም የብልጽግና ፓርቲ 22ቱን ሲያሸንፍ ቀሪዋን አንድ መቀመጫ ደግሞ የግል ተወዳዳሪ አሸናፊ ሆኗል።

በዚህም በምርጫው የተሳተፉ አብዛኞቹ የአገሪቱ ዋና ከተማ ነዋሪዎች ገዢውን ብልጽግና ፓርቲን በከተማዋ ምክር ቤትና በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲወክላቸው መርጠውታል።

ከዚህ ባሻገርም ገዢው ብልጽግና ፓርቲ ምርጫው በተካሄደባቸውና ውጤታቸው በተረጋገጡ በሌሎች ክልሎች ውስጥ በሚገኙ የምርጫ ክልሎች ላይ የበላይነትን የሚሰጠውን የመቀመጫ ብዛት ማግኘቱን የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ መረጃ ያመለክታል።

የምርጫው ውጤት ይፋ ከመደረጉ በፊት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ውብሸት አየለ አጠቃላይ ሂደቱን የሚያስረዱ መረጃዎችን በንባብ አቅርበው ነበር።

በዚህም ለምርጫ ቁሳቁሶች በአጠቃላይ ከ845 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ መደረጉንና በሁለት የውጭ አገራት ለታተሙ የድምጽ መስጫ ወረቀቶች ህትመት 9 ሚሊዮን ዶላር መውጣቱ ምክትል ሰብሳቢው አመልክተዋል።

በተካሄደው ምርጫ ወቅት ቦርዱ በ165 የምርጫ ክልሎች ላይ ከ30 የፖለቲካ ፓርቲዎችና ከሰባት የግል ዕጩዎች አቤቱታዎች ቀርበውለት ምርምራ አድርጎ አስፈላጊው እርምጃ እንዲወሰድ ማድረጉን ገልጿል።

በምርጫው ላይ በታዛቢነት በርካታ የአገር ውስጥና የውጭ ታዛቢዎች የተሳተፉ ሲሆን ባለፉት ሳምንታት የምርጫውን ሂደት በተመለከተ ሪፖርታቸውን ለመገናኛ ብዙኃን ይፋ አደርገው ነበር።

ከእነዚህም መካከል የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን፣ የሲቪል ማኅበራት ጥምረት፣ የአፍሪካ ሕብረትና የምሥራቃዊ አፍሪካ የተጠንቀቅ ኃይል በሰጡት ማብራሪያ ሁሉም በምርጫው ሂደት ላይ የጎላ ችግር እንዳልተመለከቱና ሠላማዊ ምርጫ እንደነበር ተናግረዋል።

መስመር

በዚህ ዓመት ለማካሄድ ዕቅድ በተያዘለት ስድስተኛው ዙር ጠቅላላ ምርጫ ድምጽ ለመስጠት ከ38 ሚሊዮን በላይ ዜጎች በመራጭነት ድምጽ ለመስጠት መመዝገባቸውን ብሔራዊ ምርጫ ማስታወቁ ይታወሳል።

ይህ ምርጫ በተለያዩ ምክንያቶች በሁለት ዙሮች የሚካሄድ ሲሆን የመጀመሪያውና አብዛኛውን የኢትዮጵያ ክፍሎች የሚሸፍነው ምርጫ ሰኔ 14/2013 ዓ.ም መካሄዱ ይታወሳል።

ከጥቂት ሳምንታት በፊት በተካሄደው በመጀመሪያው ዙር ምርጫ የተሰጡ የመራጮች ድምጾችን የመቁጠር፣ የማረጋገጥና ይፋ የማድረጉ ሥራ በብሔራዊ ምርጫው አማካይነት ሲካሄድ ቆይቶ ዛሬ ሐምሌ 03/2013 ዓ.ም ይፋ ተደርጓል።

በምርጫው ላይ 47 የፖለቲካ ፓርቲዎች ለውድድር እራሳቸውን ያቀረቡ ሲሆን እነሱም ለክልሎችና ለፌደራል ምክር ቤት 8,209 ዕጩዎችን ያቀረቡ ሲሆን፤ እንዲሁም 125 በግላቸው የሚወዳደሩ ዕጩዎች ተሳታፊ ሆነዋል።

ገዢው የብልጽግና ፓርቲ 2,432 ተወዳዳሪዎችን በማቅረብ በዕጩዎች ብዛት ቀዳሚ ሲሆን የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) እና እናት ፓርቲዎች ደግሞ 1,385 እና 573 ዕጩዎችን በማቅረብ ይከተላሉ።

ለፌደራሉና ለክልል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤቶች 634 የምርጫ ክልሎች እንደሚኖሩ ቦርዱ የካቲት ወር አጋማሽ ላይ አስታውቆ ነበር።

ከክልል ምክር ቤቶች ጎን ለጎን የተመዘገቡ ዕጩዎች ለ547 የፌዴራል ምክር ቤት ወንበሮች በየአምስት ዓመቱ ይወዳደራሉ።

ሆኖም በትግራይ ክልል ስር የሚገኙት 38 ወንበሮች በዘንድሮ ምርጫ ባለመካተታቸው ለተቀረው የፌዴራል ምክር ቤት 509 ወንበሮች ድምጽ ይሰጣል።

ሰኔ 14 በሚካሄደው ምርጫ ለ445 የፓርላማ መቀመጫዎች ድምጽ የሚሰጥ ሲሆን ለ64ቱ ወንበሮች ደግሞ ጳግሜ 1/2013 ዓ.ም ድምጽ ይሰጣል።

መስመር

ምርጫ 2013 በጨረፍታ

  • 37,408,600 መራጮች ተመዝግበዋል ከዚህ ውስጥ 20,317,472 ወንዶችና 17, 091, 128 ሴቶች ናቸው
  • 47 ፓርቲዎች 8,209 እጩዎችን አቅርበዋል 125 የግል ተወዳዳሪዎችም
  • 634 የምርጫ ክልሎችና 49, 407 የምርጫ ጣቢያዎች
  • 52,700 የምርጫ አስፈጻሚዎች፤ በእያንዳንዱ የምርጫ ጣቢያ 5 አስፈጻሚና 1 የኮቪድ-19 ቁጥጥር ባለሙያ
  • ሰኔ 14/2013 ዓ.ም በተደረገው ምርጫ ለ445 የፓርላማ መቀመጫዎች ድምጽ ተሰጥቷል
  • ጳግሜ 01/2013 ደግሞ ለቀሪዎቹ 64 ወንበሮች ድምጽ ይሰጣል
ምርጫ 2013