ምርጫ 2013፡ ስለምርጫው እስካሁን የሚታወቁ አሃዞች

ስለ ምርጫ እየተረዱ ያሉ ሰዎች

የፎቶው ባለመብት, National Electoral Board of Ethiopia- NEBE

በኢትዮጵያ ለ6ኛ ጊዜ በሚካሄደው ጠቅላላ ምርጫ ድምጽ ለመስጠት ከ37 ሚሊዮን 400 መቶ ሺህ በላይ ዜጎች ካርድ መውሰዳቸውን ምርጫ ቦርድ ገልጿል።

ምርጫው በሁለት ዙሮች የሚካሄድ ሲሆን የመጀመሪያው ዙር ምርጫ ሰኔ 14/2013 ዓ.ም እንደሚከናወን ይጠበቃል። ለመሆኑ ስለምርጫው ቁጥሮች ምን ይላሉ?

ምርጫው ምን ያህል ተሳታፊዎች አሉት?

ከትግራይ ክልል በስተቀር በሁሉም ክልሎችና ከተማ መስተዳደሮች 20 ሚሊዮን 317 ሺህ 472 ወንዶች እንዲሁም 17 ሚሊዮን 91 ሺህ 128 ሴቶች በድምሩ 37 ሚሊዮን 408 ሺህ 600 መራጮች ድምጽ ለመስጠት ተመዝግበዋል።

ኦሮሚያ ክልል ከፍተኛ ድምጽ ሰጪዎች የተመዘገቡበት ክልል ነው። እንደ ብሔራዊ ቦርዱ መረጃ በክልሉ ከ15 ሚሊዮን 400 ሺህ በላይ ሰዎች የመራጭነት ካርድ ወስደዋል።

በተቃራኒው ጋምቤላ ክልል 415 ሺህ የሚጠጉ ሰዎች የምርጫ ካርድ የወሰዱ ሲሆን ዝቅተኛ መራጮች የተመዘገቡበት ክልል ነው።

በተያዘው ዓመት መጋቢት ወር መግቢያ ላይ የዕጩዎች ምዝገባን አስመልክቶ መግለጫ የሰጡት የቦርዱ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚዴቅሳ 47 ፓርቲዎች 8,209 ዕጩዎችን ማቅረባቸውን እንዲሁም 125 የግል ተወዳዳሪዎች በምርጫው ለመወዳደር መመዝገባቸውን ጠቁመዋል።

ብልጽግና ፓርቲ 2,432 ተወዳዳሪዎችን በማቅረብ በዕጩዎች ብዛት ቀዳሚ ሲሆን የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) እና እናት ፓርቲዎች ደግሞ 1,385 እና 573 ዕጩዎችን በማቅረብ ይከተላሉ።

ምርጫውን ለማስፈጸም 2 መቶ 54 ሺህ አስፈጻሚዎች እንደሚሰማሩ ብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያው ከወራት በፊት ዘግቧል።

በድምጽ መስጫ ቀን በእያንዳንዱ የምርጫ ጣቢያ 5 አስፈጻሚ የሚመደብ ሲሆን የኮቪድ-19 መከላከያ መንገዶችን የሚያስተገብር አንድ ባለሙያም ይኖራል።

በድምሩ በሁሉም የምርጫ ጣቢያዎች የሚኖረውን አስፈጻሚ ቁጥር ወደ 52 ሺህ 700 ከፍ ያደርገዋል።

ምርጫ 2013

ምንያህል የምርጫ ክልልና ጣቢያዎች ይኖራል?

ለፌደራሉና ለክልል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤቶች 634 የምርጫ ክልሎች እንደሚኖሩ ቦርዱ የካቲት ወር አጋማሽ ላይ አስታውቆ ነበር።

ከክልል ምክር ቤቶች ጎን ለጎን የተመዘገቡ ዕጩዎች ለ547 የፌዴራል ምክር ቤት ወንበሮች በየአምስት ዓመቱ ይወዳደራሉ።

ሆኖም በትግራይ ክልል ስር የሚገኙት 38 ወንበሮች በዘንድሮ ምርጫ ባለመካተታቸው ለተቀረው የፌዴራል ምክር ቤት 509 ወንበሮች ድምጽ ይሰጣል።

ሰኔ 14 በሚካሄደው ምርጫ ለ445 የፓርላማ መቀመጫዎች ድምጽ የሚሰጥ ሲሆን ለ64ቱ ወንበሮች ደግሞ ጳግሜ 1/2013 ዓ.ም ድምጽ ይሰጣል።

በሶማሌና በሐረሪ ክልሎች ሙሉ በሙሉ እና በሌሎች ክልሎች የወሰኑ የምርጫ ክልሎች ሰኔ 14 ምርጫ አይካሄድባቸውም።

በ634 የምርጫ ክልሎች ላይ 49 ሺህ 407 የምርጫ ጣቢያዎች ይኖራሉ። የኦሮሚያ ክልል 17, 623 የምርጫ ጣቢያዎችን በመያዝ ከፍተኛ የምርጫ ጣቢያዎች ያሉበት ክልል ነው።

በአንጻሩ 285 የምርጫ ጣቢያዎች የሚኖሩት የሐረሪ ክልል በጣቢያዎች ብዛት አነስተኛ ቁጥር ያለው ነው።

ምርጫና መራጮች

የምርጫ ክልልና የምርጫ ጣቢያ ልዩነታቸው ምንድ ነው?

የምርጫ ክልል በስሩ የሚገኙ የምርጫ ጣቢያዎችን የሚመለከቱ ተግባራትን ያከናውናል። ለአብነትም ወደ ምርጫ ጣቢያዎች ቁሳቁሶችን ማሰራጨት፣ ለሚቀርቡ አቤቱታዎች ውሳኔ መስጠት፣ ከምርጫ ጣቢያዎች የሚመጡ ቁሳቁሶችን መረከብ፣ ምርጫ ጣቢያዎችን መቆጣጠርና ሌሎች ተያያዥ ተግባራትን ይከውናል።

የምርጫ ክልሎች ዕጩዎችን የመመዝገብ ኃላፊነት ሲኖርባቸው በአንጻሩ ምርጫ ጣቢያዎች መራጮችን ይመዘግባሉ። ምርጫ ጣቢያዎች የምርጫ ሂደት ወሳኙ ተግባር የሚከወንባቸው ስፍራዎች ናቸው።

የተመዘገቡ መራጮች ድምጽ የሚሰጡት በጣቢያዎቹ ነው። በሌላ በኩል የተሰጡ ድምጾች የሚቆጠሩቱና የጣቢያውን ጊዜያዊ ምርጫ የማሳወቅ ኃላፊነት ተጥሎባቸዋል።

ምርጫ 2013 በጨፍታ

  • 37,408,600 መራጮች ተመዝግበዋል ከዚህ ውስጥ 20,317,472 ወንዶችና 17, 091, 128 ሴቶች ናቸው
  • 47 ፓርቲዎች 8,209 እጩዎችን አቅርበዋል 125 የግል ተወዳዳሪዎችም ተመዝግበዋል
  • 634 የምርጫ ክልሎችና 49, 407 የምርጫ ጣቢያዎች ይኖራሉ
  • 52,700 የምርጫ አስፈጻሚዎች ይሰማራሉ፤ በእያንዳንዱ የምርጫ ጣቢያ 5 አስፈጻሚና 1 የኮቪድ-19 ቁጥጥር ባለሙያ ይኖራል
  • ሰኔ 14 ለ445 የፓርላማ መቀመጫዎች ጳግሜ 1/2013 ደግሞ ለ64 ወንበሮች ድምጽ ይሰጣል

ያለፉት ምርጫዎች በአሃዝ

ከኢፌዴሪ መንግሥት ምስረታ በኋላ 5 ጠቅላላ ምርጫዎች ተካሂደዋል። በ1987 ለተካሄደው ለመጀመሪያው ምርጫ ከ21 ሚሊዮን 300 ሺህ በላይ ሕዝብ ለመራጭነት ተመዝግቦ እንደነበር የምርጫ ቦርድ መረጃ ያሳያል።

በሁሉም የምርጫ ክልሎች በተካሄደው በዚህ ምርጫ ከተመዘገቡት መራጮች ከ20 ሚሊዮን 68 ሺህ በላይ ሰዎች ድምጽ ሰጥተዋል።

በፓርቲዎች የቀረቡ ዕጩዎች 536ቱን የፌዴራል ፓርላማ ወንበር ያሸነፉ ሲሆን አስሩን ደግሞ በግል የተወዳደሩ ግለሰቦች አሸንፈዋል።

ከአምስት ዓመታት በኋላ በ1993 የተካሄደው ምርጫ ላይ ለመሳተፉ ከ26 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ካርድ የወሰዱ ሲሆን ከ19 ሚሊዮን 600 ሺህ በላይ ሰዎች በ26,112 የምርጫ ጣቢያዎች ላይ መርጠዋል።

ከዚህ በኋላ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ላይ የጎላ ስፍራ የሚሰጠው ምርጫ የ1997 ተከተለ። በዚህ ምርጫ ለመሳተፍ ከ27 ሚሊዮን 300 ሺህ በላይ መራጮች ተመዝግበው የነበረ ሲሆን ግንቦት 7/1997 በተካሄደው ምርጫ ድምጽ የሰጡት 22 ሚሊዮን 660 ሺህ ዜጎች ነበሩ።

በ2002 በተካሄደው ምርጫ ድምጽ ለመስጠት ወደ 32 ሚሊዮን የሚጠጋ ሕዝብ ካርድ ወስዶ ነበር። ድምጽ የሰጡት ግን ከ30 ሚሊዮን በታች የሆኑ ዜጎች ናቸው።

በምርጫው 63 ፓርቲዎች 6,904 ለፌዴራልና ለክልል ምክር ቤቶች ዕጩዎችን ያቀረቡ ሲሆን 45 ዕጩዎች ደግሞ በግል ተወዳድረዋል።

የመጨረሻው ምርጫ ከ6 ዓመታት በፊት የተካሄደ ሲሆን 37 ሚሊዮን የሚጠጉ መራጮች ተመዝገው 34 ሺህ 350 ዜጎች ድምጽ ሰጥተዋል።

58 ፓርቲዎች 5,219 እንዲሁም 11 የግል ዕጩዎችን ለአገር አቀፉና ለክልል ምክር ቤቶች መቀመጫ ተወዳድረዋል።

በዘንድሮ ምርጫ ደግሞ ከመጀመሪያው [ከ1987ቱ] ምርጫ የ16 ሚሊዮን ብልጫ ያለው መራጭ ተመዝግቧል። ለምርጫ 2013 ለኮሮናቫይረስ መከላከል የተመደበውን 1.1 ቢሊዮን ብርና ከለጋሾች የተገኘውን ገንዘብ ሳይጨምር የኢትዮጵያ መንግሥት 3.6 ቢሊዮን ብር ፈሰስ ማድረጉም ተሰምቷል።

ዕጩዎች
ምርጫ 2013