የአዲስ አበባ ጉዳይ፡ የ2013 ምርጫ ዋነኛ ጉዳይ

የአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት

የፎቶው ባለመብት, PM Office

ላለፉት አስርት ዓመታት የፖለቲካ ፓርቲዎች ዋነኛ አጀንዳዎች መካከል የመዲናዋ የአዲስ አበባ ጉዳይ አንዱ ነው።

የከተማዋ የአስተዳደር ጉዳይ፣ የከተማዋ የባለቤትነት መብት እና በሕገ-መንግሥቱ ላይ የኦሮሚያ ክልል ከአዲስ አበባ ልዩ ጥቅም ያገኛል የሚሉት ነጥቦች ብዙ ያከራክራሉ።

ከጥቂት ቀናት በኋላ በሚካሄደው 6ኛው አገራዊ ምርጫ የሚሳተፉ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ከአዲስ አበባ የሚወከሉ 23 የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ወንበርን ለማሸነፍ እንዲሁም ከከተማዋ 138 የምክር ቤት መቀመጫ አብላጫውን ለማሸነፍ ወደ ፉክክር የገቡት ፓርቲዎች ቁጥር ከፍተኛ ነው።

ለመሆኑ እነዚህ ፓርቲዎች በአዲስ አበባ ላይ ያላቸው አቋም ምንድን ነው?

ባልደራስ፡ "አዲስ አበባን ራስ ገዝ አስተዳደር እናደርጋለን"

በእስክንድር ነጋ 'የአዲስ አበባ ባላደራ ምክር ቤት' በሚል የተጀመረው እንቅስቃሴ 'ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ' ወደሚል ፖለቲካ ፓርቲነት መሸጋጋሩ ይታወሳል።

መሠረቱን አዲስ አበባ ከተማ ላይ ያደረገው ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ በምርጫው ድል ከቀናው አዲስ አበባ ከተማን ራስ ገዝ አስተዳደር እንደሚያደርግ አስታውቋል።

ባልደራስ አዲስ አበባ ለፌደራሉ መንግሥት ተጠሪ መሆኗ ቀርቶ እንደተቀሩት ክልሎች ራሷን የቻለች ራስ ገዝ አስተዳደር እንድትሆን እሰራለሁ ይላል።

ባልደራስ በሕገ-መንግሥቱ ላይ የኦሮሚያ ክልል ከአዲስ አበባ ልዩ ጥቅም ያገኛል መባሉን አጥብቆ የሚቃወም ሲሆን፤ ከአዲስ አበባ ልዩ ጥቅም ያለው ሕዝብ፣ ብሔር ወይም ክልል የለም ይላል።

የኢፌድሪ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 49.5 የኦሮሚያ ክልል ለፌደራሉ መንግሥት ተጠሪ ከሆነችው አዲስ አበባ ያለው ልዩ ጥቅም ይጠበቅበታል ይላል።

ሕገ-መንግሥቱ የኦሮሚያ ክልል የአገልግሎት አቅርቦት ወይም የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀምን እና የመሳሰሉትን ጉዳዮች በተመለከተ፤ እንዲሁም አዲስ አበባ በኦሮሚያ ክልል መሀል የምትገኝ በመሆኑ የሚነሱ ሁለቱን የሚያስተሳስሩ አስተዳደራዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ልዩ ጥቅም ይጠበቃል ይላል።

ኢዜማ፡ "አዲስ አበባ የነዋሪዎቿ ነች"

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማሕበራዊ ፍትሕ ፓርቲ በበኩሉ አዲስ አበባ የነዋሪዎቿ ነች የሚል አቋምን ያንጸባርቃል።

"አዲስ አበባ በአስተዳደር በኩል፣ በባለቤትነት እና በመብት ጥያቄ የነዋሪዎቿ ነው" ይላል ፓርቲው።

ምንም እንኳ ፓርቲው በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ዙሪያ በግልጽ ያስቀመጠው ነገር ባይኖርም፤ የፓርቲው መሪ ብርሃኑ ነጋ (ፕሮፌሰር) በቅርቡ ባደረጉት ንግግር "ክልሎች የተዋቀሩበት ሁኔታ ተጠንቶ እና ሕዝቡ ተወያይቶበት የሚወሰን ይሆናል" ብለዋል።

የአዲስ አበባ ጉዳይም ከክልሎች አወቃቀር እና አስተዳደር ጋር ከምርጫ በኋላ አብሮ የሚታይ እና መፍትሄ የሚያገኝ መሆኑን ጨምረው ተናግረዋል።

ብልጽግና፡ "አዲስ አበባ የኦሮሞ ሕዝብ ርዕሰ ከተማ ናት"

"አዲስ አበባ ከተማ የኦሮሚያ ክልል እና የኦሮሞ ሕዝብ የፖለቲካ እና ኢኮኖሚ ማዕከል ናት" ያሉት በሚንስትር ማዕረግ የመለስ አካዳሚ ፕሬዝደንት አቶ አወሉ አብዲ ናቸው።

የኦሮሚያ ክልል ከአዲስ አበባ ከተማ ልዩ ጥቅም ያገኛል ተብሎ በሕገ-መንግሥቱ የተደነገገው መጠበቅ አለበት ይላሉ አቶ አወሉ።

ምንም እንኳ በሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 49 የሰፈነው ኦሮሚያ ክልል ከአዲስ አበባ ከተማ ልዩ ጥቅም የማግኘት ጉዳይ ተግባራዊ ሳይሆን ለዓመታት የዘለቀ ጉዳይ ቢሆንም አቶ አወሉ ፓርቲያቸው ብልጽግና ቀጣዩን ምርጫ ቢያሸንፍ የኦሮሞ ሕዝብ ከአዲስ አበባ ከተማ ማግኘት ስላለበት ጥቅም ምላሽ ለመስጠት ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል።

"ከዚህ ሽግግር በኋላ ጠንካራ መንግሥት ተቋቁሞ የኦሮሞን ሕዝብ ብቻ ሳይሆን የሁሉንም ብሔር ብሔረሰቦች ጥያቄ ሙሉ በሆነ መንገድ መመለስ በሚቻልበት ሆኔታ ላይ እንሰራለን የሚል አቋም ይዘናል" ብለዋል።

line

የትኞቹ ፓርቲዎች በአዲስ አበባ ወዳደራሉ?

አዲስ አበባ ከተማ ለ23 የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲሁም ለአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት ለ138 ወንበሮች ዕጩዎችን ታወዳድራለች።

ገዢው ብልጽግና ፓርቲ ለከተማው እና ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በርካታ እጩዎችን አቅርቧል።

በብልጽግና በኩል የጤና ሚንስትሯ ዶ/ር ሊያ ታደስ፣ የውሃ፣ መስኖ እና ኢነርጂ ሚንስትሩ ዶ/ር ኢ/ን ስለሺ በቀለ፣ የትራንስፖርት ሚንስትሯ ዳግማዊት ሞገስ፣ የብሔራዊ ባንክ ገዢው ይናገር ደሴ (ዶ/ር)፣ የጠቅላይ ሚንስትሩ አማካሪ ዛዲግ አብረሃ እና ሌሎችም በከፍተኛ የሥራ ኃላፊነት የሚገኙ ፖለቲከኞችን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በእጩነት አቅርቧል።

ብልጽግናን በመወከል ለአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አባልነት ከሚወዳደሩት መካከል ደግሞ የከተማዋ ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ የወቅቱ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳዳሪ አብረሃም በላይ (ዶ/ር)፣ ንጉሱ ጥላሁን እና የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ለሊሴ ነሜ ተጠቃሽ ናቸው።

የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያን ተከትሎ ከተፈጠረው ሁከት ጋር ተያይዞ ክስ ተመስርቶባቸው በእስር ላይ የሚገኙት የባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ ፕሬዝደንት እስክንድር ነጋ በእስር ላይ ሆነው ለአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት ወንበር ይወዳደራሉ።

በተመሳሳይ ከእስክንድር ነጋ ጋር በእስር ላይ የሚገኙት ስንታየሁ ቸኮል እና አስካለ ደምሴ ለከተማ ምክር ቤት አባልነት ይወዳደራሉ።

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማሕበራዊ ፍትሕ- ኢዜማ በበኩሉ በአዲስ አበባ መሪውን ብርሃኑ ነጋ (ፕሮፌሰር)፣ ምክትላቸውን አንዷለም አራጌ እና በፍቃዱ ደግፌ (ፕሮፌሰር) ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ካቀረባቸው እጩዎች መካከል ተጠቃሽ ናቸው።

ኢዜማ ክቡር ገናን ለአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት በእጩነት ካቀረባቸው መካከል ይገኙበታል።