ምርጫ 2013፡ ለመጀመሪያ ጊዜ ድምጽ የሚሰጡ ወጣቶች ተስፋ

ሐዋሳ ከተማ ለ6ተኛው ዙር አገራዊና ክልላዊ ምርጫ በደማቅ እየተሰናዳች ትገኛለች። የስልክ እንጨቶች በተመራጮች ፎቶ ተጨናንቀዋል። የተለያዩ ፓርቲዎችም በመኪና በመዟዟር የምረጡኝ ቅስቀሳ ላይ ናቸው።
እንድሪያስ ከሐዋሳ ወጣ ብላ ከምትገኝ ገጠር የመጣው ከስድስት ዓመት በፊት እንደሆነ ይናገራል። በዘንድሮው ምርጫ ድምፁን ለመስጠት መመዝገቡንና ዕለቱንም በጉጉት እየጠበቀ እንደሆነም ይጨምራል።
"ባለፈው ወር ነው ለመምረጥ የተመዘገብኩት" የሚለው እንድሪያስ ከዚህ በፊት መርጦ እንደማይውቅ ይናገራል።
"ያው የገጠር ልጅ እንደመሆኔ ከዚህ በፊት ስለምርጫ ምንም የማውቀው ነገር የለም" የሚለው እንድሪያስ ስለምርጫ የሰማው ሐዋሳ ከተማ ከገባ በኋላ እንደሆነ ያስረዳል።
"አሁን ሁሉን ነገር አውቄ ለመምረጥ በመዘጋጀቴ ደስተኛ ነኝ" ባይ ነው እንድሪያስ።
የታቦር ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ የሆነችው አበዙ ጌታቸውም ለመጀመሪያ ጊዜ ነው ድምፅ ለመስጠት የተመዘገበችው። የምርጫ ካርድ የወሰድችው የመራጮች ምዝገባ የተጀመረ ሰሞን እንደሆነ ትናገራለች።
"ከዚህ በፊት ሞክሬ የማላውቀው ነገር ስለሆነ በጉጉት እየጠበቅኩት ነው" ስትል ትናገራለች አበዙ። ነገር ግን ወደ ምርጫ ጣብያ ሄዳ ድምፅ ለምትፈልገው ዕጩ አሊያም ፓርቲ እንዴት እንደምትሰጥ ብዙም ግንዛቤ እንደሌላት ትናገራለች።
በፈገግታ ታጅባ "ያው ለምፈልገው ፓርቲ ድምፄን ኮሮጆ ውስጥ ማስገባት አይደል" የምትለው አበዙ ከቤተሰቦቿ እንዲሁም ከምርጫ አስተባባሪዎች ስለድምፅ አሰጣጥ ጠይቃ ለመረዳት እንደተዘጋጀች ትናገራለች።
ሌላኛዋ የሐዋሳ ታቦር ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ የሆነችው ሊሊ ቶማስ ለመጀመሪያ ጊዜ ድምፅ ለመስጠት ተመዝግባለች።
"ቀጣይዋን ሰኞ በጉገት ነው እየጠበቅኳት ያለሁት" የምትለው ሊሊ፣ የተለያዩ ፓርቲዎች ያደርጉት የነበረውን የምርጫ ቅስቀሳ በመገናኛ ብዙሃን እንደተከታተተለች ትናገራለች።
"የሚያቀርቡት ሃሳብ በጣም ተመችቶኛል። ለመምረጥ ዝግጅቴን ጨርሻለሁ" ትላለች።
ሐዋሳ ላይ ያገኘናቸው ድምፃቸውን ለመጀመሪያ ጊዜ ለመስጠት እየተሰናዱ ያሉ አብዛኛዎቹ ወጣቶች ለሚፈልጉት ዕጩ እንዴት መስጠት እንዳለባቸው ብዙም ግንዛቤ እንዴሌላቸው ቢናገሩም፤ በድምፅ መስጫው ቀን የሚደረገውን ገለፃ ለመከታተል እንደተዘጋጁ ይናገራሉ።

'ዋናው ሰላም ነው'
በኦሮሚያ እና አማራ ክልሎች አጎራባች ከተሞች ላይ እየተንቀሳቀሰች እንደ ሰዓት፣ መነጽር እና ቀበቶ ያሉ ቁሳቁሶች እንደምትሸጥ የምትናገረው፤ የ19 ዓመት ወጣቷ ማስተዋል እንደሻው፤ በቀጣዩ ምርጫ ተሳትፎ የማደርገው "ሰላም የሚያሰፍን መንግሥት ይመጣል ብዬ ነው" ስትል ለቢቢሲ ተናግራለች።
"ሰላም አለመኖሩ በጣም አስቸጋሪ ነው። ከዚህ በፊት ወደ ኦሮሚያ ከተሞች እየሄድኩ በደንብ እሸጥ ነበር። ችግር ሲበዛ ግን ወደዚያ መሄድ አቁሚያለሁ። ሰላም ካለ ሕይወት ይሻሻላል ብዬ አስባለሁ። ሰላም ሲኖር ብዙ ሰርተን ጥሩ ነገር እናገኝ ነበር። ረብሻ እየበዛ እየሰራን አይደለም" ትላለች።
ለመጀመሪያ ጊዜ እንደምትመርጥ የምትናገረው ወጣቷ፣ ከቀጣዩ ምርጫ በኋላ ሰላም ሰፍኖ ወዳሻት ቦታ ተንቀሳቃስ የንግድ ሥራዋን እንደምታጠናክር ተስፋ አላት።
"ሰላም ካለ ተዟዙሬ እሰራለሁ። ከምርጫው በኋላ ሰላም ይመጣል ብዬ አስባለሁ" ብላለች ማስተዋል።
በጣና ሐይቅ ላይ ለጎብኚዎች በጀልባ የትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ሥራ ላይ የተሰማራው፣ የ27 ዓመቱ ወጣት አድማሴ አሰፋ ድምጽ ለመስጠት ለመጀመሪያ ጊዜ የምርጫ ካርድ መውሰዱን ይናገራል።
"ባለፉት ዓመታት መጀመሪያ ኮሮናቫይረስ ተብሎ ጎብኚዎች ጠፉ፤ ከዚያ በኋላ ደግሞ በአገሪቱ ሰላም ጠፍቶ ሥራ በጣም ቀዝቅዟል። በሽታውን የሚያጠፋልን ፈጣሪ ነው፤ ዋናው እኛ እርስ በእርሳችን ፍቅር ብንሆን ሰላም ይሰፍናል" ይላል አድማሴ።
"ምርጫ ካርድ ማውጣቴ ሰላም ያመጣል የምለውን እንድመርጥ ይረዳኛል። ለዜጎቹ አሳቢ የሆነ መንግሥት ስልጣን ላይ እንዲኖር ነው ፍላጎቴ" ሲል አድማሴ ያስረዳል።
'ሠላማችንን እንዲመለስ ነው የምመርጠው'
ሰናይት የደሴ ከተማ ነዋሪ ናት። በአንድ የመንግሥት መሥሪያ ቤትም ተቀጥራ ትሰራለች። ሰናይት በአገሪቱ የሚፈፀሙ ጥቃቶች፣ ግድያዎች፣ መፈናቀል እጅጉን ያሳስባታል።
"ሰው ባለው አቅም ሰርቶ በሠላም መኖር አልቻለም፤ ይህ ያሳስበኛል። የምመርጠውም ይህ እንዲለወጥ ነው" ትላለች። ሰናይት እንደምትለው አገሪቷ በማን ብትመራ ነው ወደ ሠላሟ የምትመለሰው በሚለው ላይ ደጋግማ አስባበታለች። የፓርቲዎችን ክርክርም ከመገናኛ ብዙኃን እንደተከታተለች ትናገራለች።
ሰናይት "አገራችን ሠላም ከሆነች ምንም አልፈልግም ዋናው ሠላም ነው። ሠላማችንን የሚመልስልን ያልኩትን ለመምረጥ ነው ያሰብኩት" ብላለች።
ከዚህም በተጨማሪ የሴቶችን አቅም ከፍ የሚያደርግ፤ ሴቶች የፈለጉትን ውሳኔ በራሳቸው መወሰን እንዲችሉ ሊያደርግ የሚችል ፓርቲን ነው ለመምረጥ የተሰናዳችው።
ሰናይት ሴቶች ያለምንም ፆታዊ ተፅእኖ ውሳኔ እንዲወስኑ የሚያሰችል ሥርዓት እንዲኖርም ፍላጎቷ ነው።
"እነዚህን ጥያቄዎቼን ይመልስልኛል ብዬ ያሰብኩትን ለመምረጥ" ቀኑን እየተጠባበቅኩ ነው ስትልም ታክላለች።
'የአማራው መፈናቀል ይቁም'
የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪ የሆነው ነጋ አስረስ ሰዎችን ሚዛን በመመዘን በሚገኝ ገቢ እና በሱቅ በደረቴ ሥራ ተሰማርቶ ይገኛል። መለስተኛ የዓይን ሕመም ያለበት ነጋ ለመጀመርያ ጊዜ ነው ምርጫ ካርድ የወሰደው።
በተለያዩ ቦታዎች የአማራ መፈናቀልና መገደል "በሞባይል ሬዲዮ እዚህ ዘምባባ ሥር ቁጭ ብዬ ሰምቻለሁ። የተፈናቀለ ዘመድ ወዳጅ የምለው ባይኖረኝም ይህ ነገር ነግ በኔ ይደርስ ይሆን እያልኩ እጨነቃለሁ" ይላል።
አክሎም "ወገን ሲፈናቀል ወገን ሲሞት ያስጨንቃል" ሲል የሚሰማውን ስሜት ይናገራል።
ከጀብሎው ጋር መንገድ ላይ ሚዛን የሚሰራው ነጋ፣ ኑሮ መወደዱን ሲያስረዳ "የሚመዘነው ሰው ኪሎ እየቀነሰ ነው" ይላል።
የገላ ሳሙና፣ ቆሎ፣ ኩኪስ፣ ፌስታል እና የአፍ እና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል የሚሸጠው ነጋ ከምሸጣቸው እቃዎች ውዱ የሚባለው ፖፖቲን ማስቲካ 5 ብር መግባቱን ይናገራል።
"አዎ ሰው ሲመዘን ይደነግጣል፤ ኪሎው የሚያስቀንሰው የኑሮ ውድነቱ ነው፤ ሁሉ ነገር 'ኦቨር' ሆነ፤ ነገን ሲያስብ ይጨነቃል" በማለት የኑሮ ውድነቱን የሚያስቆም እና ሠላም ሊያሰፍን የሚችል መንግሥት እንዲመጣ ፍላጎቱ መሆኑን አመልክቷል።
የጅማ ከተማ ነዋሪ የሆኑት አቶ ያሲን ናስር አባ ሞጋ፣ ለመጀመሪያ ጊዜ እንደሚመርጡ እና በዚህም በጣም ደስተኛ መሆናቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
"የሥራ እድል የሚፈጥርልንን፣ አገር የሚገነባን እና በውጪ አገር የምናየውን እድገት የሚፈጥር መንግሥት" እንደሚፈልጉም አክለው ተናግረዋል።
የአጋሮ ከተማ ነዋሪ የሆኑት አቶ ሴና ሸረፉ በበኩላቸው "የምመርጠው ለመጀመሪያ ጊዜ ነው። ምርጫውን በጉጉት ነው እየጠበቀኩ ያለሁት። ወድጄ ለመምረጥ እየጠበኩ ነው" ሲሉ ቃላቸውን ለቢቢሲ ሰጥተዋል።
'ምርጫ የደኅንነት ስጋቴን ይቀርፋል ብዬ አላስብም'
የ20 ዓመት ወጣት የሆነው በረከት አድማሱ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ ነው። 'በሰዎች ጉትጎታ' ምርጫ ካርድ ወስጃለሁ የሚለው በረከት፤ የ12 ዓመት ከፍል ፈተና ወስዶ ሃሮማያ ዩኒቨርሲቲ ተመድቦ ለመሄድ በዝግጅት ላይ እንደሚገኝ ይናገራል።
"እኔ የሚያሳስበኝ ይሄ ምርጫ ሳይሆን ዩኒቨርሲቲ ስገባ ብጥብጥ ይፈጠር ይሆናል ወይ የሚለው ነው" ይላል። "መምረጤ አይቀርም ግን ምርጫ በመካሄዱ በዩኒቨርሲቲዎች ያለው ችግር ይቀራል ብዬ አላስብም" በማለት ያስረዳል።
የአምቦ ከተማ ነዋሪ የሆነው መስፍን ተሻለ በስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ድምፁን እንደሚሰጥ እና በዚህም "ደስተኛ " መሆኑን ይናገራል።
ድምጼ ዋጋ እንዳለው አውቃለሁ የሚለው መስፍን፣ " ምንም እንኳ ምርጫው በኦሮሚያ ላይ ያን ያህል ጠንካራ ነው ብዬ ባላስብም፣ እኔ በዚህ ምርጫ ላይ ድምጽ መስጠቴ ዋጋ እንዳለው ስለማውቅ ለእኔ ትልቅ ትርጉም አለው" ይላል።
ሐዊ በቀለ ከዚህ ቀደም መርጣ እንደማታውቅ ትናገራለች። በእራሷ ተነሳሽነት የምርጫ ካርድ መውሰዷን የምታስረዳው ሐዊ " የኦሮሞ ሕዝብ የሚያነሳቸውን ጥያቄዎች ሁሉ ይመልሳል ብዬ ለማስበው ፓርቲ ድምጼን ለመስጠት ዝግጁ ነኝ" ትላለች።
የአምቦ ከተማ ነዋሪው አቶ በርሰን ተሻለም ልክ እንደሌሎቹ መራጮች ሁሉ ይህ ምርጫ የመጀመሪያቸው መሆኑን ለቢቢሲ አስረድተዋል።
በስድስተኛው አገር አቀፍ ምርጫ ድምጽ ለመስጠት ከ37 ሚሊዮን ሕዝብ በላይ የመራጭነት ካርድ መውሰዱን የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መረጃ ያሳያል።















