ሰይፉ ቱራ የቺካጎ ማራቶንን አሸነፈ

አትሌት ሰይፉ ቱራ

የፎቶው ባለመብት, Jamie Sabau

የምስሉ መግለጫ, አትሌት ሰይፉ ቱራ

ኢትዮጵያዊው አትሌት ሰይፉ ቱራ የቺካጎ ማራቶንን አሸናፊ ሆነ።

ሰይፉ ከፍተኛ ግምት ከሚሰጣቸው የማራቶን ውድድሮች መካከል አንዱ የሆነውን የቺካጎ ማራቶን ውድድር ለማጠናቀቅ፣ 2 ሰዓት 06 ደቂቃ 12 ሰከንድ ፈጅቶበታል።

አትሌቱ ሦስተኛው የማራቶን ድሉ ሲሆን በአቦት የዓለም የማራቶን ውድድር የመጀመሪያውን ድል መጎናጸፉን መረጃዎች ያመለክታሉ።

ከፍተኛ ግምት አግኝቶ የነበረው አሜሪካዊው ጋለን ሩፕ ሁለተኛ በመሆን ውድድሩን አጠናቋል።

ከ30ኛው ኪ.ሜ ጀምሮ ከመሪዎቹ ሯጮች ጋር የነበረው ሰይፉ አምስት ኪሎ ሜትሮች ሲቀሩ ብቻውን ተነጥሎ በመምራት ውድድሩን ማሸነፍ ችሏል።

ሰይፉን እና ሩፕን ተከትሎ ኬንያዊው ኤሪክ ኪፕታኑ በሦስተኝነት ውድድሩን አጠናቋል።

እስከ 25ኛው ኪሎ ሜትር ድረስ ውድድሩን ሲመሩ ከነበሩት መካከል የነበረው ሌላኛው ኢትዮጵያዊ ሺፈራ ታምሩ አምስተኛ ሆኖ ጨርሷል።

ውድድሩን በቀዳሚነት የጨረሱት አስር አትሌቶች አምስቱ ከአሜሪካ፣ ሁለቱ ከኢትዮጵያ፣ ሁለቱ ከኬንያ ሲሆኑ ቀሪው አትሌት ከጃፓን ነው።

በሴቶች የማራቶን ውድድር ኬንያዊቷ ሩት ቼፕጌቲች አሸናፊ ሆናለች።

ሩት ውድድሩን 2 ሰዓት 22 ደቂቃ 31 ሰከንድ በሆነ ሰዓት ነው የጨረሰችው።

አሜሪካዊያኑ ማ ቤትስ እና ሳራ ሃል ሁለተኛ እና ሦስተኛ በመውጣት ውድድሩን አጠናቀዋል።

ከቀዳሚዎቹ አስር የአሸናፊነት ቦታ ከያዙ አትሌቶች ውስጥ ሰባት አሜሪካዊያን ይገኙበታል።

አሸናፊዋን ሩትን ጨምሮ ሁለቱ ኬንያዊያን ሲሆኑ ኢትዮጵያዊቷ መሠረት በለጠ ዘጠነኛ በመሆን ውድድሩን አጠናቃለች።