ለ25 ዓመታት በየቀኑ ዓሣ እያሰገሩ፣ ዓሣ የበሉት የባሕር ዳር ነዋሪ

የአቶ አለልኝ ሕይወት
የምስሉ መግለጫ, የአቶ አለልኝ ሕይወት

የአቶ አለልኝ ሕይወት ከዓሣ ጋር የተቆራኘ ነው።

በአንድ የሥራ ዘርፍ የዕድሜያቸውን እኩሌታ አሳልፈዋል።

የሥራ ጠባያቸው ወጣ ገባ የሌለው፣ በባሕር ላይ መንሳፈፍ ብቻ ሆነ ነው…።

የአቶ አለልኝ ሕይወት በጭራሽ ደርቆ አያውቅም። ከእርጥብም እርጥብ ነው። ጣና ሐይቅ ከማደር በላይ ምን እርጥብ ሕይወት አለና?

ሐይቁ አልጋቸው ነው። እንጀራዎቻቸው ከአልጋቸው ሥር ይርመሰመሳሉ። የሳቸው እንጀራ ዓሣ ነው።

'በሬ ካራጁ' ብለን እንዳንተርት የሕይወት ዑደት እንዲያ ነው። አንዱ ሊኖር ሌላው ይሰዋል።

የዓሣዎቹ እስትንፋስ ሌሊት ሲያበቃ የአቶ አለልኝ ሕይወት ጠዋት ይለመልማል። ለሩብ ክፍለ ዘመን እንዲያ ነው የኖሩት። ከዓሣዎቹ ጋር።

የሚገርም ነው።

ካሳለፉት ረዥም ሕይወት በተለይም ባለፉት 25 ዓመታት አብዛኛውን ሌሊት ያደሩት በጣና ሐይቅ ላይ ነው። ለያውም እግራቸውን ዘርግተው።

ለጥ ብሎ በተኛው ሐይቅ ላይ ለሽ ብለው። በታንኳ አንቀልባ ታዝለው። ያለ አንዳች ሐሳብ። በማይናወጠው ጣና።

ለካንስ የጀልባ ዓሣ አስጋሪዎች ሕይወት እንዲያ ኖሯል።

የሳር ታንኳ አስጋሪዎች ካልሆኑ በቀር፣ ለካንስ የባለሞተር ጀልባ ዓሣ አስጋሪዎች የሥራ ሰዓት ሌሊት ሌሊት ነው።

ለካንስት ቤታቸው አያድሩም። ለካንስ ቤታቸው ጣና ሐይቅ ነው። ጎጇቸው ታንኳ ነው።

አቶ አለልኝ ለምሳሌ 24 ሰዓታቸው ምን እንደሚመስል በአንድ አንቀጽ ያስረዱናል።

"ተሲያት ላይ ጀልባ ይዘን ወደ ጣና ሐይቅ እንዘልቃለን። መረቡን እንዘረጋዋለን። ማታ እራት ቀማምሰን እዚያው እንተኛለን። ልክ ሌሊት 9፡00 ሰዓት ሲሆን ብንን ብለን ነቅተነ፣ ቀን 9፡00 ሰዓት የጣልነውን (መረባችንን) ከሌሊቱ 9፡00 ሰዓት እንስበዋለነ።"

ሐይቅ ላይ መተኛት አደጋ የለውም? ስንል ጠየቅናቸው።

"ምንም ሆነን አናውቅ እንግዲህ። ምናልባት ጀልባው ነዳላ ከሆነ እንቅልፍ ካዛለ አፍሶ ሊሰምጥ ይችላል። ነፋስ ካለም መልህቅቱ ያቆመዋል እንጂ እንዲያው ምንም አንሆን።"

እንዲህ እያለ ጠዋት ላይ ሕይወት ይቀጥላል።

ሌሊት የታደነው ዓሣ ማልዶ ወደ ባሕሩ ዳርቻ ተጭኖ ይመጣል። ከዚያም ዓሣዎቹን በመልክ በመልኩ ይሰድሯቸዋል።

ሁሉ ጠቦት በግ አንድ አይደለም። የሸረፈ/ያልሸረፈ እየተባለ ይብጠለጠላል። ሁሉ ዓሣ አንድ አይደለም። የሰባ/ያልሰባ፣ ነጭ/ጥቁር፣ ሙልጭልጭ/ቁልጭልጭ… ይባላል።

ከባሕር የወጣ ሁሉ ዓሣ አይደለም። መልክ አለው። ወግ አለው። ለዚያም ነው በፈርጅ በፈርጁ የሚሰደር።

ከሐይቁ ወደ ባሕር ዳርቻ ሲደርስ ተረካቢ እየመዘነ በኪሎ ይወስደዋል። ወዲያውኑ ለባሕር ዳር ተጠቃሚ በትኩሱ ይከፋፍላሉ።

በባሕር ዳር ዓሣና ማቀዝቀዣ እምብዛምም አይተዋወቁም። ዓሣ የሚበላው ከውሃ እንደወጣ በቀጥታ ነው። ከሐይቅ ወደ ፍሪጅ ሳይሆን ከሐይቅ ወደ ሆድ!

በቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን በኩል ሐይቁ ዳርቻው ላይ የሚገኙት ዝነኞቹ እነ ባንቹ ይከሽኑታል።

በዱለት፣ በወጥ፣ በሸክላ፣ ከቺፕስ ሁሉ አይቀራቸውም።

እነ ቀስተ ደመና፣ እነ ይጋርዱ፣ እነ ሚካኤል፣ እነ ዓሣ አጥማጆች ማኅበር ባሕር ዳርን ይቀልቧታል። ትኩስ ዓሣ ያበሏታል። በብልሃት።

ጣና ሐይቅና እርኩስ መንፈስ

ሐይቆች በእርኩስ መንፈስ የተሞሉ እንደሆኑ አፈ ታሪክም ታሪክም ሲነግሩን ኖሯል። እውነት ይሆን?

25 ዓመታትን በሐይቅ ላደረ ሰው መቼስ ይሄን ጥያቄ አለማንሳት አግባብ አይደለም።

ቢቢሲ፡- ሐይቅ ላይ ለ25 ዓመት ሲያድሩ እንደው ሌሊት ላይ ጂኒ ምናምን፣ እንደው አንዳች እርኩስ መንፈስ ውልብ ሲል አይተው አያውቁም?

አቶ አለለኝ፡-ኧረ ምንም! አንድም አላየሁ።

ቢቢሲ፡- እሺ ይሁን! ግና የሞቀ ቤት እያለ ሐይቅ ላይ እየተንሳፈፉ ማደር ግን አይከብድም?

አቶ አለለኝ፡- ኧረ እንዲያም። ከሐይቁ ላይ ማደር እኮ ቅጥቃጤ የለው። ቅዠትም የለም። እንደታዘለ ልጅ እንቅልፉን እናጣጥመዋለን'ይ።

ለ25 ዓመታት ዓሣን መብላት ብልህ ያደርጋል?

ለመሆኑ የትኛው የተድላ ሕይወት ነው በየዕለቱ ዓሣ የሚያስበላ?

የአቶ አለለኝ ሕይወት ነዋ።

እሳቸው ባለፈው ሩብ ክፍለ ዘመን ዓሣን ሳይመገቡ ያሳለፉት ዕለት ትዝም አይላቸው።

ቢቢሲ፡- የምር በየቀኑ ለ25 ዓመታት ዓሣ በልቻለሁ ነው የሚሉን?

አቶ አለልኝ፡- እንዲያ አላልኩም፤ አታስዋሹኝ። አርብ ዕሮብ ዓሣ አይበላም። ሁዳዴ ጦም ከሆነም አልበላም። ፍልሰታም እንዲያ ነው። በነዚህ ጊዜያት ዓሣ አልበላም። በኛ በገጠር ዓሣ በጦም አንበላም። ምስርና ሽሮ ነው የምንበላ።

ቢቢሲ፡- ከጾሙ ውጪ ማለታችን ነበር…።

አቶ አለልኝ፡- ከጾም ውጪማ ታዲያ ምን እበላለሁ? አሃ! ደግሞስ እንዴት ሳልበላው እሸጣለሁ አንተዬ!

የሆነስ ሆነና፤ ዓሣ ብልህ ያደርጋል? የአቶ አለልኝ 'ምጥቀተ አእምሮ' (IQ) እንዴት ይለካ?

የሳቸውን አስተያየት ከመጠየቅ ውጪ አማራጭ የለም። እንዲህ አሉ፡-

"በሳይንሱ ዓሣ የበላ ሰው ጭንቅላቱ ክፍት ነው፤ ሁሉ ነገር ይጨብጥለታል ይሉናል። እንጃ ብቻ፤ እኛ ዓሣ አስጋሪዎች 'ካልኩሌታ' ፈልገን አናቅ። በቃል ነው ሒሳብ የምናሰላ። ከዓሣው ይሁን ከተፈጥሮ ብቻ እንጃ። በሽታም ብዙም አይደፍረነ። ለወባም ተጋላጭ አደለን።"

አቶ አለለኝ በዕድሜ ዘመናቸው ታመው ሆስፒታል የጎበኙት አንድ ጊዜ ብቻ ነው። እሱም ጠመንጃ ባርቆባቸው።

አንድ ዓሣ አስጋሪ በጣና ሐይቅ ላይ
የምስሉ መግለጫ, ዓሣ አስጋሪ በጣና ሐይቅ ላይ

የዓሣ ክ'ፋቱ፣ ውድነቱ

የዓሣ ዋጋ በአዲስ አበባ ኪስ ያደማል። የሞጃ መብል ሊሆን ምን ቀረው?

ባሕር ዳር ግን እዚያ አልደረሰም።

ለመሆኑ ዓሣን ያስወደደው ምኑ ነው?

አቶ አለልኝ ሁሉም ዓሣ እኮ ውድ አይደለም ይላሉ።

የዓሣ ዓይነቶችን በመዘርዘር ይጀምሉ።

"ቀይ ዓሣ፣ ቀረሶ፣ ቤዞ፣ ብልጫ፣ ነጭ ዓሣ ብቻ ዓይነቱ ብዙ ነው። የነጭ ዓሣ ዝርያ ራሱ ለየቅል ነው። ለምሳሌ ወርቅአፈራሁ የምንለው ዓሣ አለ። ጥብቅ ዓሣ ነው፣ የማይሰባ ዓሣ አለ። ለወጥ የሚሆን አለ። ብዙ ነው አንተዬ።"

ወርቃፈራሁ ስሙ ደስ ይላል። ምን ዓይነት ዓሣ ይሆን?

"በጣም ስብና የሚቅለጠለጥ ዓሣ ነው። 'አፈካውቻ' የምንለው ደግሞ አለ። ደግሞ 'ቤዞ' የምንላት አለች፤ ጥጥ ናት፣ ተራራ ናት። የተለየች ናት። ጥቁር ዓሣ አለ። ርካሹ ደግሞ ነጭ ዓሣ ነው። እሱን በግዙፍነት የሚያህለው የለም። ፈላጊ ግን የለውም። እሾሃማ ነው። የከተማ ሰው አይወደውም።"

ቢቢሲ፡- ከዓሣዎች ሁሉ ውዱ ዓሣ የቱ ነው?

አቶ አለኝ፡- ቀረሶ ነው። ድፍኑ እስከ 80 ብር በኪሎ ይሸጣል። ባዶ ሥጋ ኾኖ፣ እሹሁ ወልቆ ደግሞ እስከ 250 ብር ይሸጣሉ።

ቢቢሲ፡- ይሄ ፈረንጆቹ ሳልመን (Salman) የሚሉት ዓሣ ይሆን?

አቶ አለኝ፡- እሱን እንኳ አላውቀውም፤ ለፈረንጅኛው አንተ ትቀርባለህ።

ዓሣዎች እየተመናመኑ የመጡት በፖለቲካ አሻጥር ነው?

ኢህአዴግ ከገባ ባሉ የመጀሪመያ ዓመታት ዓሣ ማስገር የጀመሩት አቶ አለልኝ የዛሬ 10 እና 15 ዓመታት አካባቢ 'በክብደት እስከ 6 ኩንታል ያሰገርንበት ጊዜ ነበር' ይላሉ።

በጊዜ ሂደት ግን ዓሣ በቁጥር በእጅጉ እየቀነሰ እንደሆነ ታዝበዋል።

ዓሣዎች ወዴት እየሄዱ ነው የጠፉት? አልናቸው እንደዋዛ።

"ታዲያ ሐይቁ ያው ሆኖ ሳለ ዓሣዎች ለምን ጠፉ ይላሉ?" አልናቸው። ተንሽ ውስብስብ ማብራሪያ ሰጡን።

"ምን መሰለህ! ዝናም መትመቱን ከጣለ ማለት ነው ዓሣ ይወርዳል። ባሕሩ ይሞቃል። ግን ዝናብ ሳይጥል ባዥቶ በሰማይ ላይ ዳመናና ዝናብ ካየ ዓሣ ይሸሸጋል፡፡…

"ዓሣዎች ሰማዩ ላይ ጠጠር ካዩበት በጣም ይሸሻሉ። ለዚያ ነው የሚጠፋ። ዝናቡ መትመቱን አጠዥቶ ከጣለ ጎርፉ ከገባ፣ የተፋሰሶች ድፍርሻ ያን ሌሊት ይያዛል።"

"አሁን ያወሩት ነገር ብዙም አልገባኝም። ምንድነው አጠዥቶ፣ መትመቱን፣ ድፍርሻ የሚሉኝ ነገር?"

"…መትመቱን ጠበቅ አርጎ ክፍት ክድን ሳይል። ድርስ ምልስ ሳይል ማለቴ ነው። ሰኔ ገበሬው አርሶታል። አፈሩ ደፍርሶ ይወርዳል ከደለሉ። በዚያን ሰዓት ዓሣ ይያዛል። ድፍርሻ የምልህ እሱን ነው።"

አሁንም ያሉት እምብዛምም አልገባንም። ስለነገሩ መሠረታዊ ዕውቀት የለን ይሆናል። ብቻ እንለፈው። ስለ እንቦጭ ያነሱልኛል ብዬ ነበር እሱን ጭራሽ አላነሱትም።

በ25 ዓመታት ውስጥ የስንት ዓሣዎችን 'ነፍስ አጠፉ'?

ይህን አሐዝ ለመገመት ብዙ ተቸገሩ። አጥብቀን ጠየቅናቸው።

"እኔ እንዴት አውቄ፣ ከቁጥርም በላይ ነው። ኮምፒተር ይችለው እንደሁ እንጃ እንጂ፤ እኔ ለራሴ አይቆጠርልኝም" አሉ።

"ይተዉ እንጂ! እንደው ዓሣ በቀን በቀን የሚበላ ሰው ሒሳብ ማስላት ይጠፋዋል እንዴ?" አልናቸው። ነገሩ አሳቃቸው።

"እሯ! ይሄ በዝቶ ነው እንጂ እኛ እዚህ ዓሣ አስጋሪዎች አንዳችንም ሒሳብ ቸግሮን አያውቅ። በጭንቅላታችን ነው የምናሰላ።"

የሆነው ሆኖ አቶ አለልኝ ዓሣን ወር እስከ ወር ያሰግራሉ።

"ሠላሳውንም ቀን ምናሰግርበት ጊዜ አለነ" ይላሉ። በለስ ሲቀና ነው ታዲያ። ሁልጊዜ ግን እንዲህ መንበሽበሽ አለ ማለት አይደለም።

"ከወሩ 20 ቀን እንዳሰገርነ የምንቀርበት ጊዜ አለነ። ያ ለምንድነው ምርቱ ሲቀንስብነ፣ ነዳጅ ሲጨምርብነ ነውይ…" ይላሉ።

ነዳጅና ዓሣን ምን አገናኛቸው አቶ አለልኝ?

"አሃ! ጀልባ በምንድነውይ የሚሠራ?"

አቶ አለልኝ ቅዳሜና እሑድም ይሠራሉ። ከወር ወር ምንም እረፍት የለም።

"ዓሣዎቹ ሰንበት አያውቁም ነው የሚሉን?" አልናቸው።

"ምኑን አመጣኸብኝ አንተዬ! ዓሣዎቹ ይሄን የት ያውቁና። ወጥመዳቸውን አበጅላቸው እንጂ መረብ ውስጥ ሰተት ብለው ነው ሚገቡ" (ሳቅ)

አቶ አለልኝ በቀን ሲቀናቸው 600 መቶ ዓሣ የሚይዙበት ጊዜ አለ። ሳይሆን ሳይሆን ደግሞ 15 እና 20 ፍሬ ይዘው የሚመለሱበትም ወቅት አለ።

እንዲህ ሲመናመን አንድ ሁለት ሦስት ቀን ፋታ ይሰጡታል። ምክንያቱም የዓሣዎቹ ገቢ የነዳጅ ወጪውን አልሸፍን ሲል። ይሄ ወርሃዊ የነዳጅ ዋጋ ክለሳ ለካንስ የብስ ብቻን አይመለከትም። ተጽእኖው ጣና ይደርሳልና?

አቶ አለልኝ በወር ውስጥ እንደው በትንሹ ስንት ዓሣ ያሰግራሉ ተብለው ሲጠየቁ፡-

"…ዞሮ ዞሮ እንዲያው አልያዝንም ቢለነ፤ እንዲያው በቃ ደረቀ ቢባል። በወር 15ም ቀን 20ም ቀን ሠራን ብንል፣ ቢያንስ ቢያንስ በወር 2ሺህ ዓሣ እንይዛለን።"

25 ዓመታት ዓሣ ማስገር ሕይወት ይለውጣል?

ዓሣ መብላት ጤናን አረጋግጦላቸው ሊሆን ይችላል። የሆነስ ሆነና፣ ለሩብ ክፍለ ዘመን ዓሣን ማጥመድ ሕይወት ይለውጣል?

ጥያቄውን ለእርሳቸው ማንሳታችን አልቀረም። ይሄን ሁሉ ዓሣ ነፍስ አትጥፍተው ሕይወትዎ ምንኛ ተለወጠ? አልናቸው።

ከሳቁ በኋላ እንዲህ መለሱ፡

"በደንብ ነው እንጂ የለወጠ። '6 ልጅ አልብሼ፣ እየቀለብኩ የማስተምር በምን ሆነና!?' ስጀምር በሣር ታንኳ ነው የጀመርኩት። አሁን ጀልባ ገዝቻለሁ። ቤተሰብ ቀጥ አድርጌ አስተዳደርለሁ፤ ምን ትፈልጋለህ። ስድስት ልጅ ወልዶ ማስተማር ቀላል ነው'ይ? ተመስገን ነው እንጂ።"

አቶ አለልኝ ከስድስቱ ልጆቻቸው ሌላ ሁለት ልጆችንም እየከፈሉ ያስተምራሉ።

"እኔ ከሐይቅ ተዘፍዝፌ የኖርኩት ይበቃል ብዬ ነው ልጆቼንም የማስተምር። አሁን ጥሩ እየተማሩልኝ ነው…። ያቺኛይቱ መታደል 11ኛ ክፍል ደርሳለች፤ ወሮታ ናት…። ትንሺቱ ደግሞ እርቄ…" እያሉ የልጆቻቸውን ስኬት አወጉን።

እውነትም አቶ አለልኝ እንደ ባሕሩ የረጋ ሕይወትን ይመራሉ።

ስድስት ቤተሰቦቻቸውን አብልተው አጠጥተው አስተምረው፣ የራሳቸውን ጀልባ እየነዱ በደስታና ፍሰሐ…።

ብቻ ተመስገን ነው።

ሙልጭልጭ የጣና ሐይቅ ዓሣዎች ከባሕሩ እስካሉ ይህ ተድላ የሚቀጥል ይመስላል።

"እኔ ከሐይቅ ተዘፍዝፌ የኖርኩት ይበቃል ብዬ ነው ልጆቼን የማስተምር…" ያሏት ነገር ግን…፤ የዋዛ ንግግር አትመስልም።

እንደ ዓሣ እሾህ ተአአምሮ ላይ ተሰንቅራ ቀረች።