ጥዑሙ የጣና ሐይቁ የዘጌ ቡና ምን ክፉ አገኘው?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ዘጌዎች ቡናቸው ጥዑም ነው።
የዘጌ 'ኮከል' ቡና በዓለም ከፍተኛ ዕውቅና ከተሰጣቸው አገር በቀል የቡና ዝርያዎች አንዱ ነው ይላሉ ነዋሪዎች።
አሁን ግን ያልታወቀ በሽታ ላይ ወድቆ ቡናውም የደሴቲቱን ነዋሪዎች ለችግር ተዳርገዋል።
ለመሆኑ የዘጌ ቡና ተክል በትክክል የገጠመው ችግር ምንድው?
ዘጌ እና የቡና አፈታሪክ
የሰባት ጥንታዊ አብያተ ክርስቲያናት መቀመጫ የሆነችው ዘጌ በተለይ ዘጌ ጊዮርጊስና ኡራ ኪዳነ ምሕረት ተብለው በሚጠሩ ጥንታዊ ገዳማት ይበልጥ ትታወቃለች።
ከጥንታዊ አብያተ ክርስቲያናትና ገዳማት ሌላ ዘጌ ቡናዋም ጥዑምና ጥንታዊ እንዲሁም ቅይጥ የማያውቅ ቱባ ተክል እንደሆነ ይወሳለታል።
እንዲያውም በዘጌ ከእረኛው የከፋ ግዛት ካልዲ አፈ ታሪክ በመጠኑ ዘወር ያለ የቡና አመጣጥ ወግ አልፎ አልፎ ይነገራል።
"በድሮ ክፍለ ዘመን ሦስት ቅዱሳን ዘጌ ደሴት ሱባኤ ገቡ። ምን እንብላ ብለው ጌታን ቢማጸኑ የቡና ቅጠል ሸምጥጣችሁ ባንድ ትንፋሽ ብትጨልጡ በጸሎታችሁ ትጉህ ትሆናላችሁ ተባሉ። የዘጌ ቡናም ከዚያ የጀመረ እነሆ እንደጣፈጠ በዓለም ተበትኖ አለ።"
ዘጌ ባሕረ ገብ ደሴት ስትሆን ከጣና ዳርቻ፣ ከውቧ ባሕር ዳር በቅርብ ርቀት ከሚገኙት ደሴቶች አንዷ ናት።
በደን የተሸፈነው የዘጌ መሬት ለሰፋፊ እርሻ ምቹ አይደለም። ለቡና ተክል ግን መልካም የሚባል ነው።
የዘጌ ቡና ከሌላ ቦታ በመጣ የቡና ዝርያ የተሸፈነ ሳይሆን ለዘመናት በዚያው በሚበቅል ቱባ ቡና የሚታወቅ ነው።
አካባቢው ከዓመት ዓመት እርጥበት ስለማይለየው ለቡና ምርት ተጨማሪ ዕድል ፈጥሮ ቆይቷል።
የዘጌ ቡና ከሌሎች አካባቢ ቡናዎች በተለየ ለባዕድ ኬሚካሎች አለመጋለጡም ተወዳጅ አድርጎት ቆይቷል።
የዘጌ ቡና አምራቾች የሥራ ማኅበርም የቡና ተክሉን ለውጭ ገበያ ግብይት ሲያቀርብ ቆይቷል።
የዘጌ ቡና አምራቾች ግብይት ኅብረት ሥራ ማኅበር ባልደረባ አቶ ግርማው አለባቸው ለአማራ መገናኛ ብዙኃን በሰጡት አንድ ቆየት ያለ ቃለ ምልልስ የዘጌ ቡና ከተፈለፈለ በኋላ ኢንተር አሜሪካ ግሩፕ የሚባል ድርጅት እንደሚረከበው ገልጸው፤ የዚህ ድርጅት መዳረሻ ገበያ ደግሞ ጣሊያን፣ ጀርመን፣ ፈረንሳይና ኦስትሪያ እንደሆኑ አብራርተው ነበር።
ይህም ማለት የዘጌ ቡና በአውሮፓ ሰፊ ተቀባይነትን እንዳለው አመላካች ነው።
በሁለት ቀበሌዎች ተዋቅራ ከ10ሺህ የበለጠ ነዋሪ ያለባት ጥንታዊና ታሪካዊቷ ደሴት ዘጌ፣ መሬቷ ከ1ሺህ ሄክታር መሬት በላይ በቡና ተክል የተሸፈነ ነው።
ዘጌ ከባሕር ዳር በታንኳ የአንድ ሰዓት ጉዞ በየብስ ደግሞ የ30 ኪሎ ሜትር ርቀት ያላት ባሕረ ገብ ናት።
በተለይ የየብስ ጉዞው ምናልባት አዲስ እየተሠራ ካለው አስፋልት መጠናቀቅ በኋላ ከዚህም ሊያጥር እንደሚችል ይገመታል።
ይህም የዘጌ ደሴት ነዋሪዎችን ለንግድ መሳለጥ ትልቅ ተስፋ እንዲጥሉ አድርጓቸዋል።
የዘጌ ደሴት ነዋሪዎች ከቡና ውጭ ሎሚ፣ አደስና ጌሾ እንዲሁም ማንጎ በማምረት ይታወቃሉ።
አንዱም ግን እንደ ቡናቸው ዝነኛ አይደለም።
አሁን መፍትሄ እየፈለጉ ያሉትም ለዚሁ ለቡናቸው ነው።
በድንገት ያ የሚሳሱለትን የቡና ተክላቸውን 'ፈንገስ' ወሮባቸዋል።
ወደ ዘጌ ከመዝለቃችን በፊት በየብስ ወደዚያው ሲገባ የምትገኘዋን ቀበሌ እናቃኝ።
ይህቺ የባሕር ዳር ዙርያ ቀበሌ ወንጀጣ ትባላለች። በዚያ ሁለት ነዋሪዎችን አግኝተን አነጋግረናል።
የመጀመሪያ ነዋሪ አብቧል ዘነበ ይባላል።
በቡና ተክል ላይ የመጣው 'ተባይ' ሲነሳበት "ነገሩ ግራ ሆኖብናል" ይላል።

የፎቶው ባለመብት, JENNY WILLIAMS/RBG KEW
"በድንገት ፈንገስ የሚመስል ነጠብጣብ ነገር በቡናና በማንጎ ተክላችን ላይ ማየት ጀመርነ። ይህ ከሆነ ሁለት ዓመት ይሆነዋል። ብንጠብቅ ብንጠብቅ በሽታው አልድን አለነ" ሲል ለቢቢሲ ዘጋቢ ተናግሯል።
ፈንገሱ በብዛት የሚታየውም በቅጠሉና በፍሬው ላይ እንደሆነ ይናገራል።
"ነጫጭ ነገር በቡናው ቅጠልና ፍሬ ከታየ በኋላ ቡናው በአንድ ጊዜ ድርቅ ይልብናል፤ ምን እንደሁ እንጃ።"
ይህን አዲስ ክስተት ለአካባቢው የግብርና ባለሙያዎች አሳውቃችሁ ነበር ወይ በሚል ላነሳንለት ጥያቄ አብቧል ሲመልስ፣
"የግብርና ባለሙያዎችን ምን እናድርግ ብለን ስናማክራቸው ቁረጡትና ተገርዞ እንደገና የሚያቆጠቁጠው ተክል የተሻለ ይሆናል ብለውን እንዳሉን ብናደርግም ግን ለውጥ አላየንም" ብሏል።
ወንጀጣ ቀበሌ ከቡና በተጨማሪ ጫትና ሙዝም የነዋሪዎች ገቢ ማግኛ ሆኖ ያገለግላሉ።
"ነገር ግን ውጤት እያየንበት የነበረው በቡናና ማንጎ ላይ ነበር። አሁን ይህ 'ፈንገስ' መጣብነ እንጂ።"
ያብባል በተለይ የማንጎ ተክል ኑሮን በመደጎም ረገድ ለወንጀጣ ቀበሌ ነዋሪዎች አቻ እንዳልነበረው ይናገራል።
"በተለይ ማንጎ የዋህ ተክል ነበር። በሳር መሀል በቅሎም ታገኘዋለህ። ብዙም ተንከባከቡኝ አይልም። አንድ ማንጎ 3 እና 4 ብር ነው የሚሸጠው። ጥሩ ገቢ ያመጣልን ነበር። ይሄ ነገር በአስቸኳይ መፍትሄ ካልተፈለገለት ችግር ላይ ሊጥለን ይችላል" ሲል ስጋቱን ይገልጻል።
ቡናው ላይ የሚታየው በሽታስ ምን ይሆን?
ዓለሚቱ ጓዴም በባሕር ዳር ዙርያ የወንጀጣ ቀበሌ ነዋሪ ናት።
እሷም ለቢቢሲ እንደተናገረችው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በማሽላ፣ በጫት፣ በማንጎና በቡና ተክሎች ላይ ምንነቱ ያልታወቀ ፈንገስ እየወጣባቸው ይገኛል።
በተለይ በቡና ተክል ላይ ጉዳቱ የከፋ እንደሆነ ዓለሚቱ ትገልጻለች።
"በመጀመርያ ቅጠሉ ይደርቃል። ፍሬ ካፈራ በኋላ ደግሞ ፍሬውን የሚወጋው ነገር አለ። በፈንገሱ የተጠቃው ቡና ያፈራው ፍሬ ውስጡ ነጭ ሳይሆን ጥቁር ይሆናል" ትላለች።
"ይሁን ብለን ከክተን ስናበጥረው ጨርሶ የሆነ የማናውቀው ነገር ይሆንብናል። ቡናውን ገና ሳንለቅመው እዚያው ረግፎ ይቀራል። እኔ ቡና እንዲህ ሲሆን በሕይወቴ ገጥሞኝ አያውቅም።"
ዓለሚቱ ነገሩን ለግብርና ባለሙያዎች አሳውቃ ከሆነ በሚል ለጠየቅናት ጥያቄ ይህን ብላለች።
"የግብርና ባለሙያዎች አልፎ አልፎ የሚሰጡት ድጋፍ አለ። ብዙውን ጊዜ ትኩረት የሚሰጡት ግን ለማሽላና ለዳጉሳ ነው። የውጭ ሰብል ላይ ነው ትኩረታቸው። የሚረጭ ነገር እንደዚህ እንክብካቤ ይሰጣሉ። ለቡና ግን እስተዚህም ነው" ትላለች።

የፎቶው ባለመብት, Thinkstock
በአማራ ክልል የግብርና ባለሙያ የሆኑት አቶ ይበልጣል ስለ ችግሩ አንስተንላቸው በዘጌ ቡና ላይ የተከሰተው የቡና ፍሬ በሽታው ወይም በእንግሊዝኛው ስሙ (Coffee Berry disease) እንደሚባል ነግረውናል።
ይህ በሽታ ቡና ላይ ሲከሰት አዲስ ነገር አለመሆኑና ከዚህ በፊትም በተደጋጋሚ የሚያጋጥም የተለመደ በሽታ መሆኑን በአጭሩ አብራርተው ይህንንም የበሽታውን ምንነት ለነዋሪዎቹ እንደተነገራቸው ለቢቢሲ ገልጠዋል።
ይህ በሽታ በአበባ ወቅት ቀደም ብሎ ከተሰከተ አጠቃላይ የቡና ፍሬውን ሊገድለውና ሊያረግፈው ይችላል ይላሉ።
የቡና ተክሉ በሽታውን ሊቋቋምና ሊቀጥል ቢችል እንኳን ምርቱን መቀነሱ እንደማይቀር ለቢቢሲ አብራርተዋል።
በተለይም ጥላው ከፍተኛ በሆነበትና የአየር እርጥበቱ ከፍ ባለበት እንደ ዘጌ ያለ አካባቢ ጉዳቱ ከፍተኛ እንደሚሆንም ጨምረው ገልጠዋል።
ይህ የቡና ተክል በሽታ ወደ ኢትዮጵያ ከገባ ረዥም ጊዜ ማስቆጠሩን የጠቀሱት አቶ ይበልጣል፣ አማራ ክልል ውስጥ ከተከሰተ ግን አራት ዓመታት ግድም እንደሆነው ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በሽታው ያደረሰው ጉዳት ምን ያህል እንደሆነ ጥናት እንዳልተሠራ ያስረዱት አቶ ይበልጣል መፍትሄው ቀላል እንዳልሆነ ነግረውናል።
በከፊል ችግሩን ለመቅረፍ የቡና ተክልን አራርቆ መትከል አንዱ መፍትሄ ነው ይላሉ ባለሙያው።
ከዚህ ባሻገር ግን ይህን በሽታ የሚቋቋሙ ዝርያዎችን ማስተዋወቅ ወሳኝ መሆኑን ያሰምሩበታል።
ለዘጌ ቡና አምራቾች በአማራ ክልል ደረጃ ብቻም ሳይሆን ከጅማ ድረስ ተመራማሪዎችን በማምጣት ችግሩን በሚያቃልሉበት መንገድ ዙርያ ምክር እንደተሰጠ አቶ ይበልጣል ተናግረዋል።
በዘጌ የቡና አምራቾቹ ግን በዋናነት ከባለሙያዎች የሚጠብቁት የኬሚካል ድጋፍን ይመስላል።
"ሆኖም ባለሙያው በቡና ተክል ላይ የኬሚካል ርጭት ሐሳብ ብዙም አይመከርም፣ ይህንንም ለአብቃዮቹ ነግረናቸዋል" ይላሉ።
ኬሚካል ፈንገሱን የሚያጠፋው ከሆነ ለምን የኬሚካል ርጭት እንደማይመከር የተጠየቁት ባለሙያው አቶ ይበልጣል፣ "ቡና ለውጭ ገበያ የሚቀርብ ነው። በኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ሕግ መሠረት ቡና ላይ ኬሚካል አይረጭም ክልክል ነው" ብለዋል።
"ይረጭ እንኳ ቢባል ኮሎትሪከም ፈንገስን ለመከላከል የሚውሉ ኬሚካሎች አገር ውስጥ የሉም አይገባምም፤ ቢኖሩም ግን ርጭት እንዲደረግ አይመከርም፣ በፍጹም" ይላሉ።
ለቡና ፍሬ በሽታ ተብሎ ኬሚካል ወደ ኢትዮጵያ የገባበት አጋጣሚ እንደማያስታውሱ በማውሳት። ኢትዮጵያ ቡና ከውጭ እንደማታስገባው ሁሉ መድኃኒትም ለዚህ በሽታ አታስገባም ብለዋል።
አቶ ይበልጣል እንደሚያምኑት ይህ አሁን ዘጌ ቡና ላይ የሚታየው ፈንገስ ኬሚካል ቢረጭም በሽታውን አያድነውም። ይህም የሚሆንበት ምክንያት ኬሚካል አንድ ማሳ ላይ ቢረጭም ከቅርብ ማሳ ፈንገሱ በቀላሉ ይሰራጫል ይላሉ።
ታዲያ የዘጌ ቡናን ለመታደግ የሚሻለው ምንድነው?
አቶ ይበልጣል አሁን ያለው አመራጭ የቡና ተክል አስተዳደሩን ማስተካከል፤ ጥላውን መቀነስ እና የተሻሻሉ ዝርያዎችን እንዲተክሉ መምከር ነው ይላሉ።
ከሁሉም በላይ ደግሞ መስኖ ወደ ዘጌ እንዲገባ ማድረግ ጊዜ ሊሰጠው አይገባም ባይ ናቸው።
"የዘጌ ዝርያ እጅግ የሚፈለግ የቡና ዝርያ ነው" የሚሉት ባለሙያው በችግኝ ጣቢያም ቢሆን እሱን እያባዛን ነው የምንሰጣቸው። የአካባቢ [ኢንዲጂኒየስ] ዝርያ ነው። በሽታ በመቋቋም ግን የሚመረጥ ዝርያ አይደለም" ሲሉ ያስረዳሉ።
ይህ በዘጌ የቡና ተክል ላይ የተከሰተው በሽታ እዚያው አማራ ክልል ውስጥ በአዊና በምዕራብ ጎጃምም ከዚህ ቀደም ተከስቶ ያውቃል።
ሆኖም በዚያ አካባቢ የተሻሻሉ ዝርያዎችን በመጠቀም ችግሩን መቋቋም ተችሏል።
በዘጌ ይህን ማድረግ ለምን አልተቻለም?
"በዘጌ ቡና አብቃዮች ዝርያውን እንደ ውርስ ከቤተሰብ የመጣ አድርገው ስለሚወስዱት ማጥፋት አይፈልጉም። አያያዙም ደካማ ነው" ይላሉ አቶ ይበልጣል።
መስኖ ውሃ መጠቀም በሽታው ዘግይቶ እንዲደርስ ያደርጋል። ቡና በዘጌ በጥላ ውስጥ ነው የሚበቅለው። ለፀሐይ ቡናውን ማጋለጥም ሌላ መፍትሄ ነው። ይህ ዘዴ ጥላ የማሳሳት ዘዴ ይባላል።
ሌላው እንደ መፍትሄ የሚታየው ደግሞ በሄክታር ላይ ያለን የተክል ቁጥር መመጠን ነው።
"በአንድ ሄክታር የተክል ቁጥር ከ2ሺ 400 ባይበዛ ይመረጣል" ይላሉ ባለሙያው።
የሆነው ሆኖ የዘጌ ቡናን የሚታደግ መፍትሄ ይኖር ይሆን?
"ከኢትዮጵያ የቡና ዝርያዎች የዘጌ ቡና ምርቱ ዝቅተኛ ቢሆንም ጣዕሙ በጣም ጥሩ ነው። ቀደምት ዝርያም ነው" የሚሉት አቶ ይበልጣል፣ ከተጠቀሱት መፍትሄዎች ውጪ ግን ቡናውን ሊታደግ የሚችል አማራጭ አለ ብለው አያምኑም።
የዘጌ ቡና አብቃዮች ግን የግብርና ባለሙያዎች አንድ መፍትሄ ይዘውላቸው እንደሚመጡ አሁንም በተስፋ ይጠብቃሉ።















