ከአሥመራ መጥቶ ባሕር ዳርን ያስዋበው ዘምባባ

የተንቀሳቃሹ ምስል መግለጫ, የባሕር ዳር መለያ የሆኑትን ዘምባባዎች ማን ተከላቸው?

አዛውንቱ አቶ ዋሴ አካሉ የባህር ዳር ከተማ ነዋሪ ሲሆኑ፤ የባህር ዳር ልዩ ምልክት የሆነውን ዘንባባ በመትከል እና በመንከባከብ ከፍተኛውን ድርሻ ተወጥተዋል።

አቶ ዋሴ ላበረከቱት አስተዋጽኦ የአማራ ብድርና ቁጠባ ተቋም (አብቁተ) ሁለት ክፍል ቤቶችን በራሳቸው ቦታ ላይ አሠርቶ እንዳስረከባቸው የአማራ ብዙሃን መገናኛ ድርጅት አስነብቧል።

አቶ ዋሴ ከጥቂት ወራት በፊት ከቢቢሲ ጋር ያደረጉትን ቆይታ ከዚህ በታች ይመልከቱ።

Presentational grey line
Ato Wase

የፎቶው ባለመብት, AMMA

ከ50 ዓመት በላይ በቆየው የሥራ ህይወታቸው በተለያዩ ሙያዎች ውስጥ አገልግለዋል። "ምን ያልሰራሁበት አለ መሃንዲስ ክፍል፣ እሳት አደጋ፣ የመንግሥት ካዝና መጠበቅ ያለሰራሁት አይገኝም" ይላሉ።

"...እሳት ሲነሳ መኪና የብረት ቆብ እና የብረት ዝናር አለ አጥፍተን እንመለሳለን ማታ የለም ቀን የለም" ሲሉ ያስታውሳሉ። በተጨማሪም የባህር ዳር የጽዳት እና አትክልት ኃላፊ በመሆንም አገልግለዋል።

በዚህ ወቅት ነው ባህር ዳር የምትታወቅበትን ዘንባባዎች ለመትከል እና ለመንከባከብ እድል ያገኙት። አቶ ዋሴ ስለዚህ ጉዳይ ከቢቢሲ አማርኛ ጋር ዘርዘር አድርገው አውግተዋል።

ስንት ዓመትዎ ነው?

95 ዓመቴ ነው።

ልጆች አዎት?

10 ልጆች ነበሩኝ 4 በህይወት የሉም።

የት የት ሠሩ?

ምን ያልሠራሁበት አለ መሃንዲስ ክፍል እሳት አደጋ ዘብ የመንግሥት ካዝና መጠበቅ ያለሰራሁት አይገኝም። እሳት ሲነሳ የብረት ቆብ እና የብረት ዝናር አለ አጥፍተን እንመለሳለን፤ ማታ የለም፣ ቀን የለም።

ምን ያህል ዓመት ሠሩ?

አሁን ጡረታ ነኝ በ55 ዓመቴ ጡረታ ወጣሁ። ብዙ ነበርን አብረን የምንሠራው። ከእኔ ጋር እነ ሙሼ ጸጋ፣ አበበ አላምረው፣ እነ አዲስ ያየህ. . . ምንኑን እቆጥረዋለሁ። አሁን 10 አይሞሉም [በህይወት] ያሉት።

አቶ ዋሴ አካሉ

እንዴት ነበር የባህር ዳር ዘንባባን የመትከል ሃሳቡ የመጣው?

የጽዳት እና አትክልት ኃላፊ ነበርኩ። ፊታውራሪ ሐብተማርያም [የባህር ዳር አስተዳዳሪ ነበሩ] መጥተው ባህር ዳርን ሲያስተዳድሩ የዘንባባ ችግኙን አስመጡት። በስምንት መኪና ነው ከአሥመራ የመጣው።

በዚያ ወቅት 50 ሰው በስሬ አሠራ ነበር። ዘንባባው ከዚህ [አጂፕ ከሚባለው የባህር ዳር ሰፈር] እስከ ኳስ ሜዳ ከኳስ ሜዳ እስከ ጢስ አባይ መንገድ ተተከለ።

ኋላ ሲደረጅ ከሥር ውሃ ይጠጣል፤ ማንም ቆሻሻ አይጥልበትም። በስር በስር እየሆነ ውሃ ይጠጣ ነበር። ሌላ ደግሞ በራሱ ቀይ የሚያፈራ ይሄን ሁሉ በደንብ እይዝ ነበር። ዛሬ ከተማይቱ ከተማ ሆነች።

መቼ ነው ዘንባባዎቹ የመጡት?

ዘንባባዎቹ በ1949 ዓ.ም ከአስመራ ነው የመጡት። ዘንባባውን ያከፋፈልኩበት መዝገብ እስካሁን ድረስ አለ። በወቅቱ የዘንባባዎቹ መተከል ሰዉ እንግዳ ሆኖበት ነበር። አሁን ግን ይኸው የባህር ዳር ከተማ ጌጥ ለመሆን በቅቷል። እኔ ወጣ ብዬ ሳየው ደስ ይለኛል። በተለይ በክረምት ወቅት በጣም ደስ ነው የሚለኝ። እንግዳ ነገር ነው፤ በጣም የሚያስገርም ነው።

መቼ መትከል ተጀመረ?

ከዛሬ 63 ዓመት በፊት ነው ዘንባባው እንደመጣ ወዲያውኑ ነበር መትከል የተመጀመረው። አስታውሳለሁ መትከል የተጀመረው ጥቅምት 01/1949 ዓ.ም ነበር።

በባህር ዳር ዋና መንገድ አካፋይ ላይ የተተከሉት ዘምባባዎች

እርስዎ ከሠራተኞቹ ጋር አብረው ይሠሩ ነበር?

ዋናው ማን ሆነና። አብሬ በል እንደዚህ ትከል፤ እንደዚህ አድርግ ውሃ ስጥ እል ነበር። ውሃ የሚሰጥ በነጋታው ነው። ይሄን ሁሉ የተከታተልኩት እኔ ነኝ፤ የሚተክሉትን ሃምሳ ሰዎች በሙሉ እኔው ነበርኩ የማስተባብረው።

በስር ስር ምግብ እየሰጠን አለ። አሁን ደግሞ ተረካቢዎች ጥሩ ይዘውታል። ወጣ ብዬ ሳየው በጣም ደስ ይለኛል። ከዚህ እስከ ኳስ ሜዳ ሲያዩት ደስ ሲል። የሚያልፍ የሚያገድመው እንዳንጋጠጠ ነው። የሚመጣው ባለስልጣን ጋዜጠኛ ሁሉ አመስግኖ መርቋት [ባህር ዳርን] ይሄዳል።

እኔ በዚያ ወቅት ሁሉንም ነገር ነበር የምሠራው። በህልምም በእውንም ይታየኛል። የማስበው ስለከተማዋ ጽዳት ነው። ለዚህ ሥራ የተሰጠን ምስክር ወረቀትም ነበረ ጠፋ እንጂ አሁን፤ ሁሉ ነገር ሲያልፍ ይገርማል። እርጅና መጣ ይህችን 95 ዓመት እንደምንም ብዬ ባልፋት ጥሩ ነው።

ፊታውራሪ ምን ይሉ ነበር?

ፊታውራሪ ይጠራሃል ይላሉ ሄጄ ጠጅ ጠጥቼ ጮማ በልቼ እመጣለሁ።

ምን ተደረገልዎ?

አሁን በዚህ ምክንያት ቤት ይሠራለት ተብሎ ሦስት ክፍል ቤት ተጀምሮልኛል።

ቤትዎስ ዘንባባ ተክለዋል?

ለቤቴ አልተከልኩም ለከተማው ነው እንጂ የተከልኩት።