ባህር ዳር፡ ዘመቻ 90 ደቂቃ

ባህር ዳር፡ ዘመቻ 90 ደቂቃ

ዘወትር ቅዳሜ ማልደው በአንድ ቦታ የተሰባሰቡ ወጣቶችን በባህር ዳር መመልከት የተለመደ ነገር ሆኗል። ወጣቶቹ ሰብበሰብ ብለው ከተነጋገሩ በኋላ በጋራ ሆነው ወደ አንዱ የከተማዋ ክፍል ያቀናሉ።

ያለፈውን ቅዳሜ ወደ ጣና ሐይቅ ካቀኑ፤ በዚህኛው ቅዳሜ ወደ ቀበሌ 4 የሚቀጥለውን ቅዳሜ ደግሞ ወደ ሌላኛው አካባቢ ይሄዳሉ።

መታገስ ገብረሚካኤል ወጣቶቹን ከሚያስተባብሩት እና ከተሳታፊዎቹ መካከል አንዱ ነው። "ቅዳሜ፣ ቅዳሜ ሁሌም ከጠዋቱ 1፡30 ላይ በመገናኘት ለከተማችን 90 ደቂቃ መድበን ብዙ የጽዳት ሥራ እየሠራን ነው።" ይላል ስለሳምንታዊ ሥራቸው ሲገልጽ።

እነመታገስ በአጋጣሚ በበጎ ፈቃድ የጀመሩት የጽዳት ዘመቻ አንድ ዓመት አልፎታል።

በባህር ዳር ከተማ አንድ የስዕል አውደ ርዕይ ይዘጋጃል። ዝግጅቱ በታሰበው መንገድ ተጀምሮ በስኬት ወደ መጠናቀቁ ይቃረባል።

የመዝጊያ ሥነ-ሥርዓቱ ግን በተለመደው መንገድ እንዲሆን አልተፈለገም። "ሃሳቡ ከአንድ ዓመት በፊት የስዕል አውደ ርዕይ መጨረሻ ላይ ጣናን እናጽዳ ተብሎ ተጀመር" ሲል በወቅቱ የነበረውን መታገስ ያስታውሳል።

በዚህም ወደ ጣና ሐይቅ በማቅናት ያለውን ቆሻሻ አጽድተው የስዕል አውደ ርዕዩ ተጠናቋል። ጥቂት የነበሩት ተሳታፊዎች ጣናን በማጽዳት የተጀመረው ሥራ እንዲቋረጥ አልፈለጉም። በየሳምንቱ ቅዳሜ በመገናኘት በተለያዩ የባህር ዳር አካባቢዎች በመንቀሳቀስ ማጽዳት ጀመሩ። በዚህም ሳምንታዊው የበጎ ፈቃድ የጽዳት ሥራ ተጀመረ።

"ባህር ዳር ከተማ ውብ ነች፤ ጽዱ ነች። አሁን ግን እንደቀድሞው አይደለችም። ጣንን በጀልባ እየቀዘፍን እና እየዋኘን ብዙ ላስቲኮች እና ቆሻሻዎችን እያወጣን ነው። ቆሻሻዎች አንድ ላይ በመሰብሰብ በመኪና ጭነን እያስወገድን ነው። በገንዘብ ሊተመን የማይችል ብዙ ቆሻሻ በበጎ ፈቃደኞች አማካይነት እየተነሳ ነው። ቁጥራችንም እየጨመረ ነው። ስንጀምር 10 አካባቢ ነበርን። አሁን ከፍተኛ ነው" ይላል መታገስ።

የጽዳት ዘመቻውን ለመለየት እንዲያመቻቸው አንድ ሁለት ሦስት. . . እያሉ ቅዳሜዎችን በመሰየም 90ኛውን ቅዳሜ አልፈዋል።

በጣም የቆሸሹ ስፍራዎችን አጽድተዋል። የእምቦጭ አረምን ነቅለዋል። ወጣቶቹ በብዛት የጽዳት ሥራውን የሚያከናውኑት በፋሲሎ ክፍለ ከተማ ነው። ወይዘሮ አሻገሩ አሊ የክፍለ ከተማው የአካበቢ ጥበቃ፣ ጽዳትና ውበት ተጠሪ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ናቸው።

ኃላፊዋ የወጣቶቹን ተግባር "በርካታ ለውጥ ያመጣ ነው" ሲሉ ይገልጹታል። "የከተማው የበጎ ፈቃደኞች ቡድን በብዛት የሚሠሩት በፋሲሎ ክፍለ ከተማ ነው። ይህ ደግሞ ከተማዋ እምብርት ነው" ነው ይላሉ።

"ብዙ ለውጥ አምጥተናል" የምትለው በጎ ፍቃደኛዋ አሳሱ ነች። አሳሱ "አካባቢያቸውን እናጸዳ እና ትምህርት እንሰጣቸዋለን። አብዛኛዎቹ ደግሞ ተግበራዊ ያደርጉታል" ስትል የበጎ ፍቃድ ሥራቸው ውጤታማነትን ታስረዳለች።

የባህር ዳር ከተማ ወጣቶች ከተማቸውን እያጸዱ
የምስሉ መግለጫ, የባህር ዳር ከተማ ወጣቶች በጽዳት ላይ

አቶ ዘላለም ጌታሁን የባህር ዳር ከተማ የአካባቢ ጥበቃ፣ ጽዳት እና ውበት ጽህፈት ቤት ኃላፊ ናቸው። "ወጣቶቹ በጣም የሚያስደስት ሥራ እያከናወኑ ናቸው። ትልቅ እና ለሌሎች ክፍለ ከተሞችም አርዓያ የሚሆን ሥራ እያከናወኑ ነው" የሚሉት አቶ ዘላለም ይህንን የወጣቶቹን ተግባር በመመልከት ሌሎች የከተማዋ ወጣቶችም አካባቢያቸውን በየሳምንቱ ማጽዳት መጀመራቸውን ያነሳሉ።

የወጣቶቹ አስተባበሪ ለሆነው መታገስ ይህ ብቻ በቂ አይደልም። "እኛ በከተማው ያለውን ቆሻሻ አጽድተን እንጨርሳለን ማለት አይደለም። ዋናው የእኛ ሥራ አዕምሮ ላይ መሥራት ነው። ሁሉም ቤቱን እና አካባቢውን ቢያጸዳ ከተማዋ ጽዱ ትሆናለች።" ይላል። መታገስ "ሰው በቆሻሻ ላይ ያለውን አመለካከት እስኪቀይር ድረስ፤ ቆሻሻን በአግባቡ እስክያሶግድ ድረስ ማጽዳታችንን እንቀጥላለን" ሲልም ያክላል።

አቶ መስፍን አድማሱ የባህር ዳር ከተማ ነዋሪ ሲሆኑ ይህንን የጽዳት ዘመቻ ዓላማ ተቀብለው ከወጣቶቹ ጋር በየሳምንቱ በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ። ጅምሩን ቢያደንቁም "ከከተማው የሚወጣው ቆሻሻ ብዙ ነው። የሚያጸዳው ግን አነስተኛ ነው" ሲሉ ስጋታቸውን ያስቀምጣሉ።

ይህንን የአቶ መስፍንን ስጋት ወይዘሮ አሻገሩ ይጋሩታል። "አሁንም የማህበረሰቡ የአመለካካት ችግር አለ። በተወሰኑ ክፍለ ከተሞች የሚያጸዱ ቢኖሩም ግንዛቤው አልተቀየረም"ይላሉ። ለበጎ ፈቃደኞቹ ከመንግስት እና ከግል ድርጅቶች ለጽዳት የሚያገለግሉ አነስተኛ የቁሳቁስ ድጋፍ ቢደረግም ይህ በቂ አይደለም ሲሉ ይገልጻሉ።

"የአካባቢ ጥበቃ እና የጽዳትና ውበት አብረውን ሊሠሩ ይገባል" የሚለው ደግሞ መታገስ ነው። "ጣና እየቆሸሸ ነው። ቆሻሻ ወደ ጣና እየተጣለ ነው። ሆቴሎችም ቆሻሻቸውን ወደ ጣና እየጣሉ ነው። ሌላ የቆሻሻ መጣያ ቦታ እስኪያዘጋጁ መጠየቃችንን እንጥላለን" ይላል።

"በጣም ደስ የሚለኝ ያለማንም አስገዳጅነት ያለክፍያ መሥራቴ ነው። ጊዜዬን እና ጉልበቴን ሳፈስ ደስ እያለኝ ነው። በበጎ ፈቃድ መሥራት ደስ ይላል" ትላለች አሳሱ። "በህይወት እስካለሁ እና ባህር ዳር ጽዱ እስካልሆነች ድረስ ሥራውን እቀጥላለሁ። ሌላም ቦታ ብሄድ መሳተፌን አላቆምም" ትላለች።

"ቅዳሜ ቅዳሜ ሁሌም እዚህች ከተማ እስካለሁ ድረስ ሌላ ፕሮግራም አይኖረኝም" የሚለው ደግሞ መታገስ ነው። "ትልቅ ነገር ለከተማዬ እንዳበረከትኩ ነው የሚሰማኝ። በጣም ደስ ብሎኝ ነው የምሄደው" ሲል ያጠቃልላል።