አዲሱ የታይፎይድ ክትባት ውጤታማ ነው ተባለ

የፎቶው ባለመብት, Gates Archive/Samantha Reinders
አዲስ የተሰራው የታይፎይድ ክትባት 'በሚያስገርም ሁኔታ' እየሰራ እንደሆነና አስቸጋሪውን በሽታ ለመግታት ትልቅ ተስፋ የተጣለበት እንደሆነም ዶክተሮች ገለጹ።
እስካሁን የሙከራ ክትባት በተሰጠባቸው አካባቢዎች ከ 80 በመቶ በላይ ውጤታማ መሆኑ ታውቋል። የዘርፉ ባለሙያዎች እንደገለጹት ክትባቱ አስገራሚ ለውጥ ሊያመጣ የሚችልና በመላው ዓለም በበሽታው የሚሞቱና የሚጎዱ ሰዎችን ቁጥር በእጅጉ ይቀንሰዋል።
በአሁኑ ሰአት የመጨረሻ ሙከራዎች እየተደረጉ ሲሆን መድሃኒቶችን የተላመደ ታይፎይድ በእጅጉ በተንሰራፋባት ፓኪስታን ዘጠኝ ሚሊየን ህጻናት ክትባቱ እየተሰጣቸው ይገኛል።
ታይፎይድ 'ሳልሞኔላ ታይፊል ባክቴሪያ' በተባለ በፍጥነት የመተላለፍ አቅም ያለው ባክቴሪያ የሚተላለፍ ነው። በበሽታው በተበከለ ምግብና ውሃ ከታማሚዎች ወደ ጤነኛ ሰዎች ይተላለፋል።
የበሽታው አንዳንድ ምልክቶችም፡
- ለረዥም ጊዜ የሚቆይ ትኩሳት
- የራስ ምታት
- ማጥወልወል
- የምግብ ፍላጎት ማጣት
- የሆድ ድርቀት
ስለታይፎይድ እስካሁን በቂና አስተማማኝ መረጃ ማግኘት ባይቻልም በዓመት ከ11 እስከ 21 ሚሊየን የሚደርሱ ሰዎች በበሽታው የሚጠቁ ሲሆን ከ128 ሺ እስከ 161 ሺህ የሚደርሱት ደግሞ ህይወታቸውን ያጣሉ ተብሏል።
በኔፓል ካትማንዱ ሸለቆ የሚኖሩ እድሜያቸው ከዘጠኝ ወር እስከ 16 ዓመት የሚደርሱ 20 ሺ ህጻናትም የሙከራ ክትባቱን አግኝተዋል። በዚህ አካባቢ ታይፎይድ ወረርሽኝ በሚባል ደረጃ የተሰራጨ ሲሆን ትልቅ የጤና እክል ከሆነም ቆይቷል።
ክትባቱ ከተሰጣቸው ህጻናት መካከል ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ላይ የበሽታው ምልክት 81 በመቶ መቀነሱን ተመራማሪዎቹ የሰሩት ጥናት ይጠቁማል።
ክትባቱ ከኔፓል በተጨማሪ በማላዊ እና ባንግላዲሽም በሙከራ ደረጃ እየተሰጠ ሲሆን፣ ምን ያክል በሽታውን ተከላክሎ ይቆያል የሚለው በቀጣይ ሙከራዎች የሚታወቅ ይሆናል።
የዓለም ጤና ድርጅት በቅርቡ እንደገለጸው ታይፎይድ አብዛኛዎቹን መድሃኒቶች እየተላመደ በመምጣቱ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል።


















