በኢትዮጵያ የኮሌራ ወረርሽኝ አሳሳቢ በመሆኑ ክትባት መሰጠት ተጀመረ

ሃይቲ ውስጥ በኮሌራ ተይዛ ህክምና የሚደረግላት ህጻን

የፎቶው ባለመብት, Reuters

በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች በተከሰተ የኮሌራ ወረርሽኝ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከ600 በላይ መድረሱን ተከትሎ የኮሌራ ክትባት መሰጠት ተጀምሯል።

ክትባቱ የሚሰጠው ለበሽታው ተጋላጭ ናቸው ተብለው ለሚታሰቡ አዲስ አበባ ውስጥ ለሚገኙ አረጋውያን፣ የህፃናትና ወጣቶች ማገገሚያ ማዕከላት የሚኖሩ ሰዎች መሰጠት እንደተጀመረ የጤና ጥበቃና የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ገልጿል።

ኮሌራ ምንድን ነው?

የኮሌራበሽታ የሚተላለፈው ኮሌራ ቪብሮ ኮሌሬ በተባለ ባክቴሪያ ሲሆን የተበከሉ ምግቦችንና መጠጦች በመመገብና በመጠጣት የሚከሰት ነው። በባክቴሪያው በተበከሉ ምግቦችና መጠጦች በቀላሉ በሽታው ይተላለፋል።

በተለይ በባክቴሪያው የተጠቃ ሰው አይነ ምድር፣ ምግብንና ውሃን በቀላሉ ይበክላል።

ባክቴሪያው ወደ ሰውነት ከገባ በኋላ አስፈላጊው ሕክምና በአስቸኳይ ካልተደረገ አጣዳፊ ተቅማጥና ትውከትን በማስከተል፤ ከፍተኛ ፈሳሽን ከሰውነታችን እንዲወጣ በማድረግ እስከሞት የሚያደርስ በሽታ ነው።

ምልክቶቹ

አብዛኞቹ በኮሌራ ባክቴሪያ የተጠቁ ሰዎች የበሽታው ምልክቶች ላይታይባቸው ይችላል። ሌሎቹ ግን አጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት ያጋጥማቸዋል። በዚህም ሳቢያ ከፍተኛ መጠን ያለው የሰውነት ፈሳሽ ስለሚያወጡ ክፉኛ ይዳከማሉ። በተጨማሪም ክንድና እግሮች ላይ ሕመም እንዲሁም የሆድ ቁርጠት ያጋጥማል።

በሽታውን ለመከላከል

ንጽህንው የተጠበቀ ውሃ መጠቀም

ለማንኛው አገልግሎት በተቻለ መጠን ንጽህናው የተጠበቀ ውሃ መጠቀም ዋነኛው የበሽታው መከላከያ መንገድ ነው። የታሸገ፣ ፈልቶ የቀዘቀዘና አስተማማኝ የውሃ ማከሚያ መድሃኒቶችን መጠቀም ተገቢ ነው።

እጅን አዘውትሮ መታጠብ

ምግብ በማዘጋጀት ጊዜ፣ ምግብ ከመመገብ በፊት፣ ሕጻናትን ከመመገብ በፊት፣ መጸዳጃ ቤት መልስ፣ የሕጻን ልጅዎን ካጸዳዱ በኋላና በተቅማጥ የተጠቃ ሰውን እርዳታ ካደረጉ በኋላ እጅን በአግባቡ በሳሙና መታጠብ ያስፈልጋል።

በተገቢ ቦታዎች መጸዳዳት

ዘወትር መጸዳቻ ቤት መጠቀም፤ የመጸዳጃ ቤት በሌለባቸው ቦታዎች ከወንዞችና ከመሰል የውሀ አካላት በመራቅ ለመጸዳጃነት በተቆፈረ ጉድጓድ ውስጥ መጸዳዳት።

ምግቦች ላይ መጠንቀቅ

ወረርሽኝ ባለባቸው አካባቢዎች ምግቦችን አብስሎ ሳይቀዘቅዙ መመገብ የሚመከር ሲሆን እንዲሁም ምግቦችን ከተመገቡ በኋላም ሆነ ከመመገብዎ በፊት ሸፍኖ ማስቀጥ ይመከራል። በተጨማሪም አትክልትና ፍራፍሬዎችን በሚገባ አጥቦና ልጦ በመመገብ ራስን ከኮሌራ መከላከል ይቻላል። በጥሬው የሚበሉ ምግቦችን አለመመገብ ሁል ጊዜም የሚመከር ጉዳይ ነው።

ንጽሕናን መጠበቅ

በቤት ውስጥ የምግብ ማብሰያና የመታጠቢያ ቤቶችን ንጽህና በአግባቡ መጠበቅ፣ የመጠጥ ውሃ የሚቀመጥባቸውና የሚቀርብባቸውን እቃዎች ንጽህና መቆጣጠር፣ ቆሻሻን በአግባቡ መያዝና የአካባቢን ንጽህና መጠበቅ በባለሙያዎች ዘወትር የሚመከር አንዱ መከላከያ መንገድ ነው።

ክትባት መውሰድ

የኮሌራ ክትባት በአፍ በጠብታ መልክ የሚሰጥ ሲሆን አንድ ዓመት ከሆናቸው ህጻናት ጀምሮ መከተብ ይችላሉ። ክትባቱ ለአምስት ዓመታት በሽታውን ለመከላከል ያስችላል።