ኢትዮጵያ፡ አካል ጉዳተኛው የቴኳንዶ ስፖርት አሰልጣኝ
ከማል ቃሲም የተወለደው ጎንደር ከተማ ነው። በህጻንነቱ ከቤተሰቦቹ ጋር በመሆን ወደ ወረታ አመሩ።
"ተጫዋችና ደስተኛ" ነበርኩ የሚለው ከማል በአምስት ዓመቱ የገጠመው አደጋ ህይወቱን እስከወዲያኛው ቀይሮታል።
"ጉዳት የደረሰብኝ በ1985 ዓ.ም ነበር። ወረታ ውስጥ ከእኩዮቼ ጋር ስጫወት በመንግሥት ሽግግር ወቅት ከአገልግሎት ውጪ ሆኖ በተተወ ታንክ ነው ጉዳት የደረሰብኝ።"
በወቅቱ የአምስት ዓመት ታዳጊ የነበረው ከማል ታንኩ ላይ እየተጫወተ ሳለ "አፈሙዙን በሚያሽከረክረው ክፍተት መሐል አንድ እግሬ ሆኖ ለመሻገር ስሞክር አንደኛው እግሬ አፈሙዝ ስር ገባ። በዚያው ቅጽበት አፈሙዙ በሚዞርበት ጊዜ እግሬ ላይ አደጋው ደረሰ" ሲል ያስታውሳል።
ከወረታ ወደ ባሕር ዳር ለህክምና ተወስዶ ለወራት እዚያው ከቆየ በኋላ ወደቀየው ተመለሰ። በድንገተኛው አደጋ ጉዳት የደረሰበት ታዳጊው ከማል ከህክምናው ሲመለስ ቀኝ እግሩ ጉልበቱ ላይ ተቆርጦ በሁለት ምርኩዞች ተደግፎ ነበር።
"ህይወት እንደ አዲስ ተጀመረ። ያኛው ሌላ አሁን ደግሞ ሌላ ህይወት" የሚለው ከማል "በአካባቢያችን ሌላ አካል ጉዳተኛ አልነበረም። እንኳን በዚያ ወቅት አሁን እንኳን ማኅረሰቡ ውስጥ ስለአካል ጉዳተኝነት ያለው አመለካከት ፈታኝ ነበር። መውጣት መግባት መጫወት አልችልም ነበር" ይላል።
በታዳጊነቱ በደረሰበት አደጋ አካል ጉዳተኛ የሆነው ከማል ተደራራቢ ችግሮችን መጋፈጥ ጀመረ። ሌላ ችግር ቤተሰቡ ውስጥ ተከሰተ፤ አባት እና እናቱ ተለያይተው በተለያየ ቦታ በየፊናቸው ህይወታቸውን ለመምራት ሲወስኑ፤ እሱም ከእናቱ ተለይቶ ከአባቱ ጋር መኖር ጀመረ።
አደጋው ከደረሰበት በኋላ ከማል ሰባት ዓመት ሲሆነው ወደ ትምህርት ቤት መሄድ ጀመረ። ነገር ግን "ሙሉ ለሙሉ ህይወቴ ስለተቀየረ ትምህርት ቤት እረብሽ፣ እነጫነጭ ነበር" ሲል በጸባዩ ላይ ለውጥ መከሰቱን ያስታውሳል።
ለአካል ጉዳተኞች የሚመች መሠረት ልማት አለመኖር እና ህብረተሰቡ ስለ አካል ጉዳተኝነት ያለው አስተሳሰብም ህይወቱን ከባድ አድርጎት ነበር።
"ከባድ ነው። ትምህርት ቤት ነጻ ሆኜ መጫወት አልችልም። ትልልቆቹም ባለፍኩ ባገደምኩ ቁጥር ከንፈር መምጠጥ፤ በዚህ እድሜው እንደዚህ ሆኖ እያሉ ሲናገሩ መስማት ተስፋ ያስቆርጣሉ" ይላል።
በሁለት ክራንች መንቀሳቀስም መጫወትም አልመችህ ሲለው አንዱን ክራንች በመተው እንደልቡ ለመሆን ሞከረ። በዚህም ለመንቀሳቀስ በሚያደርገው ሙከራ በተደጋጋሚ በመውደቅ እግሩ መጎዳት እና መድማት ይገጥመው ጀመር።
በዚህ መልኩ እስከ ስድስተኛ ክፍል ወረታ ውስጥ ተማረ። በወቅቱ "ጸባዬ አስቸጋሪ እረባሽና አልቃሻ ሆኜ። ከባድ ጊዜ ነበር ያሳለፍኩት። ከልጆች ጋር ጋር መግባባት እየተቸገርኩ እጣላ ነበር። አንዳንድ ጊዜም በክራንች እስከመማታት እደርስ ነበር" የሚለው ከማል 6ኛ ክፍል ሲደርስ ወደ እናቱ ተመልሶ ጎንደር መኖር ጀመረ።
ጎንደር ሌሎች የአካል ጉዳተኞችን ተዋወቀ ስለዚህም ከወረታ ብቸኝነቱ በተወሰነ ደረጃ ተላቀቀ። ነገር ግን እናቱ ሥራ ስላልነበራቸው የሚያስፈልጋቸውን ድጋፍ የሚያገኙት አንድ አካል ጉዳተኞችን ከሚረዳ ድርጅት ነበር።
"ለአካል ጉዳተኞች የሚሰጠውን ስንዴ እና ዘይት በችግር ላይ ለነበረችው እናቴ አመጣላት ነበር። እዚያ ሌሎች አካል ጉዳተኞችን ባገኝም ጥሩ ስሜት አይሰማኝም ነበር። የዝቅትኝነት ስሜት ይሰማኝ ጀመር" የሚለው ከማል 'ረጂ እንጂ ተረጂ አልሆንም' ብሎ እርዳታውን መቀበል አቆመ።

የፎቶው ባለመብት, BBC Sport
ስምንተኛ ክፍል ደርሶ ለማለፍ የሚያስችለውን ውጤት ባለማምጣቱ ለመድገም ተገደደ። በቀጣዩ ዓመት ደግሞ ሠው ሠራሽ እግር ለማሠራት ወደ ደሴ አምርቶ ለወራት እዚያው በመቆየቱ ስምንተኛ ክፍልን በማታው ክፍለ ጊዜ መማር ጀመረ።
የማታ ተማሪ መሆኑ እንዲሁም ቀን ላይ የሚሰራው ነገር ስላልነበረው አጋጣሚው ከቴኳንዶ ስፖርት ጋር እንዲተዋወቅ ዕድል ፈጠረለት።
ከጓደኛው ጋር ቴኳንዶ የሚሰራበት ቦታ በመሄድ ስፖርቱን የተመለከተው ከማል፤ ለሰዓታት ከተመለከተ በኋላ አንዳች ነገር ውስጡ ተፈጠረ። ከማልን የተመለከተው የቴኳንዶ አሰልጣኙ ስሜቱን ጠይቆት ፍላጎት ካለው በነጻ እንዲማር ስለፈቀደለት በቴኳንዶ ፍቅር ወደቀ።
"እየወደቅኩ እየተነሳሁ ከምንም በላይ በአስተማሪዬ ድጋፍ እና በጓደኞቼ አይዞህ ባይነት ቴኳንዶውን መለማመድ ቀጠልኩ" ነገር ግን በዙሪያው ካሉ ሰዎችና ከቤተሰቡ ጭምር 'ምን ያደረግልሃል?' ይሉት ነበር።
ሆኖም እንዳሰበው ቀላል አልነበረም። ከወላጆቹ በስተቀር ሁሉም 'ምን ሊያደርግልህ?' የሚል ጥያቄ እያቀረቡ ተስፋ አስቆራጭ አስተያት ሰጥተውታል።
"በአንድ እግር ቴኳንዶ ከባድ ነው። ወድቄ እሰበራለሁ። እጄን ተሰብሬያለሁ። የቀረችውን አንድ እግሬን ተሰብሬ 2 ወር በተኛሁበት ጊዜ የነቀፉኝ ሰዎች ደስ አላቸው። እኔ ግን እስከ ህይወቴ ፍጻሜ ስፖርቱን ከመሥራት ማንም እንደማያግደኝ አወቅኩኝ።"
ከማል ቴኳንዶ መጀመሩ ብዙ ነገሮችን እንዲለውጥ ምክንያት ሆኖታል። አንደኛው ደግሞ ክራንቹን የሚጠቀምበትን ዘዴ መቀየሩ እና በሚመቸው መንገድ እንዲያስተካክለው ማድረጉ ነው።
"ክራንቹ መጀመሪያ ላይ ብረት ብቻ ነው። ቴኳንዶ ይህንን ምቹ እንዳደርግ ረድቶኛል። ይኸውም እንደጫማ ምቹ አድርጌ እንድሠራ አድርጎኛል። እንደጀመርኩ እግሬን ሳነሳ ክራንቹ ተሰብሮ ወድቄያለሁ። ሳስተምርም ወደቄ አውቃለሁ። የውሃ ቱቦ ነው በየጊዜው ቼክ አደርገዋለሁ። በየጊዜው እቀይረዋለሁ አሁን በምቾት እሠራለሁ።"
ቴኳንዶ በተለያዩ የቀበቶ ቀለሞች የሚሰጡ ደጃዎች አሉት። ጀማሪዎች በነጭ ቀበቶ ይጀምራሉ። ቢጫ፣ አረንጓዴ፣ ቀይ እና ጥቁር።
እነዚህን ቀበቶዎች አንድ ሰልጣኝ የተለያዩ የስልጠናዎችን ካጠናቀቀ በኋላ ከአሰልጣኙ የሚያገኘው ይሆናል። ከዚያ በኋላ ደግሞ በዲግሪ የሚገለጹና ዳን የሚባሉ ዘጠኝ ደረጃዎች አሉ። ዳን የሚሰጠው በአሰልጣኝ ሳይሆን በቴኳንዶ ማኅበራት የተግባርና የጽሁፍ ፈተና ሲታለፍ ከኮሪያ የሚሰጥ ነው።
"ወደ ሦስተኛ ዳን ዲግሪ ደርሻለሁ። የሚሻሻሉ ዲግሪዎች ናቸው። አሁን 3ኛ ዳን አለኝ። በዚህ ዓመት አራተኛውን ላገኝ እችላለሁ። ጊዜው ደርሷል" ይላል ከማል በቴኳንዶ የደረሰበትን ደረጃ ሲገልጽ።
"ለእኔ ሲባል ምንም የተለየ የሚደረግልኝ ነገር የለም" የሚለው ከማል በዚህ ሂደት ውስጥ ሁሉ የተለያዩ ጉዳቶች ቢገጥሙትም ወደኋላ አላለም።
ሦስተኛ ዳን የፈተኑት የውጭ አገር ሰዎች እንደነበሩ የሚኣስታውሰው ከማል፤ የሚተበቅበትን ካከናወነ በኋላ ፈታኞቹ ቆመው እንዳጨበጨቡለት ይናገራል።
"የተፈተንነው 15 ነበርን፤ ስድስቱ ወደቁ። ዘጠኛችን አለፍን። የእኔ ውቴት ጥሩ ነበር። ቴኳንዶ የሚጠይቀውን የሥራ የፓተርን ሙሉ ሠርቼ ነው ያገኘሁት" ነው በማለት ተወዳድሮ ፈተና በማለፍ አሁን ላለበት መብቃቱን ይጠቅሳል።
ከማል ቴኳንዶን ለሌሎች ማስተማር በሚያስብበት ጊዜ አካል ጉዳተኛ የቴኳንዶ አስተማሪ ስለሌለ 'ይሳካልኝ ይሆን?' እያለ ጥርጣሬ ቢገባውም የጓደኞቹና የአስተማሪው ማበረታቻ ድጋፍ ሆኖት በ2002 ዓ.ም ወረታ ውስጥ የማስተማሪያ ማዕከል ከፍቶ ማስተማር ጀመረ።
ሆኖም እንዳሰበው ቀላል አልነበበረም። ለማስተማር የሚረዳውን ፈቃድ አላገኘም። መንቀሳቀሻ የሚሆን በቂ ገንዘብ እጁ ላይ አልነበረውም። ለመንቀሳቀሻ የሚሆን ገንዘብ ለማግኘትም ፎቶውን አስር አስር ብር ሸጦ ወደ ሁለት ሺህ ብር ገደማ ሲያገኝ ሥራውን ጀመረ።

"ማስታወቂያ ስለጥፍ ግራ ገባቸው። 'ማነው የሚያስተመረው አሉኝ?' ሰዉ ለመማር ፈቃደኛ አልሆነም። የማውቃቸውን ጠርቼ በነጻ ማሠራት ጀመርኩኝ። አዳራሽም ዘመድ ፈቀደልኝ። አራት ወይም አምስት ሰው ይዤ ስሠራ ሌላው ሰው አዳራሽ ሞልቶ ያይ ነበር" ይላል።
ከዚያም ሰልጣኞች መምጣት ሲጀምሩ ፈቃድ ማውጣት ስለነበረበት ወደ አዲስ አበባ ሄዶ በመፈተን በተግባርና በጽሑፍም አንደኛ በመውጣት ፈቃድ ማግኘቱን ይናገራል። ከስድስት ወር የቴኳንዶ ስልጠና በኋላ 40 ተማሪዎችን ለመጀመሪያ ጊዜ አስመረቀ።
የተለያዩ ፈተናዎችና ውጣ ውረዶች የገጠሙት ከማል ቃሲም ከወራታ ፓዌ ከዚያም ወደ ባሕር ዳር በመሄድ ስልጠና ሰጥቷል።
በ2007 ዓ.ም ላይ አዲስ አበባ በተዋወቀው አንድ የውጭ አገር ዜጋ አማካይነት ባገኘው ድጋፍ ወደ ጀርመን በመሄድ ሰው ሠራሽ እግር ሲሰራለት በዚያውም የአንድ ወር ስልጠና አግኝቷል።
ከማል ለዓመታት በዘለቀው የቴኳንዶ ስፖርት ህይወቱ የተለየ ደስታ የፈጠረለትን አጋጣሚ "የመጀመሪያዋውን ጥቁር ቀበቶ ስቀበል ነው" ሲል ያስረዳል።
ባለትዳር እና የልጅ አባት የሆነው ከማል በቀጣይ ለቤተሰቡ "ጥሩ ነገር መስጠት" እንዲሁም የቴኳንዶ ስልጠና ሥራውን የበለጠ የማጠናከር አላማ አለው።
ከዚህ በተጨማሪም በግል ህይወቱ ዙሪያ መጽሐፍና ዘጋቢ ፊልም ማዘጋጀት ይፈልጋል።
አሁንም ብዙዎች ቴኳንዶ መሥራቱን እንደሚጠራጠሩ የሚናገረው ከማል "ለሰዎች ፎቶዬን ሳሳያቸው በፎቶ ጥበብ የተዘጋጀ ነው ይሉኛል። እኔም ወስጄ በተግባር እሰራሁ አሳያቸዋልሁ።"
በቴኳንዶ ስፖርት ከ15 ዓመት በላይ የቆየው ከማል በወረታ፣ በፓዌ እና በባሕር ዳር በሺህ የሚቆጠሩ ወጣቶችን አሰልጥኗል። በተጨማሪም በዘርፉ ውድድር ባይኖርም የተለያዩ መድረኮች ላይ ትዕንቶችን በማቅረብ ሽልማቶችን አግኝቷል።
በመላው ኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች በሚሳተፉበት የፓራሎምፒክ ውድድር ላይ ደግሞ የአማራ ክልልን በመወከል በጦርና አሎሎ ውርወራ፤ በተሽከርካሪ ወንበር እንዲሁም ክብደት ማንሳት ተሳትፎ ከሃያ በላይ ሜዳሊያዎችን አጥልቋል።
በቅርቡ በተመሠረተው የተሸከርካሪ ወንበር የቅርጫት ኳስ ውድድርም ተሳታፊ በመሆን ላይ ይገኛል።
ከስፖርቱ ጎን ለጎን ከማል ቃሲም የተሽከርካሪ ወንበር ተጠቃሚዎችና የእግር አካል ጉዳተኞች ማኅበር ሊቀ መንበር በመሆን ያለውን ልምድ በማካፈል ላይ ይገኛል።

















