አካል ጉዳት፡ በርካታ አካል ጉዳተኞችን ከዊልቸር ላይ ያነሳው ኢትዮጵያዊ

አቶ ሰለሞን የሰው ሰራሽ እግር ከሠራላቸው ሰዎች ጋር

በተፈጸመበት ሰቆቃ ሁለት እግሮቹን ያጣው ከፍያለው ተፈራ "መጀመሪያ ተኩስ ሲከፍቱብን 3 ልጆች ወዲያው ሞቱ። እኔ አንድ እግሬ ወዲያው ተቆረጠ፤ ቀኝ እግሬን ደግሞ ያለፈቃዴ ከቁርጭምጭሚቴ ከፍ ብለው ቆረጡት።

በቃሊቲ በእስር ላይ እያለሁ በጣም ያመኝ ነበር። መሞት እፈልግ ነበር፤ ግን አልቻልኩም። መፀዳጃ ቤት መሄድ ስፈልግ እጄን ይዘው ይወረውሩኝ ነበር" ይላል።

አሁን ግን ከፍያለው ቆሞ መራመድ ችሏል።

* * * *

ኮሎኔል ለገሰ ተፈራ በኢትዮ-ኤርትራ የድንበር ጦርነት ወቅት በግንባር ተሰልፈው ተዋግተዋል። በዚህም ጊዜ ከጦርነቱ ሙሉ አካላቸውን ይዘው አልተመለሱም። ጉዳት አጋጠማቸው፤ አንድ እግራቸውን አጡ።

የሚገርመው እርሳቸው በኢትዮጵያ ወገን ሆነው በሚዋጉበት ጊዜ አካላቸውን ሲያጡ፤ ወንድማቸው ደግሞ ለኤርትራ ተሰልፈው ሕይወታቸውን ማጣታቸውን ይናገራሉ።

ኮሎኔል ለገሰ አንድ እግራቸውን ቢያጡም አሁን ቆመው በመራመድ ወደ ሚፈልጉበት ቦታ ለመሄድ ይችላሉ።

ግራጫ መስመር

አቶ ንጉሤ ጤናው ደግሞ የቀድሞ ሠራዊት አባል ነበሩ። በዚያ ወቅት በነበረው ጦርነት ከጉልበታቸው በታች የእግራቸውን ክፍል አጥተዋል። ጡረታ ስለሌላቸው አሁን ላይ መጽሐፍት በመሸጥ ነው የሚተዳደሩት። ግን ያሰቡትን ለመፈጸም ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ ይችላሉ።

ግራጫ መስመር

ሌላኛዋ በሁለት ዓመት ከስድስት ወሯ በመኪና አደጋ አንድ እግሯን ያጠችው ታዳጊ የአቶ ሰለሞንን ድጋፍ ከማግኘቷ በፊት አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ነበረች።

አዲስ አበባ ውስጥ ሰው ሰራሽ እግር ቢሰራላትም ለእርሷ ምቹና ለጤናዋ ተስማሚ ባለመሆኑ ተቸግራ ቆይታለች።

በአባቷ ድጋፍ ትምህርት ቤት ትሄድ የነበረችው ታዳጊ አሁን ከጓደኞቿ ጋር ራሷን ችላ ወደ ፈለገችው ስፍራ እንደ ልቧ ትቦርቃለች።

Short presentational grey line

የእነዚህ ግለሰቦች ሕይወት እንዲለወጥ አስተዋፅኦ በማድረግ በኩል የሰው ሰራሽ አካልና የአካል ድጋፍ ባለሙያው የአቶ ሰለሞን አማረ ስም በብዙዎች ይነሳል።

ለእነዚህ የአካል ጉዳት ላጋጠማቸው ወገኖቹ በሙያው ሰው ሰራሽ አካል ሰርቶ በነፃ አበርክቶላቸዋል።

"እነሱ ከከፈሉት ዋጋ አንፃር እኔ የማደርገው ኢምንት ነው" ይላል ሰለሞን።

በእርግጥ እነሱን አንደ አብነት አነሳን እንጂ ለበርካቶች ይህንኑ ችሮታውን አልሰሰተም።

አቶ ሰለሞን ነዋሪነቱ ለንደን ነው። በሰው ሰራሽም ሆነ በተፈጥሮ የአካል ክፍላቸውን ላጡ አካል ጉዳተኞች ሰው ሰራሽ አካልን የአካል ድጋፍ በመስራት ሙያ ላይ ነው የተሰማራው።

"ይህ የሙያ ዘርፍ አሁን በኢትዮጵያ የሚሰጥ የትምህርት ዘርፍ አይደለም" የሚለው አቶ ሰለሞን፤ እርሱም እድሉን ያገኘው በአንድ ወቅት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የህክምና ትምህርት ክፍል በዓለም አቀፍ ቀይ መስቀል ድርጅት ለተወሰኑ ተማሪዎች ትምህርቱ ሲሰጥ ነበር።

አቶ ሰለሞን በሥራ ላይ

በወቅቱ ትምህርት ይሰጥ የነበረው በጳውሎስ ሆስፒታል አካባቢ በሚገኝ የሰው ሰራሽ አካልና የአካል ድጋፍ ማደራጃ ድርጅት እንደነበርም ያስታውሳል።

በጊዜው በቂ ሙያተኛ ስላልነበረ ትምህርቱን እንኳን ሳይጨርስ በኢትዮ- ኤርትራ ጦርነት ጊዜ ወደ ሥራ ገባ። አቶ ሰለሞን እንደነገረን ያኔ በሥራ ላይ የነበሩት ባለሙያዎች አራት ብቻ ነበሩ።

ከዚያ በኋላ ግን ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል በዘርፉ ትምህርት ክፍል መክፈቱንና እምብዛም ሳይገፋበት መዘጋቱን ይናገራል።

ሰለሞን እንደ አጋጣሚ የጀመረው ትምህርት ፍላጎት አሳድሮበት በለንደን ሳውዝ ባንክ ዩኒቨርሲቲ በዘርፉ የትምህርት እድል አግኝቶ ወደ ወደዚያው አቀና። በትርፍ ሰዓቱም ሥራ እየሰራ ልምዱን አጎለበተ።

በተለያየ ጊዜያት ወደ ኢትዮጵያ ባቀናበት ወቅትም የሰው ሰራሽ አካል መስሪያ ግብዓቶችን በመያዝ የበርካቶችን ሕይወት ቀይሯል።

ከኮሎኔል ለገሰ ጋር የአባትና የልጅ ግንኙነት እንዳለው የሚናገረው አቶ ሰለሞን፤ የሰራላቸውን ሰው ሰራሽ እግር በቀየረላቸው ጊዜ "መስዋዕትነት መክፈላችንን የሚረዳ አለ ወይ?" በማለት በደስታ እያለቀሱ እንደጠየቁት ያስታውሳል።

"ከፍያለው ተፈራንም ቢሆን በቴሌቪዥን ካልሆነ በአካል አላውቀውም። አገኘዋለሁ ብዬም አስቤ አላውቅም" የሚለው አቶ ሰለሞን፤ በአጋጣሚ ለአንድ ግለሰብ ሰው ሰራሽ እግር ለመስራት ባቀናበት ወቅት ለሥራው ትብብር በሚያደርጉለት የጳውሎስ ሆስፒታሉ ዶ/ር ወንድማገኝ አማካኝነት እንደተገናኙ ያስታውሳል።

"ወደ ሕንድ ተልኮ እንዲሰራለት ተደርጎ ነበር። እስኪ አንተ አግዘው ነበር" ያሉት እርሳቸው። በዚህ አጋጣሚም ከከፍያለው ጋር ተገናኝተው መኖሪያ ቤቱ ድረስ በመሄድ ሁለት ሰው ሰራሽ እግር የሰራለት።

የሙያ ፍላጎቱ እንዴት አደረበት?

ሰለሞን ከአካል ጉዳተኞች ጋር የቤተሰብ ያህል ቅርበት አለው። አንድ እጁና እግሩን ካጣ እንደ ወንድም እንደ አባትም የሚያሳድገው ልጅ ጋር አብረው ይኖሩ ነበር። ያም ሙያውን እንዲወደው አድርጎታል።

"እርሱን አንድም ቀን አካል ጉዳት እንዳለበት አስቤው አላውቅም፤ ማንም ሰው የሚሰራውን በብቃት ያከናውናል" ይላል።

ምንም እንኳን የኢኮኖሚና የሥነ ልቦና ችግሮችን ጨምሮ በርካታ ፈተናዎች ቢኖሩም አካል ጉዳተኝነት የፈለጉትን ነገር ከማድረግ ግን እንደማይገታ ይናገራል።

ይህ ተግዳሮት የሚገጥማቸውም ሕብረተሰቡም ሆነ መንግሥት እንዲሁም አንዳንድ ተቋማት ለእነሱ የሚገቡ ነገሮችን ስለማያደርጉ ነው ሲልም ይወቅሳል።

ለምሳሌ ደረጃ መውጣትና አውቶብስ መሳፈር የመሳሰሉት ምቹ ያልሆኑ ሁኔታዎች ስሜታቸውን ይጎዳዋል ይላል። በዚህ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ያሉትን ደግሞ በሚችለው አቅም ማገዝ ደስታ እንደሚሰጠው ይናገራል።

አቶ ሰለሞን ሰው ሰራሽ የአካል ክፍሎችን የሚሰራውም በተለያየ ጊዜ ያሰባሰባቸውን ግብዓቶች በመጠቀም ሲሆን አገልግሎቱን የሚሰጠው በነፃ ነው።

አቶ ሰለሞን በሥራ ላይ

"በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰው ሰራሽ አካሎችን ሰርቻለሁ"

በዚህ የሙያ ዘርፍ ከተሰማራ አንስቶ በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰው ሰራሽ የአካል ክፍሎችን ሰርቷል። ሰለሞን እንደሚለው በሙያው አንድ ሰው በወር ቢያንስ 10 ሰው ሰራሽ አካል መስራት ይችላል። በትርፍ ሰዓትም ሥራው ይሰራል። ድንገተኛ ሥራዎችም አሉ።

ከአገር ከመውጣቱ በፊት ደግሞ በሙያው ከ10 ዓመታት በላይ አገልግሏል። በመሆኑም በዚህ ስሌት በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰው ሰራሽ አካሎችን እንደሰራ ይናገራል።

"በኢትዮጵያ ውስጥ በሙያው ብቁ የሆነ የሰው ኃይልና ትምህርት ቤትም የለም። ለዚህ ተብሎ የሚገባው ቁሳቁስም ጥራቱን የጠበቀ አይደለም። አካል ጉዳተኞች ግን በሚሊየን የሚቆጠሩ ናቸው" የሚለው ሰለሞን፤ ሙያው በኢትዮጵያ ውስጥ ትኩረት እንዳልተሰጠው ይገልፃል።

ሰለሞን የመሥሪያ ቁሳቁሶቹም የአውሮፓና የሌሎቹ በጣም ልዩነት እንዳለውና አገር ውስጥ ያለው ፕላስቲክ ርካሽ ቢሆንም ምቾት እንደሌለው ይጠቅሳል።

ይህንንም የታዘበው ወደ አውሮፓ ከሄደ በኋላ ሲሆን "በአገር ውስጥ አገልግሎት ላይ የሚውሉት፤ ምቾት የማይሰጡ ሌላ ጉዳት ሊያስከትሉ የሚችሉ ናቸው። ለጤና ተስማሚ አይደለም። ይህም በሌላ ሊተካ ይገባል" ሲል ይመክራል።

ይህ የከነከነው አቶ ሰለሞን ታዲያ ለንደን ከሄደ ጀምሮ አንድ ቀን አገር ቤት ብገባ እያለ በግሉ አካል ጉዳተኞችን ለመርዳት የሚጠቅሙ ቁሶችን በየቀኑ ይሰበስብ ነበር።

ከአስራ አንድ ዓመታት በኋላ ለአንድ ሰው ሰው ሰራሽ እግር ለመስራት ወደ ኢትዮጵያ ሲሄድ 5 ሻንጣ ማቴሪያል ይዞ ገባ። አጋጣሚውን በመጠቀምም ከፍተኛ ችግር ያለባቸውንና ለሚያውቃቸውን 12 መምህራንና ተማሪዎች ዘመናዊ ሰው ሰራሽ እግር በነፃ እንደሰራላቸው ነግሮናል።

ከዚያ በኋላም ለበርካታ ሰዎችን ሕይወት መሻሻል ምክንያት ሆኗል።

እንደ ሰለሞን ከሆነ አንድ የአዋቂ ሰው ሰራሽ እግር ቢያንስ 5 ሺህ ፓውንድ (240ሺህ 758 ብር) ያስወጣል፤ የሕፃናት ደግሞ 2 ሺህ ፓውንድ (96ሺህ 303 ብር)።

በቀጣይ ምን ለመስራት አሰበ?

አቶ ሰለሞን በቀጣይ መስራት የሚፈልጋቸው የአጭርና የረዥም ጊዜ እቅዶች አሉት። በቅርቡ የኢኮኖሚ አቅማቸው ዝቅተኛ ለሆኑና አብዛኞቹ ሁለት እግራቸውን ላጡ 20 ሰዎች ሰው ሰራሽ አግር ለመስራት ወደ ኢትዮጵያ ይሄዳል።

እነዚህ ግለሰቦች አብዛኞቹ ሴቶች ናቸው። ከመካከላቸውም ወታደሮች፣ መምህራን፣ ተማሪዎች፣ አናፂና ሐኪሞች ይገኙበታል።

በኢትዮጵያና በኤርትራ መካካል የተፈጠረውን ሰላምም በማሰብ በአገራቱ ጦርነት ወቅት አካላቸውን ላጡ ለአንድ የኢትዮጵያና ለአንድ የኤርትራ ወታደር ሰው ሰራሽ አካል መስራት የዚህ እቅዱ አካል ነው።

አቶ ሰለሞን ይህን ሁሉ የሚያደርገው አስፈላጊውን ወጪ ሁሉ እራሱ እየሸፈነ ሲሆን፤ የመሥሪያ ቦታ በመስጠት የሚተባበረው ጳውሎስ ሆስፒታል መሆኑን ተናግሯል።

የሰው ሰራሽ አካል ለመስራት አገር ውስጥ የሚጠቀሙበትን ማቴሪያል አሁን ባለው ዘመናዊ ቴክኖሎጂና ማቴሪያል መለወጥ እንዲሁም ቴክኖሎጂውን ወደ አገር ውስጥ በማስገባት የመስሪያ ቦታ አግኝቶ አካል ጉዳተኞችን በስፋት ማገልገልን ደግሞ የረጅም ጊዜ እቅዱ ነው።

የተንቀሳቃሹ ምስል መግለጫ, "ስለአንድ ፓርቲና ግለሰብ አይደለም ያለው...... እንቅስቃሴው መጠናከር አለበት":- ከፍያለው ተፈራ