አካል ጉዳተኛነት፡ ትኩረት የተነፈገው የብዙ ኢትዮጵያውያን እውነታ

የፎቶው ባለመብት, MESSERET YIRGA
ኬንያዊቷ አን ዋፉላ ስትራይክ ታዋቂ የፓራሊምፒክ ተወዳዳሪ ስትሆን የሕይወትታሪኳን በመጽሐፍና በዘጋቢ ፊልም ለሕዝብ አቅርባለች። የዛሬ 47 ዓመት የሁለት ዓመት ህጻን እያለች በያዛት የልጅነት ልምሻ (ፖልዮ) ምክንያት አካል ጉዳተኛ የሆነችው አን በርካታ ውጣ ውረዶችን አሳልፋ ስኬትን እንደተጎናፀፈች ዛሬ በሙሉ ልብ ትናገራለች።
ኢትዮጵያውያን አካል ጉዳተኞች እንደ አን ጥሩም ሆነ መጥፎ ተሞክሯቸውን የሚናገሩት መቼ ይሆን? ኢትዮጵያ ውስጥ አካል ጉዳተኛ መሆን ምን ማለት ነው? በትምህርትም ሆነ በሥራ ዓለም ምን ዓይነት ውጣ ውረድስ ይገጥማቸዋል?
አካል ጉዳትና ኢትዮጵያውያን
''እንደ ዕድል ሆኖ በቤተሰቤም ሆነ ባደግኩበት ሰፈር በአካል ጉዳተኛነቴ የደረሰብኝ ምንም ዓይነት ተጽዕኖ አልነበረም። እንዲያውም አካል ጉዳተኛ መሆኔንም አላውቀውም'' የሚለው አንዱዓለም ከበደ አንድ እጁና ሁለት እግሮቹ ጉዳተኛ ናቸው።
ከሚያከናውናቸው ተግባሮችና በአካባቢው ከነበረው ተቀባይነት የተነሳ አካል ጉዳትኝነቱን የዘነጋው አንዱዓለም፤ ብዙ አካል ጉዳተኛ ጓደኞቹ ግን ስለሚገጥሟቸው የተለያዩ ችግሮች እንደሚነግሩት ይገልጻል።
መላኩ ተክሌ የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ልማት ማዕከል በመባል የሚታወቀው መንግሥታዊ ያልሆነ ተቋም ዋና ዳይሬክተር ነው። መላኩ አካል ጉዳተኛ ሲሆን ከቦታ ቦታ ለመዘዋወር ክራንች ይጠቀማል። የሚሠራበት ድርጅት አካል ጉዳተኞች በተለያዩ የሙያ ዘርፎች እንዲሳተፉ ለማድረግ የሚተጋ ነው።
ከሥራዎቻቸው መካከል አካል ጉዳተኞችን የሚያካትት ትምህርት፣ ጤና፣ መተዳደሪያና የማህበረሰብ ልማት ይገኙበታል። ድርጅቱ በአጠቃላይ ወደ 48 ሠራተኞች አሉት። ከሠራተኞቹ መካከል ደግሞ 20ዎቹ አካል ጉዳተኛ ከእነሱም ውስጥ 19ኙ ሴቶች ናቸው።
የአካቶ ትምህርት ፕሮጀክት አስተባባሪ የሆነቸው እመቤት ግርማ ''ሴት አካል ጉዳተኞች በሁሉም መስኮች እኩል መካተታቸውን ለማረጋገጥ እንጥራለን። ይህም ደግሞ በሚሰጡ ሥልጠናዎችም ሆነ በማንኛውም አገልግሎት ቢያንስ 50 በመቶ ሴቶች እንዲሆኑ ይጠየቃል'' ትላለች።
እንደ ኢትዮጵያ እያደጉ ባሉ ሃገራት ውስጥ አካል ጉዳተኛ ለሆነ ሰው ብዙ አዳጋች ነገሮች አሉ የምትለው እመቤት፤ ፈተናዎቹ ለሴት አካል ጉዳተኞች እጥፍ እንደሚሆኑ ትጠቁማለች።
ትምህርት ካለማግኘት አንስቶ እስከ ሥራው ዓለም ድረስ ለአካል ጉዳተኞች ብዙ የሚከብዱ ነገሮችን ታነሳለች። ለአካል ጉዳተኞች ተብለው የሚዘጋጁ የትምህርት ማሟያ መጻሕፍት አቅርቦትና የትምህርት ዕድል የማግኘት አጋጣሚው በጣም ጠባብ በመሆኑ በትምህርታቸው ገፍተው የሚሄዱ የአካል ጉዳተኞች ቁጥር እየመነመነ እንደሚመጣም ታስረዳለች።

የፎቶው ባለመብት, MESSERET YIRGA
የመረጃና የምቹ አገልግሎቶች ውስንነት?
በቅርቡ በእንግሊዟ ለንደን ከተማ አለም አቀፍ የአካል ጉዳት ጉባኤ ተካሂዶ ነበር። በጉባኤው ላይ ከተነሱ ነጥቦች አንዱ የአካል ጉዳተኞች ቁጥር አለመታወቁ ተጠቅሷል። አቶ መላኩ ተክሌ እንደሚሉት ከዓመታት በፊት በወጣው የተባበሩት መንግሥታት የአካል ጉዳተኞች ሪፖርት መሠረት፤ በዓለም ላይ ካሉት 1 ቢሊዮን አካል ጉዳተኞች መካከል 15 በመቶዎቹ በታዳጊ ሃገራት ያሉ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ 15 በመቶ የሚሆኑት በኢትዮጵያ ይገኛሉ።
''በማህበረሰቡ ዘንድ በቂ መረጃ የለም'' የምትለው እመቤት፤ ብዙ አካል ጉዳተኞች ከልጅነታቸው ጀምሮ እንደሚገለሉ ታክላለች። በየቤቱ ተደብቀው የሚያድጉ አካል ጉዳተኛ ልጆች ከማህበረሰቡ ጋር ከተቀላቀሉ በኋላ መድሎና መገለል ይደርስባቸዋል። ብዙ ሁኔታዎችም አልጋ በአልጋ አይሆኑላቸውም።
''እነዚህ ችግሮች ሁሉንም አካል ጉዳተኞችን የሚያጋጥሙ ቢሆኑም በሴቶች ላይ ግን ይብሳል። ከቤት መውጣት አይፈቀድላቸውም እንደውም እርባና እንደሌላችው ይቆጠራሉ። እነዚህን ተግዳሮቶች ቢያልፉ እንኳን አካባቢያቸው ምቹ አይሆንም'' ትላለች።
ባለሙያዎች ከዚህ በተጨማሪም አካል ጉዳተኞች ለራሳችው ያላችው ዝቅተኛ አመለካከትም ይጨመርበታል ይላሉ። "አቅማቸውን እንዲጠራጠሩ ይደረጋሉ" የምትለው እመቤት ለአካል ጉዳተኞች በቂ መረጃ አለመኖሩም ችግር መሆኑን ትገልጻለች።
አቶ ረታ ጌታችው በእንግሊዝ ሃገር ሊድስ ከተማ የማስተርስ ዲግሪውን በአካል ጉዳት ላይ እያሰራ ሲሆን እሱም ''ይህች ዓለም የአካል ጉዳት ለሌለባቸው ሰዎች ምቹ ሆና የተሠራች ናት'' ይላል።
አቶ ረታ አካል ጉዳተኛ ባይሆንም ለአካል ጉዳተኞች ጉዳይ በቂ ቦታ አለመሰጠቱ ኢ-ፍትሐዊ ነው ይላል። ከመረጃ አንስቶ እስከ መንገድና የሃገር ኢኮኖሚ ድረስ አካል ጉዳተኞችን የማካተት ሥራ መሰራት አለበት ይላል።
አክሎም አካል ጉዳተኞች ያሉበት ቦታ በበቂ ሁኔታ አይታወቅም ይላል። በማህበረሰቡ ዘንድ ያለው መገለል ለማስረዳት አካል ጉዳተኛ ልጅ እንዳላቸው ለማሳወቅ እንኳን የሚያሳፍራቸው ወላጆች እንዳሉ ይገልፃል።
''እነሱም ላይ አልፈርድም። ምክያቱም ከዚህ ቀደም አካል ጉዳተኛ ልጅ እንዳላችው ያሳውቁ ሰዎች ብዙ ችግር ሲደርስባቸው አይተዋል'' ይላል።
ወሲብና አካል ጉዳተኝነት
አቶ መላኩ ''የጤና ባለሙያዎች ከሕብረተሰቡ የወጡ እንደመሆናቸው፤ አካል ጉዳተኞች ወይ ለወሲብ ብቁ እንዳልሆኑ አለበለዚያም ከመጠን ያለፈ ፍላጎት እንዳላቸው አድርገው ያስባሉ'' በማለት ያሉትን ሁለት ጽንፍ አመለካከቶች ይጠቅሳሉ።
አያይዘውም የጤና ተቋማት የተለያየ አካል ጉዳት ያለባቸው ሰዎችን እንደ ጉዳታቸው አይነት ሊያስተናግዱ የሚችሉበት መንገድ እንዲዘረጉ ይጠቁማሉ።
አቶ ረታ ስለ ወሲብ ሲነሳ ተያይዞ ስለሚያጋጥመው ያልተፈለገ እርግዝናም እንደ ሃገር ሊወራበት ይግባል ይላል። "በኢትዮጵያ ይህ ጉዳይ አስቸኳይ ሆኖ አይታይም። ምክንያቱም በመጀመሪያ ድህነትን ማሸነፍ አለባቸው የሚል አመለካከት አለ"። ሲል ይገልጻል።
መሠረት ይርጋ ከአካል ጉዳተኞች ጋር የዳንስ ቡድን በማቋቋም በእንቅስቃሴ ብቻ ሳይሆን በራሳቸው እንዲተማመኑ ለማድረግ እንደሚሠሩ ትናገራለች። ከሷ የዳንስ ቡድን ውስጥ ሁለቱ አካል ጉዳተኛ ሴቶች አራቱ ደግሞ ወንዶች እንደሆኑ የምትናገረው መሠረት፤ በየጊዜው ስለሚያጋጥሟቸው እክሎች እንደሚወያዩም ትገልፃለች።
እንደ ምሳሌ ከምትጠቅሳቸው ገጠመኞች በአንዱ፤ ስሟ እንዲጠቀስ ያልፈለገች አካል ጉዳተኛ ተማሪዋ ተደፍራ ላልተፈለገ እርግዝና ትዳረጋለች። ሰውነቷ እርግዝናውን ለመቋቋም ቢቸገርም ወልዳ ልጇን ለመሳም በቅታለች።
ወልዳ መደሰት የቻለችው የመሠረትና ሌሎችም በዙሪያዋ የነበሩ ሰዎች ጥረት ታክሎበት ነው። መሰረት ወደኋላ መለስ ብላ ስታስታውስ ተማሪዋ ራሷን ለማጥፋት ሁሉ ታስብ እንደነበረ ትናገራለች። ''በጣም የሚያሳዝነው ወደ ጤና ጣቢያ ይዘናት በሄድንበት ወቅት ብዙ የጤና ባለሙያዎች 'ቢቀርባትስ' በማለት ሲያጉረመርሙ ነበር'' በማለት ስሜትን የሚጎዳውን አስተያየት ትጠቅሳለች።
ኢትዮጵያ ውስጥ በአካል ጉዳተኝነት ዙሪያ መሠራት ያሉባቸው ብዙ ነገሮች እንዳሉ አቶ ረታ አስረግጠው ይናገራሉ። መሠረትም ይቀራሉ ከምትላቸውን ነጥቦች መካከል ግንዛቤ መፍጠርን በዋነኝነት ታስቀምጣለች።
"በአለም ዙሪያም ገና ብዙ የሚቀሩ ጉዳዮች አሉ። ኢትዮጵያ እንደ አገርና ኢትዮጵያውያን እንደ ማህበረሰብ ከበፊቱ በተሻለ ለአካል ጉዳተኞች ምን ዓይነት ቦታ መሰጠት እንዳለበት ራሳችንን መጠየቅ ይኖርብናል" ይላሉ አቶ ረታ።














