ተኪ፡ መስማት በተሳናቸው የሚንቀሳቀሰው ተቋም

ተኪ በ18 መስማት የተሳናቸው ሠራተኞች ይንቀሳቀሳል

የፎቶው ባለመብት, TEKI

የምስሉ መግለጫ, ተኪ በ18 መስማት የተሳናቸው ሠራተኞች ይንቀሳቀሳል

ሚሚ ለገሰ፤ አልፋ መስማት የተሳናቸው ትምህርት ቤት ውስጥ ሳለች ከአንድ ኢትዮጵያዊና ስዊዘርላዳዊ ጋር ተገናኘች። በሦስት ሚሊዮን ብር መነሻ በጀት መስማት የተሳናቸውን ያካተተ ድርጅት የመመስረት አላማ አንግበው ነበር።

በሕጻናት ማሳደጊያ ያደገችው ሚሚ፤ ከሁለቱ ግለሰቦች ጋር በመሆን የወረቀት ቦርሳ የማምረት ሀሳብን ጠነሰሱ። መስማት የተሳናቸውን ያካተተ የሥራ ዘርፍ ለመፍጠር፣ ጎን ለጎንም አካባቢን ከፕላስቲክ ብክልት ለመከላከል።

ሚሚ ከሕጻናት ማሳደጊያ ከወጣች በኋላ በክር ሹራብ፣ ኮፍያና ቦርሳ ትሠራ ነበር። ሙያውን እንደሷው መስማት ለተሳናቸው ታስተምርም ነበር። ሆኖም የዳንቴል ሥራ ገበያው እንዳሰቡት አመርቂ አልነበረም።

ማኅበራዊ አገልግሎት የመስጠት ከፍተኛ ፍላጎት ያላት ሚሚ፤ ሙሉ ጊዜዋን ከሹራብ ሥራው ወደ ወረቀት ቦርሳው አዞረች። ከሦስት ዓመት ተኩል በፊትም 'ተኪ' የተባለው የወረቀት ቦርሳ አምራች ድርጅት ተመሰረተ።

መስማት ከተሳናቸው ልጆች ጋር ያደገችው መስከረም በየነ፤ የምልክት ቋንቋ አስተርጓሚ ናት። መስማት ከተሳናቸው ጋር በቅርበት የምትሠራው መስከረም፤ ተኪን የተቀላቀለችው ከአንድ ዓመት ከስምንት ወር በፊት ነበር።

ሚሚና መስከረም የተኪ ሥራ አስኪያጆች ናቸው።

ሚሚ ከምልክት ቋንቋ አስተርጓሚ ጋር በመሆን በተለያዩ ሥፍራዎች እየተዘዋወረች የወረቀት ቦርሳቸውን ታስተዋውቃለች፤ መስከረምም የድርሻዋን ትወጣለች።

[ሚሚ ከቢቢሲ የቀረቡላትን ጥያቄዎች በምልክት ቋንቋ ስትመልስ፤ መስከረም እያስተረጎመች ስለድርጅታቸው አውግተውናል።]

ሚሚና መስከረም የተኪ ሥራ አስኪያጆች ናቸው

የፎቶው ባለመብት, TEKI

የምስሉ መግለጫ, ሚሚና መስከረም የተኪ ሥራ አስኪያጆች ናቸው

አካታችነት ጥያቄ

ኢትዮጵያ ውስጥ የመንግሥትም ይሁን የግል ድርጅቶች አካል ጉዳተኞችን አካታች ባለመሆናቸው ይተቻሉ። አካል ጉዳተኞችን ለመቅጠር ካለመፈለግ አንስቶ ቢቀጠሩም ምቹ የሥራ ሁኔታ አለማዘጋጀት ዋነኛ ችግሮች ነው።

ተኪ ይህንን ለመለወጥ የተነሳ ድርጅት ሲሆን፤ በዋነኛነት ሴት መስማት የተሳናቸውን ቀጥሮ ያሠራል።

መስከረም እንደምትለው፤ የድርጅቶች አካታች አለመሆን የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ዓለም አቀፍ ችግር ነው።

"ድርጅቶች አካል ጉዳተኞችን መቅጠር ሲያስቡ ፍርሀት ያድርባቸዋል። መስማት ለተሳነናቸው የምልክት ቋንቋ አስተርጓሚ መቅጠር ተጨማሪ ወጪ ይሆንባቸውል። ነጋዴውም፣ ቀጣሪውም ማኅበረሰቡ ጋርም የግንዛቤ ክፍትተ አለ፤ አካል ጉዳተኞች እንደ ጉዳት አልባ ይሠራሉ ተብሎ ስለማይጠበቅ ማካተቱ አይታሰብም"

ችግሩ የሥራ ቅጥር አካታች አለመሆኑ ብቻ ሳይሆን፤ መሥሪያ ቤቶች ለአካል ጉዳተኞች ምቹ አለመሆናቸው ጭምርም ነው። ምን ያህሉ መሥሪያ ቤት ወይም ህንፃ ራምፕ (የአካል ጉዳተኞች መወጣጫ) አለው? ምን ያህል መሥሪያ ቤትስ ለአካል ጉዳተኞች አሳንስር ያዘጋጃል?

ሚሚ እንደምትለው፤ በተለይ መስማት በተሳናቸው ዘንድ ችግሩ የሚጀምረው ከቤተሰብ ነው። የምልክት ቋንቋ የሚችል ሰው እምብዛም ስላልሆነ መስማት የተሳናቸው ልጆች ከመረጃ ተገልለው ያድጋሉ። በሥራ ቦታም እንዲሁም።

"መስማት የተሳናቸው ይገለላሉ፤ ብቻቸውን የመሆን አዝማሚያም አለ። ተኪ ውስጥ ግን አንዱ አንዱን እያየ ለካ ብቸኛ አይደለሁም ብሎ ጉዳቱን አቅልሎ እንዲመለከተው ይደርጋል። መረጃም እንለዋወጣለን። መረጃ ማግኘት ደግሞ በራስ መተማመንን ይጨምራል"

ከሦስት ዓመት በፊት የተመሰረተው 'ተኪ' የወረቀት ቦርሳ አምራች ድርጅት ነው

የፎቶው ባለመብት, TEKI

የምስሉ መግለጫ, ከሦስት ዓመት በፊት የተመሰረተው 'ተኪ' የወረቀት ቦርሳ አምራች ድርጅት ነው

ምን ይደረግ?

ከ60 በመቶ በላይ አካል ጉዳተኞችን ቀጥሮ የሚያሠራ ድርጅት ከተጨማሪ እሴት ታክስ (ቫት) ነጻ ይሆናል የሚለው ድንጋጌ አካታችነትን ቢያበረታታም አተገባበሩ ላይ ክፍተት እንዳለ መስከረም ትናገራለች።

"ከ60 በመቶ በላይ አካል ጉዳተኞች ስለቀጠርን የተጨማሪ እሴት ታክስ እፎይታ ለማግኘት ስንጠይቅ ረዥም ቢሮክራሲ ገጠመን። ለሰባት ወር፣ በረዥም ኦዲት አልፈን አሁንም አልጨረስንም"

መንግሥት የድንጋጌውን ተፈጻሚነት ለማረጋገጥ ሂደቱን ቀላል ማድረግ እንዳለበት ሚሚም ትናገራለች። ከተጨማሪ እሴት ታክስ ነጻ ከማድረግ ባሻገር ከውጪ የሚገባ ጥሬ እቃን ከቀረጥ ነጻ ማድረግና ሌሎችም ማበረታቻዎች ቢኖሩ፤ ድርጅቶች አካል ጉዳተኞችን ለመቅጠር እንደሚነሳሱ ታምናለች።

ብዙ ድርጅቶች አካል ጉዳተኞችን ያካተተ ተቋም ከፍተው፤ በሥራ ቦታ አለመመቻቸትና በኪራይ ዋጋ መናር ሳቢያ ሲዘጉ እንደሚስተዋል የምትናገረው መስከረም፤ መንግሥት ለዘርፉ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ድጋፍ ቢያደርግ ለውጥ እንደሚመጣ ታስረዳለች።

አካል ጉዳተኞች ለአንድ ክፍት የሥራ ቦታ የሚጠየቀው የትምህርት ማስረጃና ሙያዊ ብቃት ቢኖራቸውም ቀጣሪዎች እድሉን አይሰጧቸውም። ቀጣሪ ድርጅቶችና ኃላፊዎች ስለ አካል ጉዳተኞች ያላቸውን ግንዛቤ ማስፋት፣ አካል ጉዳተኞች እንደማንኛውም ሰው መሥራት እንደሚችሉ መረዳት እንዳለባቸውም ታክላለች።

ጉዞ ወደ አካባቢ ጥበቃ

ኢትዮጵያ፤ ከሦስት ዓመት በኋላ እንደሚተገር በተነገረለት ድንጋጌ፤ የአካባቢ ብክለትን ለመከላከል የፕላስቲክ ምርትን የማገድ እቅድ እንዳላት ይፋ አድርጋለች። በዚህ ረገድ ጎረቤት አገር ኬንያን ጨምሮ በርካታ አገሮች ፕላስቲክ ምርትን ከዓመታት በፊት ማገዳቸው ይታወቃል።

ተኪ ከድንጋጌው ቀድሞ ለአካባቢ ጥበቃ የሚበጀውን የወረቀት ቦርሳ ለማስተዋወቅ እየሞከረ ነው። በኢትዮጵያ በአካባቢ ጥበቃ ረግድ ግንዛቤ እንዳልዳበረ የምታስረዳው ሚሚ፤ ሥራቸው ፈታኝ እንደሆነ ትገልጻለች።

ለምሳሌ የመደብር ባለቤቶች በቅናሽ የሚሸመተውን ፕላስቲክ ይመርጣሉ።

"በነጻ ለምሰጠው ነገር ለምን [ውድ የወረቀት ቦርሳ ገዝቼ] ጥቅሜን አሳልፌ እሰጣለሁ ብለው ቅር ይላቸዋል" ትላለች።

የወረቀት ቦርሳ ከፕላስቲክ አንጻር ዋጋው ቢጨምርም ለአካባቢ ጥበቃ ያለው አስተዋጽኦ ቀላል አለመሆኑን ለማስረዳት ጥረት ያደርጋሉ። ምርታቸውን ግዙፍ ተቋሞች ሲገዙ በማየት በወረቀት ቦርሳ ለመገልገል ፍቃደኝነት ያሳዩ እንደተበራከቱ መስከረም ትናገራለች።

በዋነኛነት በብዛት ለድርጅቶች ቢያከፋፍሉም፤ በግላቸው የሚገዟቸውም አሉ። በእርግጥ ከትርፍ አንጻር አዋጭ ባይሆንም ለወደፊት ነገሮች እንደሚለወጡ ተስፋ እንዳላቸው ሚሚ ትገልጻለች።

"ትርፋችን ትንሽ ሆኖ ብንሠራም ነገ የሰው ግንዛቤ ሲያድግ የተሻለ እንሸጣለን። የተነሳነው የአካባቢ ጥበቃን እና ማኅበራዊ አገልግሎትንም ይዘን ነው"

በአንድ ወቅት ከስዊዘርላንድ ኤምባሲ ጋር በመተባበር በሴት ሥራ ፈጣሪዎች ለተመሰረቱ ድርጅቶች በነጻ የወረቀት ቦርሳ አከፋፍለው ነበር። ከዚህም የተሻለ ተቀባይነት የተገኘው በባልትና ምርቶች መደብረና በፋርማሲዎች ነበር።

ተኪ እስካሁን 395 ሺህ የወረቀት ቦርሳ አምርቷል

የፎቶው ባለመብት, TEKI

የምስሉ መግለጫ, ተኪ እስካሁን 395 ሺህ የወረቀት ቦርሳ አምርቷል

ሽሮ፣ በርበሬ ሲሸምቱ በካኪ መሸፈን የሚመርጡ እንዲሁም የቲቢ እና ኤችአይቪ መድሀኒትን በሚስጥር ለመያዝ የወረቀት ቦርሳ የሚገዙም ብዙ ናቸው።

ለወደፊት የፕላስቲክ ምርት ሲታገድ የገንዘብ አቅም ያላቸው ግዙፍ ተቋሞች ከፕላስቲክ ወደ ወረቀት ቦርሳ ምርት ሊዘዋወሩ ይችላሉ። ይህም እንደ ተኪ ያሉ ተቋሞች ህልውናን ጥያቄ ውስጥ ይከታል።

ሚሚ እንደምትለው፤ በወረቀት ቦርሳ ምርት ዘርፍ ለአካል ጉዳተኞች ቅድሚያ ቢሰጥ ብዙ ሺህ ሥራ አጥ አካል ጉዳተኞችን መደገፍ ይቻላል።

"ይሄ ዘርፍ ለአካል ጉዳተኞች ቢሰጥ በከፍተኛ ሁኔታ የአካል ጉዳተኞችን ሥራ አጥነት ይቀርፋል። ማሽን ሳያስፈልግ፣ በቀላሉ ማንኛውምም አካል ጉዳተኛ ሊሠራው ይችላል። የሰውን አስተሳሰብም ለመቀየርና መንግሥትን ለማሳመንም ግንዛቤ መስጫ መድረክ ለማዘጋጀት አስበናል"

በቅርቡ ግንዛቤ ማስጨበጫና የገንዘብ ድጋፍ ማሰባሰቢያ 'ክራውድ ፈንዲንግ' የማካሄድ እቅድ እንዳላቸው ሚሚና መስከረም ይናገራሉ።

የተኪ ጅማሮ

ተኪ በ18 መስማት የተሳናቸው ሠራተኞች ይንቀሳቀሳል። እስከአሁን 935ሺህ የወረቀት ቦርሳ አምርቷል። ለመዋዋቢያ ማስቀመጫ፣ ለምግብ ማጓጓዣ እና ለተለያዩ ቁሳቁሶች የሚሆን የወረቀት ቦርሳ በተለያየ ዋጋ ያቀርባሉ።

ሚሚ እና መስከረም እንደሚሉት፤ የጥሬ እቃ ውድነት ዋነኛ ተግዳሮታቸው ነው። ከተጨማሪ እሴት ታክስ ነጻ ቢሆኑ ይህ እንደሚለወጥም ያስረዳሉ።

"እስካሁን ከቫት ነጻ ብንሆን፤ የምርታችንን ዋጋ ቀንሰን ሰው በቀላሉ እንዲገዛው ማድረግ እንችል ነበር። ገበያውን ሰብረን ገብተን ተወዳዳሪ እንሆንም ነበር" ትላለች ሚሚ።

ቀድሞ ኢትዮጵያ ውስጥ ከተረፈ ምርት ዳግመኛ የተሠራ ወረቀት ይጠቀሙ ነበር። የውጪ ምንዛሬ እጥረት ወረቀቱ የሚሠራበት ኬሚካል እንደልብ እንዳይገኝ ስላደረገ የምርታቸው ጥራት ቀንሶ ነበር። ስለዚህም ለተወሰነ ጊዜ ምርት ለማቆም ተገደዋል።

ለዚህም መፍትሔው የመንግሥት ድጋፍ እና ከተጨማሪ እሴት ታክስ ነጻ መደረግ እንደሆነ ሚሚ ታስረዳለች።

ሌላው መሰናክል ምቹ ቦታ አለማግኘት ነው። ቀድሞ የሚሠሩበት ቦታ ከአዲስ አበባ እምብርት ስለሚርቅ ምርታቸውን ለማጓጓዝ ተቸግረው ነበር።

ቦታው ለመኖሪያ ተብሎ የተዘጋጀ ስለሆነ ምርት ማከማቻ አልነበራቸውም። ተጨማሪ መስማት የተሳናቸው ለመቅጠርም አልቻሉም ነበር።

ተኪ የአካባቢ ጥበቃን እና ማኅበራዊ አገልግሎትን አጣምሯል

የፎቶው ባለመብት, TEKI

የምስሉ መግለጫ, ተኪ የአካባቢ ጥበቃን እና ማኅበራዊ አገልግሎትን አጣምሯል

ዓመት ከወሰደ ሂደት በኋላ፤ ጎተራ አካባቢ ለጥቃቅንና አነስተኛ የተመደበ ህንፃ ላይ፣ በአነስተኛ ኪራይ መንግሥት ቦታ ሰጥቷቸዋል። ለድርጅቶች ምርት ለማመላለስ ቅርብ ቢሆንም፤ ፎቅ ላይ በመሆኑ ዊልቸር ወይም ክራንች የሚጠቀሙ ሰዎች ምቹ አይደለም።

ሚሚ እና መስከረም በቀጣይ ሦስት ዓመታት፣ 5 ሚሊዮን የወረቀት ቦርሳ በአዲስ አባበ የማሰራጨት፣ ለ100 ሰዎች የሥራ እድል የመፍጠር እቅድም አላቸው።