"ቁጥራችን ትንሽ ስለሆን ነው መሰል፤ ትዝም አንላቸው" የኢትዮጵያ ዐይነ ሥውራን ማኅበር

የፎቶው ባለመብት, Akaki Kaliti Sub City Administration FB
ባሳለፍነው ሰኞ ከጠዋቱ 4፡00 ሰዓት ገደማ የ26 ዓመቱ ዐይነስውር ለጉዳይ ባቀናበት አቃቂ ክፍለ ከተማ የአሳንሰር ጉድጓድ ውስጥ ገብቶ ሕይወቱ ማለፉን የኢትዮጵያ ዐይነ ሥውራን ብሔራዊ ማህበር የህዝብ ግንኙነትና የቅርንጫፎች ኃላፊ አቶ ገብሬ ተሾመ ለቢቢሲ ገለፁ።
በአደጋው ሕይወቱ ያለፈው ድረስ ሁናቸው በብሔራዊ ዐይነ ሥውራን ማህበር ሥር በሚተዳደረው የወላይታ ዐይነ ሥውራን ትምህርት ቤት ትምህርቱን ተከታትሏል። በዘንድሮ ዓመትም በኮተቤ ሜትሮ ፖሊታን ዩኒቨርሲቲ በመምህራን ማሰልጠኛ ፕሮግራም በዲፕሎማ ተመርቋል።
ባሳለፍነው ቅዳሜና እሁድ ከሌሎች ተመራቂዎች ጋር ሥልጠና ወስደው የሥራ ቦታ ለመመደብ እጣ ይወጣላቸዋል። እጣው ሲወጣም ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ይደርሰዋል።
የተመደበበት ክፍለ ከተማ ከሚኖርበት አቃቂ ክፍለ ከተማ ስለሚርቅ ወደተመደበበት ክፍለ ከተማ ሄዶ እንዲቀይሩት ጥያቄ ያቀርባል። እዚያም አቃቂ ክፍለ ከተማን እንዲጠይቅ ስለነገሩት ወደ ክፍለ ከተማው ያቀናል።
ጥያቄውን ለማቅረብ ወዳቀናበት አቃቂ ክፍለ ከተማ 7ኛ ፎቅ ደርሶ ወደ ታች ለመውረድ የአሳንሰሩን ቁልፍ ይጫነዋል። ተከፈተለት። አሳንሰሩ ግን ወለል አልነበረውም፤ 21 ሜትር በሚገመተው የአሳንሰር ጉድጓድ ውስጥ ተምዘግዝጎ ወድቆ ይህንን ዓለም ተሰናበተ።
አቶ ገብሬ እንደሚሉት እስካሁን ለማህበሩ ከደረሱት የሞትና የአካል ጉዳት ሪፖርቶች በአሳንሰር ምክንያት የሞት አደጋ ሲያጋጥም ይህ የመጀመሪያው ነው።
"አሁን የተፈጠረው አደጋ እንኳንስ ለዐይነ ሥውር ለዐይናማም ቢሆን እጅግ አደገኛ ነው" የሚሉት አቶ ገብሬ በኮንስትራክሽን ሕግ መሠረት በ2001 ዓ.ም በወጣ የህንፃ ኮድ ላይ ያለውን ደንብና መመሪያ ያጣቅሳሉ።
በመመሪያው ላይ አሳንሰሮች ከውጭም ሆነ ከውስጥ የብሬል ፅሁፍ እንዲኖራቸው እንዲሁም ድምፅ እንዲኖራቸው ይደነግጋል፤ ነገርግን ሃገር ውስጥ የሚገጣጠሙ አሳንሰሮች ይህንን የሚያሟሉ አይደሉም ሲሉ ይኮንናሉ።
"ከውጭ የሚመጡት አሳንሰሮች ብሬል ተገጥሞላቸው ይመጣሉ፤ ድምፅም አላቸው፤ ነገር ግን ብዙ ጊዜ ድምፁን ስለማይከፍቱት አይሰሩም" ይላሉ። በትክክል አገልግሎት የሚሰጡትም በጣም ጥቂቶች እንደሆኑ የታዘቡትን አጋርተውናል።
ምንም እንኳን እርሳቸው ያለ ረዳት ብዙ ጊዜ አሳንሰር ውስጥ የመግባት ልምድ ባይኖራቸውም የገጠማቸው አለ።
"አሳንሰር ውስጥ ገብቼ የነካኋቸው አብዛኞቹ ቁልፎች አይሰሩም ነበር። የሚሰሩት 9ኛ ፎቅና ምድር ላይ ያለው ብቻ ነበር የሚሰራው፤ እኔ መሄድ የፈለኩት ደግሞ 5ኛ ፎቅ፤ ከላይ ታች ስል በኋላ ላይ በሰዎች እርዳታ ወጣሁ" ሲሉ ሲንገላቱ የዋሉበትን ቀን ያስታውሳሉ።
ከዚህ ቀደምም ዐይነ ሥውራን በመንገድ መቆፋፈር፣ በመኪና አደጋ፣ ከድልድይና ፎቅ ላይ በመውደቅ አደጋ ለሞትና አካል ጉዳት መዳረጋቸውን ይናገራሉ።
በአንድ ወቅት አንድ ዐይነ ስውር የውጭው በረንዳ [ከለላ] ከሌለው የትምህርት ቤት ህንፃ ወድቆ ከባድ አካል ጉዳት እንደደረሰበት ያነሳሉ።
ከድልድይ ላይም እንዲሁ ከለላ ባለመኖሩ የአንድ አባት ሕይወት ሲያልፍ በቅርብ ጊዜም የኮተቤ መምህራን ኮሌጅ ተመራቂ ተማሪ ውሃ ቀድታ ስትመለስ ከድልድይ ላይ ወድቃ ሕይወቷ እንዳለፈ ይናገራሉ።
"ቁጥራችን ትንሽ ስለሆነ ነው መሰል ትዝ አንላቸውም" የሚሉት አቶ ገብሬ አካል ጉዳትን በተመለከተ 'ደረጃው ይለያያል እንጂ ያልተነካ አለ' ለማለት እንደሚቸገሩ ይናገራሉ።
ከአባላቶቻቸው በጥቆማ ያገኙትንና ሰኞ እለት ያጋጠመው ይህን አደጋ በተመለከተ ማህበሩ የተለያዩ መረጃዎች እያሰባሰበና የሚመለከተውን አካል ለማነጋገር ዝግጅት እያደረጉ መሆናቸውን ለቢቢሲ ገልፀዋል።
አደጋው በርካቶችን አስቆጥቷል። የህግ ባለሙያዋና የአካል ጉዳተኞች መብት ተሟጋቿ ሎሬት የትነበርሽ ንጉሴም በፌስቡክ እንዲሁም በትዊተር ገጿ ላይ ቁጣዋን አስፍራለች።
ይህ ጽሑፍ በX. የቀረበ ይዘት ይዟል። ገጹ ቴክኖሎጂዎች ወይም ኩኪዎች ሊኖረው ስለሚችል ገጹ ከመከፈቱ በፊት የእርስዎን ፍቃድ እንጠይቃለን። ፍቃድዎን ከመስጠትዎ በፊት የX ኩኪ ፖሊሲ እና የ ማንበብ ይፈልጉ ይሆናል። ይዘቱን ለማንበብ ‘እቀበላለሁ ቀጥል’ የሚለውን ይምረጡ።
የ X ይዘት መጨረሻ
ቢቢሲ ያነጋገራቸው የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ፖሊስ ፅ/ቤት የወንጀልና የትራፊክ አደጋ ክፍል ኃላፊ ኮማንደር ተስፋየ ወሰንየለህ አደጋው ሰኞ ጠዋት ከ 3፡00-4፡00 ሰዓት ባለው ጊዜ እንዳጋጠመ ገልፀውልናል።
ተመራቂው ዐይነ ሥውር የሥራ ምደባ ቦታውን ለማስለወጥ በክፍለ ከተማው ውስጥ ትምህርት ቢሮ አምርቶ እንደነበርም ያረጋግጣሉ።
"ከ7ኛ ፎቅ ወደ 3ኛ ፎቅ ለመውረድ በሚሞክርበት ሰዓት ነው የወደቀው" የሚሉት ኃላፊው ከነበረበት 7ኛ ፎቅ ወደ 3ኛ ፎቅ ስለተነገረው ወደዚያ ለመሄድ በሚሞክርበት ጊዜ አደጋው እንደደረሰበት ያስረዳሉ።
ኮማንደሩ እንደሚሉት አሳንሰሩን ሌሎች ሰዎች እየተገለገሉበት ስለነበር በእንቅስቃሴ ላይ ነበር። ይሁን እንጂ ግለሰቡ አሳንሰሩ የቆመ መስሎት በሩን ከፈተው። አሳንሰሩ በእንቅስቃሴ ላይ ስለነበር እርሱ ያለበት ቦታ ላይ የአሳንሰሩ ወለል አልነበረምና ጉድጓዱ ውስጥ እንደገባ ያብራራሉ።
የክፍለ ከተማው ህንፃ በዚህ ዓመት አገልግሎት መስጠት የጀመረ ሲሆን አሳንሰሩ ብዙ ጊዜ ብልሽት እንደሚያጋጥመው ለቢቢሲ ገልፀዋል።
የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በጉዳዩ ላይ ምርመራ እያደረገ መሆኑንም ኮማንደሩ አክለዋል።















