"እንደተወለድኩ ሊገድሉኝ ነበር፤ ዛሬ ገጣሚ ሆኛለሁ"

የተወለደችው በሕንድ ገጠራማ አካባቢ ነው። ኩሊ ኮሂል ትባላለች። ሰረብራል ፓላሲ ከተባለ ህመም ጋር የተወለደችው ኩሊ በሕይወት መትረፏ እድለኛ ያስብላታል።
ህመሙ ሰውነት እንዳይንቀሳቀስ ያደርጋል። የኩሊ ቤተሰብ ጎረቤቶች ልጅቷ ህመምተኛ ስለሆነች ወንዝ ውስጥ ትጣል ብለው ነበር። ቤተሰቦቿ ግን ወደ ዩናይትድ ኪንግደም ወሰዷት።
ወንዝ ውስጥ ትጣል የተባለችው ጨቅላ ዛሬ አድጋ ገጣሚ ሆናለች።
ያደገችበት ውልቨርሀምተን ውስጥ ግጥም ለማቅረብ መድረክ ላይ እስክትወጣ የጠበቀችበትን ቀን ታስታውሳለች። በጣም ፈርታ ነበር። ቃላት ከአፏ የሚወጡ አልመሰላትም።
አስተዋዋቂው ሲጋብዛት የመድረኩ መብራት እሷ ላይ አነጣጠረ። ታዳሚው አጨበጨበ።
ኩሊ እየተንቀጠቀጠች ድምጽ ማጉያውን አነሳች። ለመጀመሪያ ጊዜ ግጥሟን በአድማጭ ፊት ያነበበችው ያን ዕለት ነበር።
ህመሟ ንግግሯን፣ እንቅስቃሴዋን፣ የሰውነቷን ሚዛን ያውካል።
መድረክ ላይ ወጥታ ግጥሟን ማንበቧ፤ አካል ጉዳተኛ በመሆኗ ሕይወቷ ዋጋ እንደሌለው የነገሯትን ሰዎች ድል የምትነሳበት መንገድ ነበር።
“እናቴእንድትጥለኝይነግሯትነበር”
ኩቲ በአውሮፓውያኑ 1970 ኡታር ፕራደሽ የተባለ መንደር ውስጥ ነው የተወለደችው። እናቷ እሷን ሲወልዱ 15 ዓመታቸው ነበር።
ኩሊ የበኩር ልጅ ናት። በእሷ ምትክ ወንድ ባለመወለዱ ማኅበረሰቡ ተበሳጭቶ ነበር። ሰውን ያስቆጣው ሴት መሆኗ ብቻ እንዳልነበረ ትናገራለች።
“ልዩ ስለሆንኩ እንደ እንግዳ ፍጥረት ያዩኝ ነበር። ማንም እንደኔ አይነት ሴት ሊያገባ ስለማይችል እናቴ እንድትጥለኝ ይነግሯት ነበር። በመንደሩ ስለ አካል ጉዳት ግንዛቤ አልነበረም። ችግሬ ምን እንደሆነ የተረዳ አልነበረም። ለቤተሰቦቼ የቀደመ ሕይወት ቅጣት እንደሆንኩ ይነገራቸው ነበር።”
የመንደሩ ነዋሪዎች ወንዝ ውስጥ ተጥላ እንድትሰጥም ይፈልጉ ነበር። ሕይወቷን ያተረፉት አባቷ ናቸው። "ወስደው እንደ እቃ ሊጥሉኝ ሲሉ አባቴ አዳነኝ" ትላለች ኩቲ።
በዚያ መንደር ውስጥ ልጃቸው ልትኖር እንደማትችል የተረዱት ቤተሰቦች ወደ ዩናይትድ ኪንግደም ተሰደዱ። ያኔ ሁለት ዓመት ተኩል ነበረች።
አባቷ የአውቶብስ ሹፌር ሆኑ።
ኩሊ ዩናይትድ ኪንግደም ሄዳም ሕይወት አልጋ ባልጋ አልሆነላትም። በዙርያዋ ያሉ ሰዎች "እርግማን ናት" ብለው ማሰባቸው ነገሮችን አክብዶባታል።
"ብዙዎች አካል ጉዳተኞች እንደ ማንኛውም ሰው መውጣት፣ መማር፣ ማግባት ወዘተ የሚችሉ አይመስላቸውም" ስትል መድልዎውን ትገልጻለች።
በዩናይትድ ኪንግደም የእስያ ተወላጅ አካል ጉዳተኞችን የሚደግፈው ተቋም፤ አካል ጉዳት ለቀደመ ሕይወት ቅጣት ነው ተብሎ መታሰቡ፤ አካል ጉዳተኞች እንዲገለሉ ምክንያት ሆኗል ይላል።

ኩሊ የተማረችው በአካል ጉዳተኞች ትምህርት ቤት ውስጥ ነው። ከትምርት ቤቱ ውጪ መገለል ይሰማት እንደነበር ታስታውሳለች።
"አካል ጉዳተኛ ብለው ሌሎች ልጆች ይጠሩኛል። ቃሉን እጠላዋለሁ። ይጠቋቆሙብኛል፣ ያፈጡብኛል። ቤተ አምልኮ ስንሄድ ራሱ ሰዎች ያዩኛል። ምንም የማልረባ እንደሆንኩ እንዲሰማኝ ያደርጉኛል። ልጆች ለምን እንደዛ ትራመጃለሽ? ለምን እንደዛ ታወሪያለሽ? ይሉኛል።"
እድሜዋ እጨመረ ሲመጣ ከሰው ጋር ለመግባባት ትቸገር ጀመር።
በንግግር መግባባት ሲያቅታት ወደ ጽሑፍ ተሸጋገረች። አስተማሪዎች ግጥም ሲያነቡ ደስ ይላት እንደነበር ታስታውሳለች።
“ከዚያ እፎይታ ለማግኘት ግጥም መጻፍ ጀመርኩ። ስለ ስሜቴ መጻፍ፣ ቃላት ማገጣጠም ደስ ይለኝ ጀመር።"
"የምጽፈውእፎይታለማግኘትናለመዝናናትምነው"
በ13 ዓመቷ ወደ መደበኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ገባች። ከክፍል ጓደኞቿ ጋር ስትግባባ፣ በሥነ ጽሑፍ ስትገባም ነገሮች መሻሻል አሳዩ።
"የምጽፈው እፎይታ ለማግኘትና ለመዝናናትም ነው። አካሌ ላይ ጉዳት ቢኖርም አዕምሮዬ ይሠራል። ይሰማኛል፣ አስባለሁ። መጻፍ ኃይል ሰጠኝ።"
ኩሊ ትምህርት ቤቷን ወዳው ነበር። ግን ፈተና ትወድቅ ስለነበር አዘነች። በ16 ዓመቷም ከትምህርት ቤት ስለወጣች ዩኒቨርስቲ ላልገባ እችላለሁ ብላ ቅር ተሰኘች።
ያኔ ቤተሰቦቿ ሊድሯት መዘጋጀት ጀመሩ።
"ቤተሰቦች ለልጃቸው እንደምመጥን ለማየት ይመጡ ነበር። ባህላዊ ልብስ ለብሼ እጠብቃቸዋለሁ። ሲያዩኝ ‘ልጃችን እሷን እንዲያገባ ነው የምትፈልጉት’ ይሉና ወጥተው ይሄዳሉ።"
“አካል ጉዳተኛ አይደለም። የእኔ ጉዳትም ግድ አልሰጠውም"
ግጥም እንደምትጽፍ ማንም አያውቅም ነበር። አንድ ቀን ግን ሰዎች እንደሚያነቡት ተስፋ ታደርግ ነበር። ሰዎች ስለ ህመሟ እንዲረዱ ማድረግ እንጂ ከንፈር እንዲመጡ አትፈልግም።
የትዳር አጋሯን ያገኘችው በዚያ ወቅት ነበር።
"መጀመሪያ ብዙ አልወደድኩትም ነበር። ኋላ ላይ ግን ፍቅር ያዘኝ። እሱም ወደደኝ። አካል ጉዳተኛ አይደለም። የእኔ ጉዳትም ግድ አልሰጠውም።
ኩሊ የወጣቶች ሥልጠና ዘርፍ ላይ ሥራ ጀምራ፤ ወደ ውልቨርሀምተን የከተማ ምክር ቤት ገብታለች። ከ30 ዓመታት በላይም ሠርታለች።
አሁን በአርባዎቹ እድሜ ክልል ትገኛለች። ጥሩ ትዳርና ሦስት ልጆች አሏት።
"እንደ እናት፣ ሚስት፣ አማች፣ ሠራተኛ የሚጠበቅብኝ ነገር አለ። አካል ጉዳት ከሌለባቸው እናቶች የሚጠበቀው አይነት ሥራ ላከናውን አልችልም። ገበያ አለመውጣቴ፣ የልጆቼን ጫማ ማስር አለመቻሌም ያበሳጨኛል።"
"በጽሑፍ ስሜታቸውን የሚገልጹ. . .ሴቶች ጊዜ አባካኝ ተደርገው ይቆጠራሉ"
በከተማ ምክር ቤት ስትሠራ ከሥነ ጽሑፍ ክፍል ሠራተኛው ሳይመን ፍሌቸር ጋር ተገናኘች። ግጥሞቿና አጭር ልብ ወለዷ ላይ አስተያየት እንዲሰጣትም ጠየቀችው።
በጽሑፎቿ ውስጥ በሚነበበው ስሜት፣ ስብራት እና እውነተኛነት የተማረከው ሳይመን ጽሑፎቿን ለህትመት እንድታዘጋጅ አበረታታት።
ለብዙ ድምጽ አልባ ሴቶች ድምጽ እንደምትሆን ያምናል። እሷም ስሜታቸውን ለመግለጽ የሚከብዳቸው ሴቶችን ለማነሳሳት ቆረጠች።

“ዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ እንደኔ ያሉ የፑንጃብ [ህንድ ውስጥ ያለች ግዛት] ሴቶችን አውቃለሁ። ያንዳንዶቹ ሴቶች ህልም ሚስት፣ እናት፣ አያት፣ የልጅ ልጅ፣ አማች በመሆን ከስሟል። በጽሑፍ ስሜታቸውን የሚገልጹ የፑንጃብ ሴቶች ጊዜ አባካኝ ተደርገው ይቆጠራሉ። ልጅ መንከባከብ፣ ማብሰል ላይ እንድናተኩር ይፈለጋል። እኔ እድለኛ ሆኜ ከዚህ ቀንበር አምልጫለሁ።"
የፑንጃብ ሴት ጸሐፊዎች ማኅበር መስርታ፤ በየወሩ ይገናኛሉ። ራሳቸውን በነፃነትም ይገልጻሉ። ስለ ጠጪ ባሎች፣ የቤት ውስጥ ጥቃት እንዲሁም ስለ ሕይወት ውብ ነገሮችም ያወራሉ።
ለመጀመሪያ ጊዜ ግጥሟን መድረክ ላይ ያነበበችው ከሦስት ዓመት በፊት ነው። "ህልም አለኝ" ስትል ነበር ንባቧን የጀመረችው።
"ለ15 ደቂቃ ያህል ወደ 40 ሰዎች በተሰበሰቡበት ግጥሜን አነበብኩ። ትንሽ ቃላት ብገድፍም በቻልኩት መጠን በግልጽ ለማናገር ሞክሬያለሁ። አድማጩ ግጥሜት በትዕግስትና በጉጉት ነበር የተቀበለው። አካሌ ላይ ጉዳት ቢኖርም አዕምሮዬ፣ ልቤና ነፍሴ ያገለግላሉ። መድረክ ላይ የተዋጣላት አንባቢ ላልሆን እችላለሁ። ግን እሻሻላለሁ።"
የኩሊ በራስ መተማመን ለፑንጃብ ሴቶች ስብስብም መነሳሳት ፈጥሯል። አምና የቡድኑ አባላት ሥራዎቻቸውን በአንድ ፌስቲቫል ላይ አቅርበዋል።
የ49 ዓመቷ ኩሊ፤ ብዙ አሳልፋ እዚህ ደርሳለች። የደረሰችበትን ድምዳሜ እንዲህ ትገልጻለች፦
"የደረስኩበት ድምዳሜ አካል ጉዳት የመላው ማኅበረሰቡ ችግር እንደሆነ ነው። ማኅበረሰባችን አካል ጉዳተኞችን አይደግፍም። የግል ጉዳዮቻቸው እንዲሁም ችግሮቻቸውን በቁም ነገር የሚወስድ የለም። ጉዳዮቻቸውና ችግሮቻቸው ይድበሰበሳሉ። ሁላችንም በተወሰነ ደረጃ የአካል ጉዳት አለብን። ይህም ስለ አካል ጉዳት ያለን የተዛባ አመለካከት ነው። ይህን አመለካከት ለመቅረፍ በርካታ ትውልዶች ማለፍ አለብን።"














