አዲስ አበባ ፡ ሕገወጥ የመሬት ወረራ ላይ የወጣው ሪፖርትና የቀድሞው ምክትል ከንቲባ ምላሽ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ትናንት፣ ሰኞ፣ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) በአዲስ አበባ ከተማ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለያዩ ክፍለ ከተሞች እየተባባሰ የመጣ፣ የመንግሥታዊ መዋቅሮች ድጋፍ ያለው ሕገ-ወጥ የመሬት ወረራ እና የጋራ መኖሪያ ቤቶች ኢፍትሃዊ ዕደላ እንዳለ ባካሄድኩት ጥናት ደርሼበታለሁ ሲል ማስታወቁ ይታወሳል።
የቀድሞው የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ እና የአሁኑ የማዕድን ሚኒስቴር ሚኒስትር ታከለ ኡማ (ኢንጂነር) በበኩላቸው በቀጥታ የኢዜማን ጥናት ባይጠቅሱም ምላሽ ሰጥተዋል።
አቶ ታከለ በፌስ ቡክ ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት መልዕክት እንዳሉት "የመሬት ወረራን በተመለከተ ከመጀመሪያዋ ቀን ጀምሮ እስከ መጨረሻዋ እለት ድረስ ጠንካራ የሆነ እርምጃ ስንወስድበት የቆየንበት ጉዳይ ነው።" ብለዋል።
አቶ ታከለ አክለውም ለ20ሺህ አርሶ አደሮች የተሰጡ የኮንዶሚኒየም ቤቶች በተመለከተም ከአንድ አመት ተኩል በፊት በካቢኔ የተወሰነና የተተገበረ መሆኑን በዚሁ መልዕክታቸው ላይ አስፍረዋል።
የሚፈልጉት ይዘት የለም
በ Facebook ተጨማሪ ይመልከቱቢቢሲ ከሌሎች ድረ-ገጾች ለሚመጡ መረጃዎች ሀላፊነት አይወስድም.የ Facebook ይዘት መጨረሻ
ተግባሩ በይፋ የተከናወነ መሆኑን በማንሳትም ከመሬታቸው ላይ ተፈናቅለው በዝቅተኛ ስራ ላይ ተሰማርተው የነበሩ 67 ሺህ አባወራዎች እንደነበሩ በመጥቀስ ከእነርሱ መካከል "የከፋ ችግር ላይ ለወደቁት 20 ሺህ ኮንዶሚንየም" መሰጠቱን አንስተው ተግባሩንም " ቢያንስ እንጂ የሚበዛ አይደለም።" ብለዋል።
በተጨማሪም በዚህ ተግባራቸው እንደሚኮሩ ገልፀው "በግፍ የተገፋን፣ በግፍ ከመሬቱ የተፈናቀለን አርሶ አደር መካስ ያኮራናል!" ብለዋል።
አቶ ታከለ በፌስቡክ መልዕክታቸው ኢዜማን ባያነሱም " አንድም ቀን በግፍ ለተፈናቀሉ አርሶአደሮች የመቆርቆር ስሜት አሳይቶ የማያውቅ ቡድን ዛሬ የአርሶአደሮችን ጉዳት ለተቀባይነት ማግኛ መጠቀሚያ ሲያደርገው ማየት " ብለዋል።
በተጨማሪም "በሀሰተኛ መረጃ ድካማችንና ስራችንን ለማጠልሸት ቢሞከርም ስራችን ይናገራልና ፍርድ የህዝብ ነው!" ሲሉ መልዕክታቸውን አጠቃልለዋል።
የኢዜማ የጥናት ሪፖርት ምን ነበር?
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) በአዲስ አበባ ከተማ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለያዩ ክፍለ ከተሞች እየተባባሰ የመጣ፣ የመንግሥታዊ መዋቅሮች ድጋፍ ያለው ሕገ-ወጥ የመሬት ወረራ እና የጋራ መኖሪያ ቤቶች ኢፍትሃዊ ዕደላ እንዳለ ባካሄድኩት ጥናት ደርሼበታለሁ ብሏል።
ፓርቲው እዚህ ውጤት ላይ ለመድረስ ያስቻለውን ጥናት ያደረገው ከኅብረተሰቡ የመሬት ወረራን እና ሕገ ወጥ የቤት እደላን አስመልክቶ የተሰጡ ጥቆማዎችና በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን የቀረቡ ዘገባዎች መሰረት በማድረግ ኮሚቴ አዋቅሮ ባደረገው ምርመራ መሆኑን ጠቅሷል።
በተለያዩ መንገዶች በተደረጉ የመረጃ ማሰባሰቢያ ዜዴዎች አማካይነት ኢዜማ በተጨባጭ አረጋግጨዋለሁ እንዳለው "ታይቶ በማይታወቅ መጠንና ስፋት ግልፅ የሆነ የመሬት ወረራ እና ሕገ-ወጥ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ዕደላ ተድርጓል" ብሏል።
በዚህ መልኩ የተያዙ ቦታዎችም ሕጋዊ ይዘት እንዲኖራቸው የሚያስፈልጋቸው ሰነዶች እንደተዘጋጁላቸው እንደደረሰበት የሚገልጸው የፓርቲው የጥናት ውጤት የከተማው አስተዳደር አካላትም ይህን ሂደት እንደሚያወቁ ጠቅሷል።
ቢቢሲ በኢዜማ የቀረበውን ይህንን የጥናት ውጤት መሰረት በማድረግ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሚሰጠው ምላሽን ለማግኘት ያደረገው ጥረት ለጊዜው አልተሳካም።
ኢዜማ በጥናቱ ላይ "የከተማው አስተዳደር እያየና እየሰማ በሕገ-ወጥና በተደራጀ መልኩ በወረራ የተያዙ ቦታዎች በፍጥነት ካርታና ፕላን ተሰርቶላቸው ለሦስተኛ ወገን በሽያጭ ተላልፈዋል በማኅበርና በግል ለማምረቻና ለንግድ አገልግሎት እንዲውሉ ተደርገዋል" ብሏል።
የጋራ ቤቶችን በተመለከተም የከተማው አስተዳደር ባወጣው ደንብ መሰረት "በምንም መስፈርት የቤት ተጠቃሚ ሊሆኑ የማይገባቸው ግለሰቦችና ቡድኖች ቤትና የነዋሪነት መታወቂያ ተሰጥቷቸዋል" ሲል በጋራ የመኖሪያ ቤቶች በኩል አሉ ያላቸውን የአሰራር ችግሮች ጠቅሷል።
ጥናቱ እንዳለው በከተማዋ የተለያየ አይነት ሕገ-ወጥ የመሬት ወረራ ተግባራት እንደተከናወኑ አመልክቶ፣ እነዚህም በጅምር ቤት ስም ከባለ ይዞታዎች ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ በመግዛት ግንባታ የማካሔድ፣ ባዶ መሬቶችን በቡድንና በግለሰብ ደረጃ በማጠር የመያዝ እንዲሁም ለሌላ ወገን የማስተላለፍ በተጨማሪም "በመንግሥት መዋቅር ውስጥ በተዘረጋው ሰንሰለት በጥቅም ተጋሪነትና በዝምድና" ሠፋፊና ቁልፍ ቦታዎችን መያዝ በከተማዋ ውስጥ መታየቱን ገልጿል።
ፓርቲው በጥናት አገኘሁት እንዳለው በመሬት ወረራው ላይ ግንባር ቀደም ተሳታፊ የነበሩት ሰዎች፣ 'ቦታዎቹ ከዚህ ቀደም የቤተሰቦቻችን ናቸው፤ በቂ ካሳ ሳይከፈለን ከቦታችን ተነስተናል' የሚሉ ግለሰቦችና ወረራ የተፈፀመባቸው አካባቢ ላይ የሚገኙ "የክፍለ ከተማና የወረዳ ኃላፊዎችና ፈፃሚዎች ናቸው" ብሏል።
ጨምሮም በተደራጀ መልኩ የተፈፀመው የመሬት ወረራ በመንግሥት ሥልጣን ላይ ያሉ አመራሮች የተሳተፉበት እንደሆነና "ግለሰቦች፣ ቡድኖች እና አደረጃጀቶች መሬቱን ወርረው እንዲይዙ አመቻችተዋል፤ የመንግሥትን ሥልጣንንም ለሕገ ወጥ ተግባር ከለላ እና ሽፋን እንዲሆን አድርገዋል" በማለት ጠቅሷል።
ከዚህ ባሻገርም ፓርቲው ያደረገው ጥናት የጠቀሳቸው የመንግሥት አካላት ሕገ-ወጥ የሆኑ የግንባታ ፈቃዶች፣ ካርታ እና ልዩ ልዩ ሰነዶችን ለማይገባቸው ግለሰቦችና ቡድኖች በማዘጋጀት ሕገ ወጥ ድርጊቶቹ ሕጋዊ መስለው እንዲቀርቡ ከፍተኛ ተሳትፎ አድርገዋል በማለት ከስሷል።
ይህ ሕገ-ወጥ የመሬት ወረራ ተግባር በከተማዋ አዲስ አለመሆኑን ያመለከተው የኢዜማ ጥናት፣ አሁን በአዲስ አበባ ከተማ ከተስተዋለው ጋር ሲነጻጸር በዚህ ደረጃና ፍጥነት የተስፋፋበት ጊዜ አልነበረም።
በአሁኑ ጊዜ የተከሰተው የመሬት ወረራ የተከናወነባቸው ስፍራዎች ስፋት ከፍተኛ ከመሆኑም በላይ፣ ወረራው የከተሞችን አረንጓዴ ቦታዎች፣ የወንዝ ዳርቻዎች እንዲሁም ለመሰረተ ልማት አውታር ዝርጋታ በፕላን የተከለሉ ቦታዎችን ያካተተ በመሆኑ የጉዳቱ መጠን ከፍተኛ ነው ብሏል።
ኢዜማ ባደረገው ጥናት ላይ እንዳመለከተው፣ እንዲህ አይነቱ የመሬት ወረራ በስፋት የተከሰተው በከተማዋ ዳርቻ ላይ ባሉ ቦታዎች ላይ ሲሆኑ በአምስት ክፍለ ከተሞች የሚገኙ የተወስኑ ቦታዎችን በመዳሰስ የተለያዩ ማሳያዎችን አስቀምጧል። እነዚህም ንፋስ ስልክ ላፍቶ፣ የካ፣ ቦሌ፣ ኮልፌ ቀራኒዮና አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተሞች ናቸው።
ጥናቱ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን አሰጣጥ በተመለከተ "የመንግሥት ሕገ ወጥ ተግባር በግልጽ ታይቷል" ብሏል። ለዚህም ኢፍትሐዊ ሕጎችንና መመሪያዎችን በማውጣት፣ ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ ሕጎችንና ደንቦችን በማሻሻል ለካቢኔውና ለከንቲባው በተሰጠ ልዩ ሥልጣን "ከንቲባውም ሆነ ካቢኔያቸው ቤቶችን እንደፈለጉ እንዲያድሉ ምክንያት ሆኗል" ሲል ጠቅሷል።
"በዚህም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኢፍትሐዊ በሆነ መልኩ ፈጽሞ ኮንዶሚኒየም ቤቶች ለማይገባቸው ግለሰቦችና ቡድኖች ቤት የማስተላለፍ ተግባር እንደፈፀመና እየፈጸመ መሆኑን አረጋግጠናል" ብለዋል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘም የኦሮሚያ ክልል የመንግሥት ሠራተኞች ከአሁን ቀደም ቦታና ኮንዶሚኒየም የተሰጣቸው ቢሆንም በአሁኑ ወቅት ደግሞ ድጋሚ በአዲስ አበባ የጋራ መኖሪያ ቤቶች እየታደላቸው መሆኑን እንዳረጋገጡ ጠቅሰዋል።
"በዚህ መሠረትም ከኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ቢሮዎች ሳር ቤት አካባቢ ከሚገኘው ጽሕፈት ቤት ሁሉም የተመዘገቡ ሠራተኞች በሰኔ ወር ላይ በሺዎች የሚቆጠሩ ቤቶች የድልደላ እጣ የወጣላቸው ሲሆን፣ ሁሉም ሠራተኞች የኮንዶሚኒየም ብሎክ ቁጥርና የቤቱን ቁጥር በስማቸው ተረጋግጦ የተሰጣቸው ሲሆን የነዋሪነት መታወቂያ የተዘጋጀላቸው" መሆኑን ገልጿል።
ጥናቱ ጨምሮም "የጋራ መኖሪያ ቤቶች ሕንጻዎች ውስጥ የተሠሩ የንግድ ቤቶች በተመለከተ የልማት ተነሺ አርሶ አደሮች፣ ልጅና የልጅ ልጅ ተብለው በገፍ ስለመታደላቸው፤ በእግር ኳስ ደጋፊነት ስም ለተሰባሰቡ ማኅበራት መከፋፈላቸው ተጨባጭ ማስረጃዎች ተገኝተዋል" ሲል በሪፖርቱ ላይ ገልጿል።
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ተከስቷል ስላለው ሕገወጥ የመሬት ወረራ እና የጋራ መኖሪያ ቤቶች ኢፍትሃዊ ዕደላን በተመለከተ ጥናት አድርጎ ያገኘውን ውጤት ይፋ ባደረገበት ዘገባው ላይ መደረግ ስላለባቸው የማስተካከያ እርምጃዎች የመፍትሔ ሃሳብ አቅርቧል።
ፓርቲው በጥናት አገኘሁት ያለውን ይህንን ውጤት ይፋ ለማድረግ ባለፈው አርብ እንዲሁም ሰኞ የጠራው ጋዜጣዊ መግለጫ ፓርቲው ማሟላት የነበረበትን ቅድመ ሁኔታ አላሟላም በሚል በፖሊስ እንዳይካሄድ መደረጉ ይታወሳል።














