አሜሪካ ከአፍጋኒስታን ከወጣች በኋላ ከታሊባን ጋር በዶሃ ያደረገችው ውይይት ተጠናቀቀ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አሜሪካ ባለፈው ነሐሴ አፍጋኒስታንን ጥላ ከወጣች በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ከታሊባን ጋር በኳታር ዶሃ ያካሄደችውን ውይይት አጠናቀቀች።
ኳታር ውስጥ የተደረገው ውይይት ዋነኛ ትኩረቱ አክራሪ ኃይሎችን መግታት፣ አሜሪካዊያን ዜጎችን ማስወጣትና ሰብዓዊ እርዳታ ማቅረብ ነበር ተብሏል።
የአሜሪካ ባለሥልጣናት ምንም እንኳ ቡድኑ በሥራው የሚገመገም ቢሆንም የተደረጉት ውይይቶች ግን "ከልብ የመነጩና ሙያዊ" ነበሩ ብለዋል።
ዩናይትድ ስቴትስ ከታሊባን ጋር ውይይት ማድረጓ ለቡድኑ እውቅና መስጠት እንዳልሆነ ትናገራለች።
ታሊባን እሑድ አመሻሹን በለቀቀው መረጃ አሜሪካ ሰብዓዊ እርዳታ ለአፍጋኒስታን ለማቅረብ መስማማቷን ገልጿል።
"የዩኤስ ተወካዮች እንዳሉት ለአፍጋናውያን የሰብዓዊ እርዳታ ያቀርባሉ፤ ለሌሎች የዕርዳታ ድርጅቶች ደግሞ ድጋፍ ያደርጋሉ" ይላል የታሊባን መግለጫ።
ነገር ግን ዩናይትድ ስቴትስ በዚህ ጉዳይ እስካሁን አስተያየት አልሰጠችም።
ቃል አቀባይ ኔድ ፕራይስ ሁለቱ አካላት ስለ ሰብዓዊ እርዳታ አቀራረብ አውርተዋል፣ ከማለት ውጭ ዝርዝር መረጃ ከመስጠት ተቆጥበዋል።
ታሊባን፤ ኢስላሚክ ስቴት ኢን ኮራሳን ፕሮቪንስ የተሰኘውን ቡድን ለመግታት ከአሜሪካ ጋር ቃል አልገባሁም ብሏል።
ነገር ግን ዶሃ የሚገኙት የታሊባን ቃል አቀባይ ሱሄል ሻሂን አሶሺዬትድ ፕሬስ ለተሰኘው የዜና ወኪል፤ ቡድናቸው ብቻውን አይኤስን [ዳዒሽ] መግታት እንደሚችል ተናግረዋል።
ኢስላሚክ ስቴት ኢን ኮራሳን ፕሮቪንስ የተሰኘው ቡድን ባለፈው አርብ በሰሜናዊ አፍጋኒስታን በምትገኘው ኩንዱዝ ከተማ አንድ መስጅድ ላይ ጥቃት አድርሶ 50 ሰዎች መሞታቸው ተዘግቧል።
የተባበሩት መንግሥታት ጥቃቱን አስመልክቶ "በዚህ ሳምንት በሃይማኖታዊ ተቋም ላይ ያነጣጠረ ሦስተኛ ገዳይ ጥቃት ነው። ይህ የሚያሰቅቅ የአመፅ ዘይቤ አካል ነው" ብሏል።
በታሊባን የተሾሙት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አሚር ካን ሙታኪ ከአሜሪካ ጋር ያደረጉት ውይይትን አስመልክቶ ሁለቱ ወገኖች በ2020 የተፈረመውን የዶሃ ስምምነት ውል ለማክበር መስማማታቸውን ተናግረዋል።
ይህ የዶሃ ስምምነት እንደ አልቃይዳ ያሉ ቡድኖች የአሜሪካን እና የአጋሮቿን ደህንነት አደጋ ላይ እንዳይጥሉ እርምጃዎችን ለመውሰድ ሰፊ ግዴታዎችን በታሊባን ላይ ጥሏል።












