የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከምርጥ 200 አየር መንገዶች 20ኛ ደረጃ ላይ ተቀመጠ

የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን

የፎቶው ባለመብት, Anadolu Agency

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ባጓጓዘው የመንገደኛ ብዛት ከምርጥ 200 አየር መንገዶች 20ኛ ደረጃ ላይ መቀመጡን አለም አቀፍ የትራንስፖርት ማህበር አስታውቋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ይህንን ስፍራ ያገኘው ከ16 ሚሊዮን በላይ መንገደኞች በማጓጓዝ መሆኑን አየር መንገዱ ማህበሩን ዋቢ አድርጎ ካገኘው መረጃ መረዳት ተችሏል።

በዚህ የደረጃ መስፈርት መሰረት በአንደኛ ደረጃ የተቀመጠው የኤምሬትስ አየር መንገድ ሲሆን 78 ሚሊዮን 746 ሺህ መንገደኞችን አጓጉዟል።

በሁለተኛ ደረጃ የተቀመጠው የአየርላንዱ ራይኔይር በበበኩሉ 64 ሚሊዮን 928 ሺህ መንገደኞችን ማጓጓዙ ተገልጿል።

በሶስተኛ ደረጃ የተቀመጠው የኳታር አየር መንገድ 57 ሚሊዮን 171 ሺህ መንገደኞችን ማጓጓዙን ከድረ-ገፁ የተገኘው መረጃ ያስረዳል።

የኮሮናቫይረስ ክፉኛ ከጎዳቸው ዘርፎች መካከል የአየር ትራንስፖርት አንዱ ሲሆን፤ በዓለም ዙሪያ ያሉ በርካታ አየር መንገዶች ሠራተኞቻቸውን ከመቀነስ አንስቶ ከበረራ ውጪ አስኪሆኑ ድረስ ጉዳት አድርሷል።

በአፍሪካ ውስጥ የሚገኙ አየር መንገዶች በባለፈው አመት ቀውስ ውስጥ የገቡና ሥራ ለማቆም የተገደዱ ያሉ ሲሆን፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግን ጭነቶችን በማመላለስ አስቸጋሪውን ጊዜ ለማለፍ እንደቻለ ተነግሯል።

በባለፈው አመት በአምስት ወራት ውስጥ በኮሮናቫይረስ ምክንያት በአየር ትራንስፖርት ዘርፉ ላይ በተፈጠረው መስተጓጎል ሳቢያ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አንድ ቢሊዮን ዶላር ገቢ አጥቷል ተብሏል።

የኮሮናቫይረስ ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ በአየር መንገዶች ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ ቀውስ ማምጣቱን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈፃሚው አቶ ተወልደ ገብረ ማርያም ለቢቢሲ ተናግረው ነበር።

በዚያን ወቅት ከ90 በመቶ በላይ የመንገደኛ በረራዎች መቆማቸውን ለቢቢሲ የተናገሩት ዋና ሥራ አስፈፃሚው፣ በባለፈው አመት ከየካቲት እስከ ሰኔ መጨረሻ ድርጅቱ መንገደኛ በማጓጓዝ ሊያገኘው ይገባ የነበረው ወደ አንድ ቢሊየን ዶላር ገቢ ሳያገኝ መቅረቱን ገልፀዋል።

በአሁኑ ወቅት ከኮሮናቫይረስ ስጋት ጋር ተያይዞም የመንገደኞች ደኅንነት ስጋት በሆነበትም ወቅት አየር መንገዱ አስፈላጊውን ለውጦች በማካሄድ የመንገደኞች ደኅንነትን ማስጠበቅ ዋናና ቀዳሚ ተግባሩ መሆኑንም ማስታወቁ የሚታወስ ነው።

በአፍሪካ ትልቁና ፈር ቀዳጅ የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለመንገደኞቹ የኮቪድ-19 ኢንሹራንስ ከመስከረም 21/2013 ዓ.ም መጀመሩን አስታውቋል።

የኢንሹራንስ ሽፋኑ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ለሚጓዙ ዓለም አቀፍ መንገደኞች በሙሉ ሲሆን፤ መንገደኞችን መመለስ፣ ለይቶ ማቆያና ሌሎችም የህክምና ወጪዎችን እንደሚሸፍን አየር መንገዱ ማስታወቁ ይታወሳል።

'ሼባ ኮምፎርት' የሚል ስያሜ የተሰጠው ይህ ኢንሹራንስ መንገደኞች በኢትዮጵያ አየር መንገድ ተሳፍረው በጉዟቸው ወቅት በኮቪድ-19 ቢያዙ የህክምና ወጪያቸው እስከ አንድ መቶ ሺህ ዩሮ ድረስ ይሸፈንላቸዋል።

ከዚህም በተጨማሪ ለለይቶ ማቆያም በየቀኑ 150 ዩሮ፣ ለአስራ ቀናትም ያህል እንደሚሸፈንላቸው ከአየር መንገዱ የተገኘው መረጃ ያስረዳል።

በአለም ላይ ስመ ጥር ከሆኑት መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ እንደ አውሮፓውያኑ በ1945 ሥራ የጀመረው በአሜሪካ ሠራሽ አውሮፕላኖች ነበር።

በጊዜው አየር መንገዱን ከከፈቱት ዐፄ ኃይለሥላሴ ጋር በተደረገ ስምምነት አየር መንገዱ ያቋቋመው ዛሬ ላይ ገበያ ላይ የሌለው የአሜሪካኑ TWA (Trans World Aviation) ነበር።