ኮሮናቫይረስ ፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለመንገደኞቹ የኮቪድ-19 ኢንሹራንስ ሽፋን ጀመረ

የኢትዮጵያ አየር መንገድ

የፎቶው ባለመብት, KOLA SULAIMON

በአፍሪካ ትልቁና ፈር ቀዳጅ የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለመንገደኞቹ የኮቪድ-19 ኢንሹራንስ ከመስከረም 21/2013 ዓ.ም መጀመሩን አስታውቋል።

የኢንሹራንስ ሽፋኑ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ለሚጓዙ ዓለም አቀፍ መንገደኞች በሙሉ ሲሆን፤ መንገደኞችን መመለስ፣ ለይቶ ማቆያና ሌሎችም የህክምና ወጪዎችን እንደሚሸፍን አየር መንገዱ ባወጣው መግለጫ አስፍሯል።

'ሼባ ኮምፎርት' የሚል ስያሜ የተሰጠው ይህ ኢንሹራንስ መንገደኞች በኢትዮጵያ አየር መንገድ ተሳፍረው በጉዟቸው ወቅት በኮቪድ-19 ቢያዙ የህክምና ወጪያቸው እስከ አንድ መቶ ሺህ ዩሮ ድረስ ይሸፈንላቸዋል።

ከዚህም በተጨማሪ ለለይቶ ማቆያም በየቀኑ 150 ዩሮ፣ ለአስራ ቀናትም ያህል እንደሚሸፈንላቸው ከአየር መንገዱ የተገኘው መረጃ ያስረዳል።

አየር መንገዱ የመንገደኞቹን ጤናና ደኅንነት ለመጠበቅና ያለምንም ሃሳብ በሰላም እንዲጓዙ ለማድረግም ይህንን የኢንሹራንስ ሽፋን መጀመሩን አስታውቋል።

ዓለም አቀፉ የኢንሹራንስ ሽፋኑንም በተመለከተ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ተወልደ ገብረ ማርያም እንዳሉት

"በዓለም ላይ ጥብቅ የደኅንነት መከላከያን በማስተወቅ ቀዳሚ ከሆኑት አየር መንገዶች አንዱ በመሆኑ ደስተኞች ነን። የኮቪድ-19 ዓለም አቀፉን ኢንሹራንስ ሽፋን በመስጠት የመንገደኞቻችንም በራስ መተማመንን እንጨምራለን" ማለታቸውንም መግለጫው አስፍሯል።

በአሁኑ ወቅት ከኮሮናቫይረስ ስጋት ጋር ተያይዞም የመንገደኞች ደኅንነት ስጋት በሆነበትም ወቅት አየር መንገዱ አስፈላጊውን ለውጦች በማካሄድ የመንገደኞች ደኅንነትን ማስጠበቅ ዋናና ቀዳሚ ተግባሩ መሆኑንም አሳውቋል።

ሼባ ኮምፎርት ኢንሹራንስ ከአክሳ ፓርትነርና አዋሽ ኢንሹራንስ ኩባንያ ጋር በመጣመር ሽፋኑን የሚሰጥ ሲሆን፤ ኢንሹራንሱም ለደርሶ መልስ ቲኬት ለ92 ቀናት አንድ ጉዞ 31 ቀናትን የሚሸፍን ይሆናል።

ይህ አየር መንገዱ ለተጓዞቹ ያቀረበው ኢንሹራንሱ ሽፋንም ከመስከረም 21/2013 ዓ.ም እስከ መጋቢት ድረስ የሚቆይ ይሆናል።

የኮሮናቫይረስ ክፉኛ ከጎዳቸው ዘርፎች መካከል የአየር ትራንስፖርት አንዱ ሲሆን፤ በዓለም ዙሪያ ያሉ በርካታ አየር መንገዶች ሠራተኞቻቸውን ከመቀነስ አንስቶ ከበረራ ውጪ አስኪሆኑ ድረስ ጉዳት አድርሷል።

በአፍሪካ ውስጥ የሚገኙ አየር መንገዶች ባለፉት ስድስት ወራት ቀውስ ውስጥ የገቡና ሥራ ለማቆም የተገደዱ ያሉ ሲሆን፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግን ጭነቶችን በማመላለስ አስቸጋሪውን ጊዜ ለማለፍ እንደቻለ ተነግረዋል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አገራት ለአየር ትራንስፖርት በራቸውን እከፈቱ ቢሆንም የኮሮናቫይረስ ስጋት የፈጠረው ተጽእኖ እስካሁን አልተቃለለም።