ኮሮናቫይረስ፡ የአፍሪካ አየር መንገዶች በዚህ ዓመት ብቻ 2 ቢሊዮን ዶላር ይከስራሉ

ጭንብል ያደረገ መንገደናኛ

የፎቶው ባለመብት, AFP

የአፍሪካ የአየር ትራንስፖርት ኢንዱስትሪ በዚህ ዓመት 2 ቢሊዮን ዶላር እንደሚከስርና ወቅቱ ለዘርፉ በታሪክ እጅግ መጥፎው እንደሚሆን ዓለም አቀፉ የአየር ትራንስፖርት ማኅበር ባወጣው ሪፖርት አስታወቀ።

በዚህም ሳቢያ የአፍሪካ አየር መንገዶች ባለፈው ታኅሳስ ወር ከተገመተው 200 ሚሊዮን ዶላር ኪሳራ ባሻገር በአጠቃላይ 2 ቢሊየን ዶላር ገቢ እንምደሚያጡ ተነግሯል።

በዓለም ደረጃ የአየር ትራንስፖርቱ ዘርፍ 84 ቢሊዮን ዶላር ይከስራል ተብሎ ተገምቷል።

የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመግታት አገራት ከወሰዷቸው እርምጃዎች መካከል አንዱ በሆነው በአየር ትራንስፖርት እገዳ ምክንያት ዘርፉ ክፉኛ ተዳክሟል።

በተጨማሪም በአፍሪካ ውስጥ በአየር ትራንስፖርቱ ዘርፍ ተሰማርተው የሚገኙ የሦስት ሚሊየን ሰዎች የሥራ ዕድልም ስጋት ውስጥ መውደቁም ተነግሯል።

አፍሪካ ውስጥ የሚገኙ አብዛኞቹ አየር መንገዶች ወረርሽኙ ከመከሰቱ በፊት ተጨማሪ አውሮፕላን ለመግዛት በሂደት ላይ የነበሩ ሲሆን፤ አሁን ግን ግዢዎችን የመሰረዝና የማዘግየት ውሳኔያቸውን እያስታወቁ ነው።

በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ኤርባስ የተባለው አውሮፕላን አምራች ኩባንያ አንዳንድ አየር መንገዶች አዘዋቸው በሂደት ላይ በነበሩ አውሮፕላኖች ምክንያት ክስ እንደሚመሰረት አስታውቋል።

በአፍሪካ ውስጥ ከፍተኛ ብዛት ያለው አውሮፕላን ከኤርባስ አዞ የነበረው አዲሱ የናይጄሪያ አየር መንገድ ግሪን አፍሪካ ኤር የተባለው ሲሆን 50 ኤ220 አውሮፕላኖችን ለመግዛት ትዕዛዝ ሰጥቶ ነበር።

ነገር ግን በወረርሽኙ በተፈጠረው ችግር ምክንያት በተፈጠረ የገንዘብ ችግር ምክንያት እየተንገዳገደ ያለው አየር መንገዱ እንኳን አዲሶቹን አውሮፕላኖች ለቀበል ይቅርና በሥራው ላይ ለመቆየት ሲል የተወሰነ ንብረቱን በመሸጥ ላይ ይገኛል።