የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላንን ወደ በረራ መለሰ

ET Boeing 737 Max 8

የፎቶው ባለመብት, ET

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሦስት ዓመታት ለሚተጋ ጊዜ ከበረራ አግዶት የነበረውን ቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላን ወደ አገልግሎት መለሰ።

አየር መንገዱ ዛሬ ጥር 23/2014 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ ላይ አውሮፕላኑ የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ የቦይንግ እና የአየር መንገዱ ቦርድ አባላትን አሳፍሮ ወደ በረራ ተመልሷል ብሏል።

አየር መንገዱ ባጋጠሙ አስከፊ አደጋ ምክንያት ከበረራ አግዷቸው የነበሩት አራት ቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላኖቹን ወደ መደበኛ የመንገደኞች በረራ በያዝነው ሳምንት እንደሚመልስ አስታውቆ ነበር።

ከአፍሪካ ትልቁ አየር መንገድ የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ያሉትን ዘመናዊ ቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላኖች ከበረራ ውጪ ካደረገ ሁለት ዓመት አልፎታል።

መጋቢት 01 ቀን 2011 ዓ.ም ጠዋት ከአዲስ አበባ ወደ ኬንያ ዋና ከተማ ናይሮቢ 149 ሰዎችን ይዞ ይበር የነበረው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላን የበረራ ቁጥር ET302 መከስከሱን ተከትሎ ነበር አውሮፕላኖቹ በመላው ዓለም ከበረራ ውጪ የሆኑት።

በኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ላይ ከደረሰው አደጋው ቀደም ብሎ በኢንዶኔዢያው ላየን ኤየር አየር መንገድ ተመሳሳይ ቦይንግ አውሮፕላን ላይ አደጋ አጋጥሞ የ181 ሰዎች ሕይወት ተቀጥፏል።

ከሁለቱ አደጋዎች በኋላ በመላው ዓለም የሚገኙ በርካታ አየር መንገዶች ቦይንግ 737 ማክስን 8 አውሮፕላኖችን ማብረር አቁመው ነበር።

አየር መንገዱ ዛሬ ባወጣው መግለጫ ላይ ከሁሉም በፊት ቅድሚያ የሚሰጠው ለደኅንነት ነው ብሏል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚው አቶ ተወልደ ገብረማሪያም አየር መንገዱ አውሮፕላኑን ወደ አገልግሎት ለመመለስ ከውሳኔ ላይ የደረሰው በዓለም ዙሪያ ያሉ የበረራ ደኅንነት ተቆጣጠሪ አካላት አውሮፕላኑ አስተማማኝ መሆኑን አረጋግጠው አስፈላጊውን ፈቃድ መስጠታቸውን ተከትሎ ነው ብለዋል።

ከዚህ በተጨማሪም በዓለም ዙሪያ ያሉ ሌሎች 36 አየር መንገዶች አውሮፕላኑን ወደ በረራ መመለሳቸውን ተከትሎ ዋና ሥራ አስፈጻሚው ገልጸዋል።

አየር መንገዱ አውሮፕላኑን ወደ መደበኛ አገልግሎት ከመመለሱ በፊት 'የሙከራ' ናቸው የተባሉ በራራዎችን አካሂዷል።

አየር መንገዱ አውሮፕላኑን ወደ አገልግሎት ከመመለሱ በፊት ያደረጋቸውን የሙከራ በረራዎችን ከፍላይት ራዳር24 እና ፍላይት አዌር ድረ-ገጾች በተገኘው መረጃ መሠረት አውሮፕላኑ በቅርቡ ጥር 17 እና ዛሬ ጥር 24/2014 ዓ.ም በረራዎችን አድርጓል።

እንደ ፍላይት አዌር ድረ-ገጽ ከሆነ ማክሰኞ ጥር 17 ረፋድ 5፡20 ላይ ለበረራ የተነሳው የበረራ ቁጥር ET9301 ለ53 ደቂቃዎች አየር ላይ ቆይቶ እኩለ ቀን 6፡13 ላይ ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ተመልሶ አርፏል።

ፍላይት ራዳር24 ላይ እንደተመለከተው ደግሞ አየር መንገዱ ሌላ በቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላኑ ዛሬ ማክሰኞ ከሰዓት በኋላ ሌላ የሙከራ በረራ አድርጓል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ እና በኢንዶኔዚያው አየር መንገድ ላይ አውሮፕላኖች ላይ በበረራ መቆጣጠሪያው እክል ገጥሞት ባስከተለው አደጋ ከበረራ ውጪ እንዲሆን የተደረገው ቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላን እጅግ ዘመናዊ ተብለው ከሚጠቀሱት መካከል አንዱ ነው።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ አራት ቦይንግ 737 ማክስ 8 ያሉት ሲሆን ከአደጋው ቀደም ብሎ ተጨማሪ 25 ተመሳሳይ አውሮፕላኖችን ለመግዛት አዝዞ በያዝነው የፈረንጆች ዓመት ይረከባል ተብሎ ይጠበቃል።

በአፍሪካ ግዙፉ አየር መንገድ የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ፤ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ስርጭትን ተከትሎ በርካታ አየር መንገዶች ለኪሳራ ሲዳረጉ አየር መንገዱ ግን ትርፋማነቱን ስለማስቀጠሉ ብዙ ተብሎለታል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአምስት አህጉራት በመቶዎች ወደሚቆጠሩ መዳረሻዎች ያሉት ሲሆን 130 አውሮፕላኖች አሉት። እነዚህም እጅግ ዘመናዊ የሚባሉትን 16 ኤይርባስ ኤ350-900 እና 19 ቦይንግ ቢ787-8 ይጨምራሉ።