መስፍን ጣሰው ለኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሆኑ፣ አዳዲስ የቦርድ አባላት ተሰየሙ

አቶ መስፍን ጣሰው

የፎቶው ባለመብት, Ethiopian Airlines

የምስሉ መግለጫ, የኢትዮጵያ አየር መንገድ አዲሱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው

በአፍሪካ ግዙፉ አየር መንገድ ለሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ መንገድ አዲስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ እና አዳዲስ የቦርድ አባላት ተሰየሙለት።

የረጅም ዓመታት ስኬታማ ዋና ሥራ አስፈጻሚው የነበሩት አቶ ተወልደ ገብረማሪያም በፈቃዳቸው ሥራቸውን መልቀቅ ተከትሎ ከ35 ዓመታት በላይ በተለያዩ ኃላፊነቶች አየር መንገዱን ሲያገለግሉ የቆዩት አቶ መስፍን ጣሰው ኃላፊነቱን እንዲረከቡ ተሹመዋል።

በተጨማሪም ስኬታማውን አየር መንገድ በሥራ አመራር የቦርድ አባላነት እንዲያገለግሉ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት ዋና ዳይሬክተር፣ የኢትዮጵያ አየር ኃይል ዋና አዛዥ እና ሌሎችም ተካተዋል።

ለአስራ አንድ ዓመታት ያህል የኢትዮጵያ አየር መንገድን በዋና ሥራ አስፈጻሚነት ሲመሩ የቆዩት አቶ ተወልደ ገብረማሪያም በጤና እክል ምክንያት ከኃላፊነታቸው ለመነሳት ጥያቄ አቅርበው ተቀባይነት ማግኘታቸው ተገልጿል።

አቶ ተወልደ ባለፉት ስድስት ወራት አሜሪካ ውስጥ ሕክምና ሲከታተሉ መቆየታቸው የተነገረ ሲሆን የጤናቸውን ሁኔታ በትኩረት ለመከታተል ከጊዜያቸው በፊት ጡረታ ለመውጣት ጠይቀው ነው የተፈቀደላቸው።

የዋና ሥራ አስፈጻሚውን መልቀቂያ የተቀበለው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ቦርድ፣ አቶ ተወልደን በመተካት ተቋሙን እንዲመሩ አቶ መስፍን ጣሰውን መሾሙን አስታውቋል።

አዲስ የተሾሙት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ የቦርድ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ግርማ ዋቄ በሰጡት መግለጫ አዲስ ስለተዋቀረው የአየር መንገዱ ቦርድና ስለተተኪው ዋና ሥራ አስፈጻሚ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

አዲስ የተሾሙት ዋና ሥራ አስፈጻሚው አቶ መስፍን ጣሰው ቀደም ሲል በኢትዮጵያ አየር መንገድ ውስጥ በተለያዩ የሥራ ክፍሎች ውስጥ አገልግለዋል።

ከእነዚህም ውስጥ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መምሪያ፣ በጥገናና ኢንጂነሪንግ እንዲሁም ኦፕሬሽን ዳይሬክተር በመሆን ሰርተዋል።

ካለፉት ሦስት ዓመታት ወዲህ ደግሞ በኢትዮጵያ አየር መንገድ የሥራ አመራር ቦርድአባል ሆነው ሲያገለግሉ ቆይተዋል።

ከዚያ በተጨማሪ ደግሞ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የከፍተኛ ድርሻ ባለቤት የሆነውና በምዕራብ አፍሪካ አገራት ውስጥ በስፋት የሚታወቀው የአስካይ አየር መንገድን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሆነው በመስራት ላይ ናቸው።

አስካይ አየር መንገድ በከባድ ኪሳራ የተዳከሙ የምዕራብ አፍሪካ አገራት አየር መንገዶችን በመተካት በተለያዩ ባለሀብቶች በክፍለ አህጉሩ ያለውን የአየር ትራንስፖርት ከፍተት ለመሙላት የተቋቋመ አየር መንገድ ነው።

በአፍሪካ ግዙፍ የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድም መቀመጫውን ቶጎ ሎሜ ባደረገው አስካይ ውስጥ 40 በመቶ ድርሻ በመያዝ ባለው ሰፊ የአየር ትራንስፖርት ልምድ ትርፋማ እንዲሆን እንዳስቻለው ይነገራል።

አቶ መስፍን ጣሰውም ይህንን አየር መንገድ በመምራት ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር ጥብቅ ቁርኝት እንዲኖረው ያደረጉ ሲሆን ለስኬታማነቱ ተጠቃሽ ናቸው።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ይፋ ካደረገ የዋና ሥራ አስፈጻሚ ሹመት በተጨማሪ፣ አዲስ የሥራ አመራር ቦርድ ማዋቀሩን አሳውቋል።

በዚህም መሠረት የቀድሞው የብሔራዊ ባንክ ገዢ አቶ ተክለወልድ አጥናፍ፣ የብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት ዋና ዳይሬክተር አቶ ተመስገን ጥሩነህ፣ የአየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጄነራል ይልማ መርዳሳ፣ አቶ ታደሰ ጥላሁን እና ሌሎችም በቦርዱ ውስጥ ተካተዋል።