በአዲስ አበባ ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ህጻናት ተማሪዎች ለእስር መዳረጋቸውን ኢሰመኮ ኮነነ

ተማሪዎች

የፎቶው ባለመብት, ehrc.org

በአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች ከኦሮሚያ ክልል ሰንደቅ ዓላማ እና መዝሙር ጋር በተያያዘ በተነሳው ውዝግብ ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ህጻናት ተማሪዎች ለእስር የመዳረጋቸውን እርምጃ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ኮነነ።

እነዚሀ ህጻናት ለተለያየ ጊዜ በእስር መቆየታቸው “ተገቢ ያልሆነ እና ለተፈጠረው ውዝግብ እና ግጭት ተመጣጣኝ ያልሆነ እርምጃ” መሆኑን ኢሰመኮ ረቡዕ ታኅሣሥ 19/2015 ዓ.ም. ባወጣው የምርመራ ሪፖርት አስታውቋል።

በአዲስ አበባ ከተማ በኦሮምኛ ቋንቋ ትምህርት በሚሰጥባቸው የመጀመሪያ እና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በተነሳው ውዝግብ ምክንያት ህጻናት ተማሪዎች ለአካላዊ እንግልት እና ከሕግ ውጭ ተገቢ ላልሆነም እስር መዳረጋቸውንም በዚህ ሪፖርት አካቷል።

በርካታ ህጻናት ተማሪዎችን የተሟላ አገልግሎት በሌላቸው እና ለአካለ መጠን የደረሱ ተጠርጣሪዎች በሚታሰሩባቸው ፖሊስ ጣቢያዎች ታስረው መቆያታቸውን የኢሰመኮ ሪፖርት አውግዟታል።

ህጻናቱን አስሮ የማቆየት “አስፈላጊነት፣ የሕጋዊነት እና የተመጣጣኝነት መርሆችን ያልተከተለ የሕጻናትን መብቶች የሚጥስ ተግባር ነው” ብሏል።

ኢሰመኮ የፀጥታ ኃይሎች ተመጣጣኝ በሆነ ሁኔታ ሁከቱን በመቆጣጠር፣ እጅግ ቢበዛ ሁኔታው እስኪረጋጋ ድረስ ተማሪዎቹን በየትምህርት ቤታቸው ግቢ ወይም ባሉበት ቦታ እንዲቆዩ ማድረግ ነበረባቸው ብሏል።

በተጨማሪም በቀጥታ በወንጀል ተግባር ላይ የነበሩ ተማሪዎች ካሉም እንደአስፈላጊነቱ አጠር ላለጊዜ ብቻ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ቆይተው ሳይውል ሳያድር እና እንደአግባብነቱ በፖሊስ ጣቢያ በሚሰጥ ዋስትና መለቀቅ ነበረባቸው ብሏል።

ተማሪዎቹ ጥፋት ፈፅመው ከሆነም ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናትን በሚመለከተው የዓለም አቀፍ ሰብአዊ መብቶች ድንጋጌዎች እና አግባብነት ባላቸው የኢትዮጵያ ሕጎች መሠረት ሊፈጸም ይገባ እንደነበር ጠቅሷል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

“ለሕፃናት ልጆች የሚገባው የሕግ ከለላ እንደተጠበቀ ሆኖ የማጣራት ሥራ ከማከናወን በስተቀር፤ ሕፃናት ተማሪዎችን በጅምላ ለእስር መዳረግ ፈጽሞ ተቀባይነት የሌለው እርምጃ በመሆኑ ለወደፊቱ ሊደገም የማይገባ ነው፡” በማለት አጽንኦት ሰጥቷል።

ሆኖም ፖሊስ ዕድሜያቸው ከ15 ዓመት በታች የሆኑ ህጻናትን በአፋጣኝ ወደ ህፃናት ችሎቶች እንዲቀርቡ ማድረጉንና ወዲያውኑ መለቀቃቸውንም ገልጿል።

ኮሚሽኑ ከኦሮሚያ ክልል ሰንደቅ ዓላማ እና መዝሙር ጋር ተያይዞ ሁከት የተከሰተባቸውን ሁሉንም ትምህርት ቤቶች ባይሸፍንም የተወሰኑ ትምህርት ቤቶች ባለድርሻ አካላትን አናግሯል።

ተማሪዎችን፣ መምህራን እና ኃላፊዎችን በተለያዩ ፖሊስ ጣቢያዎች በእስር ላይ የነበሩ ተማሪዎችን እና ሌሎች ተጠርጣሪዎችንም እንዲሁም ፖሊስን እና የሚመለከታቸውን አካላትን በማናገር ሪፖርቱ እንደተጠናቀረ ተገልጿል።

በአሁኑ ወቅት በተወሰነ ደረጃ ሁኔታዎች ጋብ ቢሉም ለወደፊቱ ይህንን መሰል ሁኔታዎችን እና የሰብዓዊ መብቶች ጥሰትን በዘላቂነት መከላከል ይገባል ብሏል።

በእነዚህ ትምህርት ቤቶች ውስጥ የኦሮሚያ ክልል ሰንደቅ ዓላማ እና የክልሉ መዝሙር በሚመለከት የተለያየ ሃሳብ እና ፍላጎት ያላቸው ተማሪዎችን ጨምሮ የትምህርት ቤቶቹ ማኅበረሰብ አባላት መካከል የተፈጠረ አለመግባባት ረብሻው ተነስቷል ብሏል፡፡ 

የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ከፌደራሉ መንግሥት ሰንደቅ ዓላማ ጎን የኦሮሚያ ክልል ሰንደቅ ዓላማ መሰቀል እና መዝሙሩም መዘመር አለበት ብሎ ያስተላለፈው ውሳኔ ሕጋዊ መሠረት የለውም በሚል ከተወሰኑ የማኅበረሰቡ አባላት ተቃውሞ እንደገጠመው አመልክቷል።

ይህንን ውሳኔ በደገፉ እና በተቃወሙ ተማሪዎች መካከል ረብሻ እና ግጭት መፈጠሩን ያተተው ሪፖርቱ፣ ፖሊስ ሁኔታውን ለመቆጣጠር በወሰደው እርምጃ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት መከተሉንም ተገልጿል። 

በዚህም ከተማሪዎች እስር በተጨማሪ ትምህርት ተስተጓጉሏል፣ የተማሪዎች እና የትምህርት ቤቶች ንብረት ወቀድሟል እንዲሁም ተማሪዎች ላይ ለከባድ እና ቀላል የአካል እና የሥነ ልቦና ጉዳት መድረሱን ገልጿል።

ሆኖም የአንድ ተማሪ ሕይወት ጠፍቷል ተብሎ የተነገረው ትክክለኛ መረጃ እንዳልሆነ ኢሰመኮ አመልክቷል።

ሪፖርቱ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በሕገ መንግሥቱ መሠረት ራሱን በራሱ የማስተዳደር ሙሉ ሥልጣን ያለውና ተጠሪነቱም ለፌደራሉ መንግሥት ነው ብሏል።

በሕገ መንግሥቱ መሠረት ክልሎች የየራሳቸው ሰንደቅ ዓላማ እና አርማ እንዳላቸው ቢደነገግም የአንድ ክልል ሰንደቅ ዓላማ በሌላ ክልል ወይም ከተማ አስተዳደር የመንግሥት ወይም የግል ተቋሞች ውስጥ እንዲሰቀል የሚያስችል የሕግ መሠረት የለም ብሏል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ መዝሙርን በተመለከተም ግልጽ ያለ ድንጋጌ በሕገ መንግሥቱ እንደተጠቀሰ ገልጾ “አላስፈላጊ ውዝግብ እና ሁከት መፍጠር ለሰብአዊ መብቶች መጣስ ሥጋት የሚፈጥር ድርጊት በመሆኑ ሊታረም የሚገባው ነው፡” ብሏል - የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን።