በታንዛንያ ከ5 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ታስረው እንደሚገኙ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ

ስደተኞች በሊቢያ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ስደተኞች በሊቢያ

በታንዛንያ ከአምስት ሺህ በላይ የሚሆኑ ህገወጥ ስደተኞች በእስር ላይ መሆናቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

ከ100 ሺህ በላይ ህገወጥ ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን በአንድ አመት ብቻ ወደሃገራቸው መመለስ ቢቻልም በሺዎች የሚቆጠሩ እስረኞች በታንዛንያ መኖራቸውንም ነው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ደመቀ መኮንን በሆሳዕና ከተማ በተካሄደ የምክክር መድረክ ላይ የተናገሩት።

ሚኒስትሩ በሰሜን ከተፈጠረው ጦርነት በተጨማሪ ህገወጥ የሰዎች ዝውውርና ስደት አገሪቷን እየፈተኗት ይገኛሉ ማለታቸውንም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ትናንት፣ ታህሳስ 15፣ 2015 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

ሚኒስትሩ በህገወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመካላከል በደቡብ ክልል ሆሳዕና ከተማ በተካሄደው የምክክር መድረክ ላይ ስደተኞቹ ከየትኞቹ አገራት እንደመጡ ስለመግለፃቸው መግለጫው ያለው ነገር የለም ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቅርቡ በማላዊ እና ዛምቢያ በኢትዮጵያውያን ስደተኞች ላይ የደረሰውንም የህይወት መቀጠፍ በመጥቀስ የችግሩን የከፋ ሁኔታ የሚያሳይ ነው ብለዋል።

በማላዊ ለአስከፊ ብዝበዛ መጋለጣቸው የታመነባቸው 30 የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች አስክሬን የጅምላ መቃብር መገኘቱ ይታወሳል።

በተጨማሪም ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ናቸው የተባሉ የ27 ሰዎች አስከሬን በደቡብ አፍሪካዊቷ አገር ዛምቢያ መዲና ሉሳካ አቅራቢያ መንገድ ዳር “ተጥለው” ተገኝተዋል። 

በቅርቡም ሳዑዲ አረቢያ ሕጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ የሌላቸው ናቸው የተባሉ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውን ስደተኞች በተጨናነቁ እስር ቤቶች በሰቆቃ ውስጥ እንደሚገኙ አምነስቲ ኢንተርናሽናል አስታውቋል። አምነስቲ

በሳዑዲ አረቢያ እስር ቤቶች ውስጥ ያሉበትን ሁኔታ እና እየገጠማቸው ያለውን አሳሳቢ ሁኔታን በተመለከተ ባወጣው መግለጫ ቁጥራቸው ከ30 ሺህ እንደሚልቅ አመልክቷል። 

“የስደትን አጠቃላይ ገጽታና አደጋን ሊወክሉ በማይችሉ ጥቂት ግለሰቦች የስኬት ታሪክ በመታለል ብዙ ኢትዮጵያውያን የሕገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች ሰለባ ሆነዋል” በማለትም አስረድተዋል።

 የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን

የፎቶው ባለመብት, Ministry Of Foreign Affairs

ከሳቸው በተጨማሪም በመድረኩ ላይ ተገኝተው የነበሩት የፍትህ ሚኒስትሩ ዶክተር ጌዴዮን ጢሞቴዎስ

'ኑ እስረኛ ውሰዱ፤ ኑ አስክሬን ውሰዱ' እየተባልን የዜግነት ክብራችን ዝቅ እንዲል ሆኗል። በመሆኑም ለዚህ ምክንያት የሆኑትን ህገ-ወጥ አዘዋዋሪዎች ማጋለጥ እና ለሕግ በማቅረብ አለብን “ ማለታቸውንም የፍትህ ሚኒስቴር በማህበራዊ ገጹ አስፍሯል።

አቶ ደመቀ ኢትዮጵያውያን ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን ከስር በመስረቱ በመቅረፍ የመፍትሄው አካል እንዲሆኑ ጥሪ አቅርበዋል።

በሆሳዕና ከተማ እየተካሄደ ያለው የውይይት መድረክ ''በህብረተሰቡ ጠንካራ ተሳትፎ ህገወጥ የሰዎች ዝውውርን በጋራ እንከላከል'' በሚል መሪ ቃል ነው።

ሆሳዕና ጉባዔውን እንድታካሂድ የተመረጠችበት ዋነኛው ምክንያትም በሃገሪቱ ህገወጥ የሰዎች ዝውውር ከፍተኛ ሰለባዎች ከሆኑባቸው አንዷ መሆኗን ጥናቶችን ዋቢ አድርገው ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

በተጨማሪም ህገወጥ የሰዎች ዝውውር ችግር ጎልቶ በሚታይባቸው የሀገሪቱ ሰሜን ምስራቅ አካባቢዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም አክለው ገልጸዋል።

ኢትዮጵያውያኑ በአደገኛ ባሕር እና በረሃ አቆራርጠው በሕገወጥ መንገድ በሚጓዙበት ጊዜ በሺዎች የሚቆጠሩት ባሕር ውስጥ የመስመጥ፣ በአዘዋዋሪዎች እና ድንበር ጠባቂዎች የመገደልና በረሃብና በውሃ ጥም መንገድ ላይ መሞታቸው ሲዘገብ ቆይቷል።