በማላዊ ለብዝበዛ የተጋለጡ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች እንዳሉ ተገለጸ

የፎቶው ባለመብት, UN
በማላዊ የስደተኞች መጠለያ ካምፕ ውስጥ በርካታ የሕገ ወጥ ሰዎች ዝውውር ሰለባ የሆኑ ኢትዮጵያውያን እንዳሉበት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስታወቀ።
ድዛሌካ በተሰኘው የስደተኞች መጠለያ ካምፕ ውስጥ በወንዶች፣ በሴቶች እና በህፃናት ላይ መጠነ ሰፊ ብዝበዛ እንደሚደርስ ይፋ የተደረገው በተባበሩት መንግሥታት የመድኃኒት እና የወንጀል ፅህፈት ቤት (ዩኤንኦዲሲ) እና የማላዊ ፖሊስ ባደረጉት የጥምረት ክትትል ነው።
ተቋሙ ከ90 በላይ ሰለባዎችን መታደጉን ገልጾ፣ አብዛኛዎቹ ከ18-30 የሚሆኑት ኢትዮጵያውያን ወንዶች ናቸው ተብሏል። ሌሎቹ ደግሞ ከ12- 24 ዕድሜ ያሉ ታዳጊዎችና ሴቶች ሲሆኑ የኢትዮጵያ፣ የብሩንዲ እና የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ዜጎች ናቸው።
አንዳንዶቹ የሕገ ወጥ ሰዎች ዝውውር ሰለባ የሆኑ ሰዎች ወደ ትውልድ ቀያቸው እንዲመለሱ ሌሎች ደግሞ በመጠለያዎች እንክብካቤ እየተደረገላቸው እንደሚገኝም ሪፖርቱ አስፍሯል።
በስፍራው ገበያ በሚመስል ሁኔታ ታዳጊ ልጆች የሚሸጡበትና እነዚህም ለግዳጅ ሥራ እና ለወሲብ ንግድ ብዝበዛ እንደሚዳረጉ የዩኤንኦዶሲ ተወካይ ማክስዌል ማትዌር ይናገራሉ።
የሕገ ወጥ ሰዎች ዝውውር ሰለባ ከሆኑት መካከል የአስር አመት ታዳጊ ትገኝበታለች ተብሏል። አንዳንዶቸ ድብደባ እንደደረሰባቸው፣ መደፈር እንዲሁም ህፃናት ለአስገዳጅ የግብርና ሥራ መዳረጋቸውን ሪፖርቱ ጠቅሷል።
ከእነዚህም ውስጥ የተወሰኑ ታዳጊዎችና ሴቶች በሕገ ወጥ ዝውውር በደቡብ አፍሪካና በሌሎች አገራት ለወሲብ ንግድ የሚሸጡ ሲሆን በርካቶችም ብዝበዛ እንደረሰባቸው ሪፖርቱ አጋልጧል።
ወንድ ስደተኞችም በመጠለያ ካምፑ ውስጥ ባሉ እርሻዎች እንዲሁም በማላዊና በሌሎች አገራት በግዳጅ ሥራ እየሰሩ እንደሆነ በመጥቀስ ሁኔታው አሳሳቢ ነው ብሏል።
የመጠለያ ካምፑ በሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ማዕከልነት እያገለገለ መሆኑንና ሕገ ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች ሰለባዎችን በሃሰተኛ ሽፋን በመመልመል ድንበር አቋርጠው ወደ ማላዊ ያመጧቸዋል ብሏል።
ሰለባዎቹም ደቡብ አፍሪካ ለሥራ ትወሰዳላችሁ በሚል ማታለያ ከኢትዮጵያ፣ ብሩንዲና ኮንጎ የተወሰዱ ሲሆን በካምፑ ውስጥ እስከ ማላዊ ድረስ የተወሰዱበትን ብር እንዲከፍሉ እንደሚገዱም ሪፖርቱ አትቷል።
በመጠለያ ካምፑ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ የሕገ ወጥ ሰዎች ዝውውር ሰንሰለቶችን ለመቆጣጠር፣ ሰለባዎችን ለመለየት እና እንዲሁም ሕገ ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎችን ለፍርድ ለማቅረብ እርምጃዎችን በመወሰድ ላይ መሆኑም ተገልጿል።
በስደተኛ መጠለያ ውስጥ የሚገኙ ሰራተኞች እንዲሁም የሕግ አስከባሪ የጸጥታ ኃይሎች ሕገ ወጥ አዘዋዋሪዎችን አድኖ መያዝ በሚቻልበት ሁኔታ እና ምላሽ መስጠት በሚቻልበት ሁኔታ ስልጠና እየወሰዱ ነው ተብሏል።
በዚህም መሰረት እስካሁን ባለው ከሦስቱም አገራት አምስት ሕገ ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል። በርካታ ሰለባዎች ምስክርነት ለመስጠት ፍራቻ በመስፈኑ በፍርድ ቤት ከሶ ፍትህን በማግኘት ረገድ ችግር መደቀኑም ተነግሯል።
በአውሮፓውያኑ 1994 የተቋቋመው የድዜሌካ የስደተኞች ካምፕ በማላዊ ትልቁ ሲሆን 50 ሺህ ስደተኛና ጥገኛ ጠያቂዎችን ይዟል። ካምፑ የተቋቋመው አስር ሺህ ሰዎችን ለመያዝ ነበር።












