"ሰላም እንፈልጋለን ማለታችን የድብቅ ድርድር እናደርጋለን ማለት አይደለም" ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ

የፎቶው ባለመብት, HOPR

የምስሉ መግለጫ, ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የሰላም ሂደቱን በተመለከተ የሚያጠና ኮሚቴ መዋቀሩን ተናገሩ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዛሬው ዕለት ሰኔ 07/2014 ዓ. ም. በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከአባላት ለተነሳላቸው ጥያቄ ምላሽ በሰጡበትም ወቅት ነው ይህንን ያስታወቁት።

በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የሚመራ ኮሚቴ በብልጽግና ሥራ አስፈፃሚ መሰየሙንና ሰላሙን በተመለከተ መሳካት ያለባቸው ተግባራትን፣ እንዲሁም ስለሚጠበቁ ነገሮች እያጠና ነው ብለዋል።

እስካሁን ባለውም ኮሚቴው ለብልጽግና ሥራ አስፈፃሚ ሪፖርት ያላቀረበ ሲሆን፣ ሲያቀርብም በይፋ ለሕዝብ በዝርዝር የሚቀርብ ይሆናል ብለዋል።

ከህወሓት ጋር በሚደረገው ድርድርም ይኽው ኮሚቴ ተደራዳሪ መሆኑንም በዚህ ወቅት ግልፅ አድርገዋል።

በዚህ 6ኛው ምክር ቤት በ1ኛ ዓመት የሥራ ዘመኑ ባካሄደው 13ኛው መደበኛ ስብሰባ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተደጋጋሚ አፅንኦት ሰጥተው የተናገሩት መንግሥታቸው ሰላም እንደሚፈልግ ነው።

“ከህወሓትም ይሁን ከማንኛውም ሰላም ፈላጊ ጋር የምንፈልገው ሰላም ነው፤ የሚቻል ከሆነ ለሰላም መቆም ችግር የለውም” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ጦርነት እንደማያተርፍና ከሁለቱም ጎን የሚያለማ ወጣት እየረገፈና አገሪቱም የምታወጣው ገንዘብ ከፍተኛ ነው ብለዋል።

ሆኖም በተለያዩ ሚዲያዎች ህወሓትና የፌደራሉ መንግሥት በቅርቡ በናይጄሪያ ተገናኝተዋል የሚባለውን ጨምሮ በተለያዩ አገራት ተወያይተዋል የሚባለው “ተረት ተረት ነው” ብለዋል።

በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከናይጄሪያ መንግሥት ባለሥልጣናት ጋር በነበራቸው ውይይት ስለ ህወሓትም ሆነ ስለ ጦርነቱ የተነሳ ነገር እንደሌለም አስረድተዋል።

በተለይም ከሰላሙ ሂደትና ድርድር ጋር ተያይዞ ለፓርላማው ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ ሕዝቡም እየተደረጉ ያሉ ውይይቶችና የሰላም ሂደቶችን በተመለከተ የማወቅ መብት እንዳለውም አስገንዝበዋል።

“ሰላም እንፈልጋለን ማለታችን የድብቅ ድርድር እናደርጋለን ማለት አይደለም" ሲሉም የመንግሥታቸውን አቋም ገልጸዋል።

ሰላም ለማምጣት በሚደረገው ሂደት የሚደበቅ ነገር እንዳልሆነና ንግግሮች ሲጀመር ለሕዝቡ በወቅቱ የሚገለጽ ይሆናል በማለት በርካታ አሉባልታዎች እንደሚነዙ አንስተዋል።

በተለይም ከድርድሩ ጋር ተያይዞ አማራ ሳያውቅ እየተካሄደ ነው ወይ? በሚል ከአንደኛው ምክር ቤቱ አባል ለቀረበላቸው ጥያቄም ሲመልሱ "ውጊያው ከአማራ ጋር ብቻ እንዳልሆነና ከኢትዮጵያም ጋር ነው" ብለዋል።

የተከሰተው ጦስ የኢትዮጵያ ችግርና ፍዳ እንደሆነ በመግለጽ ወደታች ሁኔታውን ማውረድና ነገሮችን መሰንጠቅ ተገቢ አይደለም ብለዋል።

“ለብቻ የተሰራ እንዲሁም የብቻ ጠላት የለም” በማለት አስምረዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

መንግሥታቸው ከሰላም ጋር በተያያዘ ለመነጋገር የሚፈልጉበት ምክንያት በርካታ እንደሆነ ጠቅሰዋል። በተለይም የበርካታ አገራት መሪዎች ኢትዮጵያን የምታክል አገር የውስጥ ችግሯን ለምን አትፈታም? በሚል እንደሚያናግሯቸውና በተጨማሪም የአገር ጥቅምም ስለሚጎዳ ሰላሙ እንደሚጠቅምም ጠቅሰዋል።

“ለጥይት የሚወጣው ዶላር ለመድኃኒትና ለግንባታ መዋል አለበት። ሕዝቡ ልማት ነው የሚፈልገው” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በአገሪቱ ውስጥ ከፍተኛ ግሽበት እንዳለና ለጥይት የሚወጣ ዶላር መኖር የለበትም ብለዋል በዛሬው የፓርላማ ማብራሪያቸው።

በተለይም በዚህ ሰላም ተጠቃሚው የትግራይ ሕዝብ እንደሆነም ጠቅሰዋል።

“ሰላም ከመጣ የምትጠቀመው ትግራይ ናት” ያሉ ሲሆን የትግራይ ሕዝብ በከፍተኛ ሁኔታ እንደተጎዳና ለሕዝብም መቆርቆር እንደሚያስፈልግም አፅንኦት ሰጥተዋል።

ለሰላም ቅድሚያ መንግሥታቸው እንደሚሰጥና የተቻለውን ሁሉ ያደርጋል ብለዋል።

ከጅምሩ አንስቶ በአገር ውስጥም ይሁን በአካባቢው ጦርነት እንዳይኖር መንግሥታቸው የሰራ መሆኑን አስታውሰው በዚህም ወደ ኤርትራ በመሄድ ለአመታት የዘለቀው ግጭት እልባት እንዲያገኝ ማስቻላቸውን አስረድተዋል።

ከዚህም በተጨማሪ በሶማሊያና በኬንያ እንዲሁም በደቡብ ሱዳን ድርድሮች ኢትዮጵያ የተሳተፈችው በቀጠናው ሰላም ለማስፈን ነው ብለዋል ።

“ከማንም ጋር ትናንትም፣ ዛሬም ነገም ውጊያ አንፈልግም” ብለዋል።

በባለፉት አመታት አገሪቱ ውስጥ በተፈጠሩ ግጭቶችና ሁከቶች ህወሃትን ተጠያቂ ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህም ግጭቶችን ስፖንሰር ከማድrግ በተጨማሪም የአገሪቱን መከላከያ ሸርሽሯል ብለዋል።

"ህወሓት የደረሰበትን ሽንፈት ሊቋቋመው ባለመቻሉ ጦርነት እንደከፈተም" አውስተዋል። መንግሥታቸው ጦርነት እንዳልጀመረና ለመከላከል የገባበት ነው ብለዋል።

መንግሥታቸው ለሰላም የቆመ ነው የሚሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለምሳሌም ያህል እነ ኦነግ፣ ግንቦት ሰባትን ወደ አገር ውስጥ የመጋበዝ እንዲሁም በብሄራዊ ምርጫ ብልጽግና ካሸነፈ በኋላም ለተቃዋሚዎች ሥልጣንን በማጋራት አሳይቷል ብለዋል።

ጦርነቱ በግዳጅ የገበቡበት እንደሆነ የሚገልጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በውጊያ የተገኘው ድል በሰላም ማስቀጠልም ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ አትፈርስም በሚል የአስተዳደራቸው አቋም ኢትዮጵያ በልማት ጎዳና ላይ መገኘት መቻሏን እንዲሁም ተቋማት እየገነባች ነው ብለዋል።

ከዚህም ጋር ተያይዞ የፀጥታ ተቋማቱን ዝግጅት በተመለከተ ህወሓትን ከግምት ብቻ ያስገባ ሳይሆን በቴክኖሎጂ፣ በአቅምና ከፍተኛ ደረጃ ላይ ያለና ይህችንም ጥንታዊት አገር ወደፊት የሚያስቀጥል ነው ብለዋል።

ከውጊያ በላይ በሳይበር በከፍተኛ ጉዳት እንደሚደርስና በባለፈው አመትም በአገሪቱ ስድስት ሺህ የሚገመት የሳይበር ጥቃት እንደደረሰና በሚሊዮኖችም ብር መታጣቱን ጠቅሰው በየትኛውም በኩል የሚደርሱ ጥቃቶችን ለመከላከል አገሪቷን የሚያስቀጥል ተቋም ይገነባል ብለዋል።

የሕግ ማስከበር ዘመቻ

ሌላኛው ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት የተነሳው ጥያቄ በቅርቡ መንግሥት በተለያዩ ክልሎች እያካሄድኩ ነው ካለው የሕግ ማስከበር ዘመቻ ጋር በተያያዘ ነው።

ለሕግ ማስከበር ዘመቻው መነሻው ብልጽግና ከሕዝቡ ጋር ባደረገው ውይይት እንደሆነ ጠቅሰው ሕዝቡ በዋነኝነት ያነሳው ችግር ሰላም፣ የዋጋ ግሽበት እንዲሁም መልካም አስተዳደሮች ናቸው ብለዋል።

ይህንንም ተከትሎ የብልፅግና ማዕከላዊ ኮሚቴ በአገር ደረጃ ጥናት ያደረገ ሲሆን በአማራ፣ በኦሮሚያና በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ሰፋ ያለ ከሰላም ጋር ተያይዞ ችግር እንዳለና በአዲስ አበባ ከዝርፊያ ጋር በሶማሊያ ከአልሻባብና ከኮንትሮባንድ ጋር ተያይዞ እርምጃ ሊወሰድ እንደሚገባም መወሰኑም ተጠቅሷል።

በባለፉት ሁለት ወራት በተደረገውም የሕግ ማስከበር ዘመቻ በሰፊው የተተገበረው በኦሮሚያ ክልል መሆኑን ጠቅሰው፣ በዚህም 1 ሺህ የሸኔ አባላት መገደላቸውን፣ በብዙ ሺህ መማረካቸውን እንዲሁም በርካታ ውጤታማ ሥራ መሰራቱን ጠቅሰዋል።

በተጨማሪም በአማራ፣ በአዲስ አበባ፣ በሶማሌና በቤንሻንጉል ጉሙዝ የተሳኩ ሥራዎች እንደተሰሩና ከሕግ ማስከበር ዘመቻ በኋላም በነበረው ውይይት ሕዝቡ መደሰቱን ጠቅሰዋል።

 በአማራ ክልል በተለይም በርካታ ሕዝብ ደስተኛ እንደሆነና ከዚህ ቀደም በነበረው ሁኔታ እናቶች መተኛት በማይችሉበት ሁኔታ “ጥይቶች ሲንጣጡ ነበር የሚያድረው” በማለት ሕዝቡ በከፍተኛ ጭንቀት ላይ እንደነበረም ገልጸዋል።

ከሕግ ማስከበር ዘመቻው በፊት በአማራ ክልል ሁኔታዎችን በሰላም ለመቋጨት ጥረቶች ቢደረግም ሊፈታ አለመቻሉን አስታውሰዋል።

ብቸኛ ኃይል መጠቀም ሥልጣን ያለው መንግሥት መሆኑን በማስታወስ፣ ሆኖም ባለው የፌደራል ሥርዓት መዋቅር በአማራ ክልል የተካሄደው ዘመቻ መቶ በመቶ በአማራ ልዩ ኃይል የተከናወነ መሆኑንም ጠቅሰዋል ።

በአማራ ክልል ብቻ ሳይሆን በሌሎችም ክልሎችም በዋነኝነት የሕግ ማስከበር ዘመቻው የተፈፀመው በክልሎቹ የጸጥታ መዋቅሮች የታዘዘ እንደሆነና በፌደራል እየተመራ እንደሆነ የሚነገረውም ስህተት መሆኑን ጠቁመዋል።

በሕዝብ ጥያቄ የተጀመረ ነው ባሉት የህግ ማስከበር ዘመቻ የፌደራሉ መንግሥት የቴክኒካል ድጋፍ የመስጠት ሚና እንዳለው አስረድተዋል።

በአማራ ክልል ከተደረገው ዘመቻ ጋር ተያይዞ የፋኖ ታጣቂዎች ኢላማ ሆነዋል በሚል ከተጠየቀው ጥያቄ ጋር በተያያዘ በሰጡት ምላሽም።

"ፋኖ ለአማራም ለኢትዮጵያ ኩራት እንደሆነና በጀግንነት እንደተዋጋ ጠቅሰው" ይሄ መወደስ ያለበት ተግባር ቢሆንም ስሙን መጠቀሚያ ያደረጉ ታጣቂ አካላት እንዳሉም ተናግረዋል።

 በአማራ ክልል ሴቶችን መድፈር፣ ህፃን መጥለፍ፣ መዝረፍ፣ ሐሰተኛ ብር ማምረት፣ ተበራክቶ የነበረ ሲሆን የፋኖ ታጣቂዎች ይህንን እንደማያደርጉም ይህ መሳሪያ የታጠቀ ኃይልና ለአማራ ሕዝብም ሆነ ለኢትዮጵያ ሕዝብ እንደማይጠቅምና በክልሉ የተደራጀ አንድ መዋቅር አስፈላጊነትን አስረድተዋል።

በዚህም በቁጥጥር ስር የዋሉትን አካላት ገልጸው በአማራ ክልል ውስጥ ከታሰሩ ሰዎች ውስጥ 3 ሺህ 500 የከዳ የመከላከያ ሠራዊት ሲሆን ከ2 ሺህ በላይ ደግሞ የአማራ ኃይል አባላት ናቸው።

በተጨማሪም በርካታ ኩንታል አደንዛዥ ዕፅ፣ ቦምብ፣ ስናይፐር፣ ሐሰተኛ ገንዘብ በተለያዩ ክልሎች በቁጥጥር ስር በማዋልም ስኬት መቆጠሩን አውስተዋል።

በዚህም ሕግ ማስከበር ባሉት ዘመቻ ባለፉት ሁለት ወር ውስጥ ከአምስት ሺህ የብልጽግና አባላት በላይ እንደተባረሩ፣ እንደታሰሩና በደረጃም ዝቅ መደረጋቸውን ጠቅሰው የማጥራት ስራውም ከውስጥ እየተሰራ እንደሆነ አስረድተዋል።

ሆኖም በዘመቻው በስህተት የተያዘ፣ የተጎዳ ሰውና ጥፋት ካለ ሊታረም እንደሚገባና በዋነኝነት ተግባሩ የክልሎቹ ቢሆንም ምክር ቤቱ ይከታተላል ብለዋል። የአማራ ክልልም በስህተት ያሰራቸውን ከሺህ በላይ ሰዎች መፈታታቸውን አስረድተዋል።

በአማራ ክልል መውጣት መግባት አስፈሪ እንደነበር በርካቶች ተኝተው የማያድሩበት ሁኔታ ተፈጥሮ ነበር በማለት ለወደፊቱ የሕግ ማስከበር ዘመቻው ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አፅንኦት ሰጥተዋል።

ምክር ቤት አባላት

የፎቶው ባለመብት, HOPR

የጋዜጠኞች እስር

ከሰሞኑ የሕግ ማስከበር ዘመቻ ጋር ተያይዞ የተለያዩ የጋዜጠኛ መብት ተሟጋቾች ከ16 በላይ ጋዜጠኞች መታሰራቸውን መግለፃቸው ይታወሳል። ከዚህም ጋር ተያይዞ በዛሬው የፓርላማ ውሎ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ከለውጡ በኋላ ሚዲያዎች ላይ አፈና እየደረሰ ነው የሚል ጥያቄ ቀርቦላቸዋል።

እሳቸውም በምላሹ በአገሪቱ ውስጥ በተሟጋቾች፣ ጋዜጠኛና በሌሎች ስሞች መከላከያን ጨምሮ ተቋማትን ለማፍረስ እንቅስቃሴዎች እንዳሉ ጠቅሰዋል። ሃሳብን በነፃነት የማስተላለፍን የማፈን እርምጃ አለ የሚለውን እንደማይስማሙበት አስረድተዋል።

በሃይማኖቶች መካከል መበጣበጥን ለመፍጠር የሚሰሩ እንዳሉና እነዚህም ተጠያቂ እንደሚሆኑና በአገር ሉዓላዊነት መደራደር እንደማይቻልና ጋዜጠኝነት የወንጀል መደበቂያ መሆን እንደሌለበትም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

“መከላከያን በማይገባ ድንበር ከነካህ ትቀፈደዳለህ። መከላከያ ከሌለ አገር የለም” ሲሉም አስጠንቅቀዋል።

በኢትዮጵያ ውስጥ ብሔሄርን፣ ሃይማኖትን የሚያንቋሽሹና ለሁከት የሚያነሳሱ ሥራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን በመጥቀስ የዚህ ዘመቻም ዋነኛም አላማ ሕግና ሰላም ማስከበር እንደሆነም ጠቁመዋል።

በአጠቃላይ እየተሰራም ያለው ሥራ የአገሪቱን ደኅንነት ማስከበርና አገሪቱን ለማፍረስ በርካታ ኃይሎች መኖራቸውንም አፅንኦት ሰጥተዋል። ሆኖም በሥርዓቱ ውስጥ ያልተገባ ሥራ እየሰሩ ያሉ የፀጥታ ኃይል አባላትም ካሉ ተጠያቂ እንደሚሆኑም ጠቅሰዋል።

"ተረኝነት"

ሌላኛው በፓርላማ አባል የቀረበላቸው ጥያቄ ተረኝነትን አስመልክቶ ነው። ኢትዮጵያ የሁሉም ቤት እንደሆነችና ሰፊ አገር፣ የሰው ሃብት፣ በርካታ ወጣቶች ያሉባት፣ የታሪክና ባህል ሃብት እንዲሁም የተፈጥሮ ሃብት አላት ብለዋል።

አገርን እንደ ዕቁብ የሚያዩና በርካታ ብሔር ብሔረሰቦችን የማያካትት አገር መገንባት እንደማይቻል አስረድተዋል። “ፈረቃ ለአገር አይሆንም። በትብብር መምራት ነው የሚቻለው። ትርፉ ኪሳራ ነው” ብለዋል።

በተለይም ባለፉት ወራት መንግሥታቸው በተረኝነት እየተፈረጀ መሆኑን ገልጸው ባደረጉት ግምገማ ሕግ አውጪ፣ ሕግ አስፈፃሚ፣ ሕግ አስተርጓሚና ርዕሰ ብሔሯን ጨምሮ ያሉትን የመንግሥት አካላትን በማየት ተረኝነት የለም ብለዋል።

በእነዚህ የመንግሥት አካላት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አንድ ኦሮሞ ብቻ ነው የሚሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በሚኒስትሮችም ደረጃ 6 ኦሮሞ፣ ስድስት አማራና ስድስት ደቡብ ሚኒስትሮች መሆናቸውን በመጥቀስ ተረኝነት እንደሌለው ጠቅሰዋል።

በተለያዩ መሥሪያ ቤቶችም የኦሮምኛ ቋንቋ ካልተወራ አገልግሎት አይሰጥም የሚል ቅሬታ እንደደረሳቸውና መሥሪያ ቤቶችን በፈተሹበት ወቅት የኦሮሞ ተወላጆች ቁጥር ሊበልጥ ቀርቶ የሚገባው አይደለም በማለት መረጃዎችን ዋቢ ማድረጋቸውን ጠቅሰው አስረድተዋል።

በልማት ድርጅቶችም ይህ እንደማይስተዋል በመጥቀስ የኢትዮጵያ አየር መንገድን የሠራተኞች የብሔር ተዋፅኦን በማሳየት የኦሮሞ ብሔር ተወላጆች እንደሚባለው አይደለም ብለዋል።

 የኦሮሞ ህዝብ 35 በመቶ መሆኑና ከትግራይ ሕዝብ ጋር ማነጻጸር እንደማይገባና በአገሪቱ የሚገባውንም ድርሻ ሊያገኝ እንደሚገባም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

በተለይም ከሰሞኑ በአዲስ አባባ የኦሮሚያ መዝሙር ተዘመረ ተብሎ ተረኝነት ለማሳየት የተነሳው ኦሮሞ ጠልነት እንደሆነም ጠቅሰዋል።

በአዲስ አበባ ኦሮሞ ጠል ኃይሎች እንዳሉና የተለያዩ ዓለም አቀፍ ትምህርት ቤቶች መዝሙር ባይጎረብጣቸውም የኢትዮጵያ አንዱ ሕዝብ የሆነው ኦሮሞ መዝሙር መረበሹ ጥላቻ አሳዛኝ እንደሆነም ነው የተናገሩት።

'ለውጡ ተቀልብሷል?'

ሌላኛው በተወካዮች ምከር ቤት አባላት ጥያቄ የቀረበው የባለፉት አራት ዓመታት ለውጥ እንዲሁም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቃል የገቧቸው ጉዳዮች ተፈፅመዋል የሚሉ ናቸው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ ባለፉት አራት ዓመታት ኢትዮጵያ በገጠማት ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ ተግዳሮቶች ዓይን የለውጡ ዓንድምታ ሊታይ ይገባል ብለዋል።

ተፈጥሯዊ ብለው የጠቀሷቸው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ፣ አንበጣና ድርቅ አገሪቷን ያጋጠማት ችግሮች ሲሆኑ፤ እቅዶችን ለመከለስና አሰራሮችን ለመፈተሽ በመገደዳቸው የአገሪቷ ሁኔታ በዚያ አንድምታ ሊታይ እንደሚገባው አስምረዋል።

በተጨማሪም አገሪቷን ለሰብዓዊና ለምጣኔ ሀብት ቀውስ የዳረጋት ጦርነት እንዳጋጠማትና ይህንንም “አገርን ከመፍረስ በታደገ ዘመቻ” ቀልብሰነዋል ብለዋል።

ኢትዮጵያ ያጋጠማት ጦርነት ቀላል የሚባል ሳይሆን "እንድትፈርስ የተጠነሰሰ ነው" ካሉ በኋላ፣ ሆኖም ይህ አለመሳካቱን ተናግረዋል።

“ኢትዮጵያ አልፈረሰችም ሳይሆን የብልጽግና መሰረቷን እየጣለች ነው” ብለዋል።

አገሪቷን ያጋጠሟት ችግሮች ተቋማት ባልዳበበሩት እንዲሁም ፓርቲያቸው ባልደረጀበት ሁኔታ ነው ብለዋል።

ከዚህ ሁሉ በተጨማሪ አገሪቷ ያልተገባ ጫና እንዲሁም በዩክሬንና ሩሲያ ያጋጠመው ጦርነት አገሪቷ ላይ ከፍተኛ ጫና መድረሱንም ጠቁመዋል።

ሆኖም በሰው ሰራሽም ሆነ በተፈጥሯዊ ችግሮች አገሪቷ ፈተና ውስጥ ብትሆንም እያንዳንዱ መከራ ዕድል ይዞ እንደሚመጣና በእርስ በርስ ጦርነትና በሌሎች መከራዎች እያለፉ ያሉ አገራትም መማር እንደሚገባም አስታውሰዋል።

መንግሥታቸውም ከእነዚህ ተግዳሮቶች ትምህርት እንደወሰደና ኢትዮጵያን አስተማማኝ ቦታ ሊያስቀምጥ የሚችልበት መንገድ ላይ ናት ብለዋል።

“ሪፎርሙ ለማመን የሚከብዱ ውጤቶች እያመጣ ነው። ለእናንተ ሳይሆን ለእኔ ለራሴ፤ የፈጣሪን ቸርነት በተግባር ያየንበት አስደማሚነት የታየበት” ነው ብለዋል።

መንገድ

ከለውጡ በፊት የመንገድ አውታር 127 ሺህ ኪሎሜትር የነበረና ይሄ በአጠቃላይ በአገሪቱ የክልልና የፌደራል ኔትወርክ የሚሸፍን ሲሆን ከለውጡ በኋላ 165 ሺህ መድረሱን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ መንገድ አስተዳደር የተሰሩ ኮንክሪት አስፓልቶች ቀድሞ ተቋሙ የኢትዮጵያ መንገድ ባለሥልጣን በነበረበት ወቅት 13 ሺህ ኪሎሜትር ነበር ብለዋል። ሆኖም በባለፉት አራት ዓመታት ገደማ ብቻ 4 ሺህ 700ኪሎሜትር መንገድ አጠናቆ እንዳስረከበም ገልጸዋል።

በተጨማሪም 8 ሺህ 113 ኪሎሜትር እየተገነባ እንደሆነና በቅርቡ የሚጠናቀቅ እንዲሁም ተጨማሪ 9 ሺህ 100 ኪሎ ሜትር በጀት ጸድቆለት በተለያየ ምክንያት ባይጀመርም እቅድ ላይ መሆኑን አውስተዋል። በአጠቃላይ በአገር አቀፍ ደረጃ 22 ሺህ ኪሎሜትር መንገድ መሰራቱንና ይህም ለውጡ ያመጣው ስኬት ነው ብለዋል።

በተለይም በአንዳንድ ክልሎች ከዚህ ቀደም ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ከፍተኛ ሥራዎች መሰራታቸውን ገልጸው ይህ ግን በቂ እንዳልሆነና የበለጠ መሰራት እንዳለበት አመልክተዋል።

አየር መንገድ

ሌላው መሻሻል ያሳየው የኢትዮጵያ አየር መንገድ መሆኑን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከለውጡ በፊት 100 አውሮፕላኖች የነበሩት አየር መንገዱ 135 አውሮፕላኖች ያሉት ሲሆን በዚህም 35 በመቶ እድገት ማሳየቱን ተናግረዋል።

በተጨማሪም የአየር መንገዱ መዳረሻ የነበሩት አገራት ከ115 ወደ 127 ደርሷል መድረሳቸውን ጠቅሰዋል።

በገቢም ደረጃ ከለውጡ በፊት 3.3 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ያገኝ የነበረው አየር መንገዱ፣ በአሁኑ ወቅት ግን 4. 8 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ሲያገኝ፣ ስድስት ሚሊዮን መንገደኞች ያስተናግድ የነበረው ወደ 22 ሚሊዮን መንገደኞችን ለመድረስ ችሏል በማለት በተለያዩ ተግዳሮቶች ውስጥ የተገኘ ስኬት ነው ብለዋል።

ቴሌኮሙዩኒኬሽን

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በዛሬው ፓርላማ ንግግራቸው የጠቀሱት ኢትዮ ቴሌኮምን ሲሆን ከለውጡ በፊት 38 ሚሊዮን ደንበኞች እንደነበርና በአሁኑ ወቅት ጭማሪ አሳይቶ ወደ 65.5 ሚሊዮን አድጓል ብለዋል። በተጨማሪም በገቢ ደረጃም ከለውጡ በፊት የነበረው 33.5 ቢሊዮን ብር በ21.5 ቢሊዮን ብር የገቢ ጭማሪ በማሳየት ወደ 55 ቢሊዮን ብር ማደጉን አስረድተዋል።

በአጠቃላይ ተቋሙ በጦርነቱ ምክንያት የማይሸፍናቸው አካባቢዎች ቢኖሩም በገቢም ሆነ ተደራሽነቱ በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን በማውሳት አስተዳደራቸው ስኬት ላይ መሆኑን አፅንኦት ሰጥተዋል።