ደምቢዶሎ ውስጥ በፀጥታ ኃይሎችና በታጣቂዎች መካከል ግጭት እንደነበር ነዋሪዎች ተናገሩ

በምዕራብ ኦሮሚያ ደምቢዶሎ ውስጥ በመንግሥት ኃይሎች እና በሸኔ ታጣቂዎች መካከል የተኩስ ልውውጥ እየተካሄደ መሆኑን ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናገሩ።
መንግሥት በሽብርተኝነት የሰየመውና ኦነግ-ሸኔ የሚለው፣ ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ሲል የሚጠራው ኃይል የሕዝብ ግንኙነት ኦዳ ተርቢ በትዊተር ገጻቸው ላይ በደምቢዶሎ እና በጊምቢ ወታደራዊ ዘመቻ እያደረገ መሆኑን አስፍረዋል።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው የደምቢዶሎ ነዋሪዎች በከተማዋ ከማለዳው 12 ሰዓት ጀምሮ የተኩስ ልውውጥ እየተካሄደ መሆኑን ገልጸዋል።
ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ የከተማዋ ነዋሪ “አሁን የመሳሪያ ተኩስ እየተሰማ ነው። ከጠዋት 12፡30 ጀምሮ እስከ አሁን (5፡00) ከባድ የተኩስ ልውውጥ እየተካሄደ ነው። ሰው ወደ ውጪ መውጣት አይችልም። ቤታችንን ዘግተን ነው ያለነው” ብለዋል።
እኚህ ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ የከተማው ነዋሪ ተኩሱ በብዙ የከተማዋ ቀበሌዎች ውስጥ እየተካሄደ መሆኑን ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ሌላ የደምቢዶሎ ከተማ ነዋሪ በበኩላቸው በኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት እና በመንግሥት ኃይሎች መካከል ግጭት እየተካሄደ መሆኑን ተናግረዋል።
ታጣቂዎቹ በደንቢዶሎ ውስጥ እንደታዩ የገለጹት ነዋሪው “በመላ ከተማዋ እየተተኮሰ፣ በበራችን ደጃፍ ሲያልፉ አይተናቸዋል።" ብለዋል።
የፌደራል መንግሥት እና የክልሉ ኃይሎች፤ ማለትም መከላከያ፣ ፌደራል ፖሊስ፣ የኦሮሚያ ልዩ ኃይል እና መደበኛ ፖሊስ ከታጣቂዎቹ ጋር ተኩስ ሲለዋወጡ እንደነበር እኚህ ነዋሪ ለቢቢሲ እማኝነታቸውን ሰጥተዋል።
“በከተማዋ ምንም እንቅስቃሴ የለም። ሁሉም ሰው ቤቱን ዘግቶ ነው ያለው። በመንገድ ላይም ምንም ነገር የለም። ወታደሮች ብቻ ናቸው እየተሯሯጡ ያሉት” በማለት ደምቢዶሎ ከተማ ስላለችበት ሁኔታ ይገልጻሉ።
በሌላ በኩል የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ቃል አቀባይ ኦዳ ተርቢ ታጣቂዎቻቸው በደምቢዶሎ እና ጊምቢ ከተሞች ከመንግሥት ኃይሎች ጋር እየተዋጉ መሆናቸውን በትዊተር ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።
በዚህ ጉዳዩ ላይ ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ቢቢሲ የቄለም ወለጋ ዞን አስተዳዳሪ የሆኑትን አቶ ገመቹ ጉርሜሳን ለማግኘት ሞክሮ፣ ሥራ ላይ መሆናቸውን እና በኋላ እንዲደወልላቸው በመንገር ተጨማሪ ማብራሪያ ከመስጠት ተቆጥበዋል።
ቢቢሲ የዞኑን አስተደዳር እና ፀጥታ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ለማግኘት ያደረገው ጥረት ለጊዜው አልተሳካም።
ኦዳ ተርቢ በትዊተር ገጻቸው ላይ የኦነግ ሠራዊት እና የጋምቤላ ነጻ አውጪ ግንባር በደምቢዶሎ ከተማ የጋራ ኦፕሬሽን እያካሄዱ መሆኑን ገልጸዋል።
ዛሬ ማክሰኞ ማለዳ ታጣቂዎች በጋምቤላ ክልል ዋና ከተማ ላይ ጥቃት ከፍተው የከተማዋን የተወሰነ ክፍል ተቆጣጥረው እንደነበረና “የሸኔ እና የጋምቤላ ነፃነት ግንባር” በጋራ ጥቃት ከፍተው እንደነበረና ከረፋድ አራት ሰዓት በኋላ መጠነኛ መረጋጋት እንደተመለሰ ክልሉ ባወጣው መግለጫ አመልክቷል።
በጋምቤላ ከተማ በታጣቂዎች እና በፀጥታ ኃይሎች መካከል ዛሬ ማክሰኞ ከማለዳ ጀምሮ በተካሄደ የተኩስ ልውውጥ በክልሉ የፀጥታ አባላት እና በታጣቂዎቹ ላይ ጉዳት መድረሱን የቢቢሲ ምንጮች አረጋግጠዋል።
በምዕራብና በደቡብ የኦሮሚያ አካባቢዎች እንደሚንቀሳቀስ የሚናገረው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአሸባሪ ቡድንነት የተሰየመ ሲሆን፣ የፌደራል እና የክልሉ መንግሥት ታጣቂ ቡድኑን ለመቆጣጠር በተለያዩ ጊዜያት ዘመቻ ሲያካሂዱ ቆይተዋል።












