ከ30 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን በሳዑዲ እስር ቤቶች በአሰቃቂ ሁኔታ ውስጥ ይገኛሉ - አምነስቲ

ስደተኞች በተጨናነቀ የሳዑዲ እስር ቤት ውስጥ

የፎቶው ባለመብት, HRW

የምስሉ መግለጫ, ስደተኞች በተጨናነቀ የሳዑዲ እስር ቤት ውስጥ

በሳዑዲ አረቢያ ሕጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ የሌላቸው ናቸው የተባሉ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውን ስደተኞች በተጨናነቁ እስር ቤቶች በሰቆቃ ውስጥ እንደሚገኙ አምነስቲ ኢንተርናሽናል አስታወቀ።

ዓለም አቀፉ ሰብአዊ መብት ተሟጋች አምነስቲ ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በሳዑዲ አረቢያ እስር ቤቶች ውስጥ ያሉበትን ሁኔታ እና እየገጠማቸው ያለውን አሳሳቢ ሁኔታን በተመለከተ ባወጣው መግለጫ ቁጥራቸው ከ30 ሺህ እንደሚልቅ አመልክቷል።

ጨምሮም የሳዑዲ ባለሥልጣናት “በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንን ኢሰብአዊ እና ጭካኔ በተሞላበት አያያዝ ላልተገደበ ጊዜ በእስር ከቆዩ በኋላ በግድ ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ይደረጋል” ብሏል።

ኢትዮጵያውያኑ ለዚህ ስቃይ የሚዳረጉት ሕጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ ስለሌላቸው ሲሆን፣ ይህም ሁኔታ ሳዑዲ ባላትና “ጨቋኝ” ነው በሚባለው ‘ካፋላ’ የሠራተኞች ቅጥር ሥርዓት ምክንያት የተባባሰ መሆኑን አመልክቷል።

አምነስቲ ኢንትርናሽናል የኢትዮጵያውያኑን ሁኔታ ይፋ ባደረገበት ሪፖርቱ ላይ እንዳለው፣ ወንዶች፣ ሴቶች እና ልጆች የሚገኙባቸው ስደተኞቹ በዘፈቀደ ተይዘው በእጅጉ የተጨናነቁ ናቸው ባላቸው አል-ኻራጅ እና አል-ሹማይሲ በተባሉ እስር ቤቶች ይገኛሉ።

የመብት ተቆርቋሪ ድርጅቱ የመካከለኛው ምሥራቅ እና የሰሜን አፍሪካ አካባቢ ኃላፊ የሆኑት ሄባ ሞራዬፍ እንደተናገሩት ባለፉት አምስት ዓመታት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በሳዑዲ አረቢያ በአሰቃቂ ሁኔታ ውስጥ በማለፋቸው “በርካቶች ለከባድ እና ለዘላቂ አካላዊ እና አእምሯዊ ችግሮች ተዳርገዋል።”

“በአሁኑ ወቅትም ከ30,000 በላይ ኢትዮጵያውያን በተመሳሳይ ሁኔታ ተይዘው ተመሳሳይ ዕጣ እየተጋፈጡ ነው። አንድ ሰው ሕጋዊ ሰነድ የለውም ማለት ሰብአዊ መብቱ ይገፈፋል ማለት አይደለም” ብለዋል ሄባ።

በኢትዮጵያውያኑ ስደተኞች ላይ እየተፈጸመ ያለውን ግፍ በተመለከተ አምነስቲ ኢንተርናሽናል፣ የሳዑዲ ባለሥልጣናት ባለፉት ሁለት ዓመታት በእስር ቤቶች በስደተኞቹ ላይ የተፈጸሙ ማሰቃየቶችን እንዲሁም ቢያንስ 10 ሞቶች ላይ ምርመራ እንዲያካሂዱ ጠይቋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ የሳዑዲ ባለሥልጣናት የመኖሪያ ሰነድ ሳይኖራቸው በአገሪቱ ውስጥ ይገኛሉ ያሏቸውን ስደተኛ ሠራተኞችን በአሰሳ በመያዝ ወደ ኢትዮጵያ እንዲመለሱ የማድረግ ዘመቻ ሲያካሂዱ ቆይተዋል።

“ሳዑዲ ባላት ካፋላ በተባለው ጨቋኝ ሥርዓት” ሰነድ የሌላቸው የውጭ አገር ዜጎች የሆኑ ሠራተኞች ሕጋዊ እንዲሆኑ የሚያስችል ዕድል አይሰጥም። በተጨማሪም ሕጋዊ ሰነድ ይዘው ስቃይ ከሚፈጽሙባቸው አሰሪዎች ያመለጡ ሠራተኞች ከሆኑም ሕጋዊነታቸውን ያጣሉ።

በሳዑዲ አረቢያ በአሁኑ ወቅት 10 ሚሊዮን የሚገመቱ ስደተኛ ሠራተኞች የሚገኙ መሆናቸውን ያመለከተው አምነስቲ፣ በተለይ ለስቃይ የተጋለጡ ናቸው ባላቸው ኢትዮጵያውያን ላይ ማተኮሩን ገልጿል።

የኢትዮጵያ እና የሳዑዲ መንግሥታት እየተጠናቀቀ ባለው የአውሮፓውያን ዓመት ቢያንስ 100 ሺህ ኢትዮጵያውያን ወንዶች፣ ሴቶችና ልጆችን ወደ አገራቸው ለመመለስ ዕቅድ መያዛቸውንም መግለጫው አመልክቷል።

በርካታ ኢትዮጵያውያን የተሻለ ሥራ እና ሕይወት ፍለጋ በአደገኛ መንገድ ከሚሰደዱባቸው የመካከለኛው ምሥራቅ አገራት መካከል ሳዑዲ አረቢያ አንዷ ስትሆን፣ ስደተኞቹ በመንገዳቸው ላይ ከሚገጥሟቸው አደጋዎች ባሻገር በመድረሻቸውም ከባድ ሰቆቃ ይገጥማቸዋል።

ኢትዮጵያውያኑ በአደጋኛ ባሕር እና በረሃ አቆራርጠው በሕገወጥ መንገድ በሚጓዙበት ጊዜ በሺዎች የሚቆጠሩት ባሕር ውስጥ የመስመጥ፣ በአዘዋዋሪዎች እና ድንበር ጠባቂዎች የመገደልና በረሃብና በውሃ ጥም መንገድ ላይ መሞታቸው ሲዘገብ ቆይቷል።

በሳዑዲ አረቢያ በመቶ ሺዎች ኢትዮጵያውን ስደተኞች የሚገኙ ሲሆን፣ ባለሥልጣናት ሕገ ወጥ ናቸው ባሏቸው ስደተኞች ላይ እርምጃ በሚወስዱበት ኢላማ ከሚሆኑት መካከል አንዱ ናቸው።

በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በአሁኑ ጊዜ በተለያዩ የሳዑዲ እስር ቤቶች ውስጥ በአሰቃቂ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙ ከዚህ ቀደም ቢቢሲ በድምጽና በምስል ያገኛቸው መረጃዎችን መሠረት አድርጎ በተደጋጋሚ መዘገቡ አይዘነጋም።