'ካፋላ': ከባርነት አይተናነስም የሚባልለት የአረብ አገራት ሕግ

በሊባኖስ የተደረገ ሰላማዊ ሰልፍ

የፎቶው ባለመብት, TRT World

የካፋላ ስርአት በተለያዩ የአረብ አገራት ስራ ላይ የሚውል በስደተኛ ሰራተኞች እና በአሰሪዎቻቸው መካከል ያለ ግንኙነትን ሚያስተዳድር ሕግ ነው።

ስደተኛ ስራተኛ የሚለው ቃል በራሱ መብራራት አለበት። የውጪ አገር ሰራተኞች ከስደተኛ ሰራተኞች ይለያሉ።

አንድ ሰራተኛ ከሚኖርበት አገር በሕጋዊ መልኩ ተመልምሎ ወደ ሌላ አገር ለስራ ሄዶ 'ስደተኛ ሰራተኛ' ተብሎ እንዲጠራ የሚያደርጉት መለኪያዎች አሉ።

''ሙያ የሌለው የውጪ አገር ሰራተኛ'' ስደተኛ ሰራተኛ ተብሎ እንዲጠራ ከሚያደርጉት መስፈርቶች መካከል ናቸው።

በተለይም ወቅታዊ ስራን ለማካሄድ የሚጓዙ እና ከጥቂት ግዜ የስራ ቆይታ በኋላ የሚመለሱ ሰራተኞች በዚህ ስም ይጠራሉ፤ ስያሜው የሚያመጣውን ውጤቶችንም ይቀበላሉ።

የካፋላ ስርአት ምንድነው?

ካፋላ በርካታ ትርጉም ያለው ቃል ነው። ነገር ግን በዚህ አውድ የዋስትና ወይም ''የስፖንሰርነት ስርአት'' ተብሎ በግርድፉ ሊተረጎም ይችልላል።

አንድ አሰሪ ከሌላ አገር የሚቀጥረውን የቤት ሰራተኛ በተመለከተ በርካታ መብቶችን ያገኛል።

አንድ ሰራተኛ ከአሰሪዎቹ/ቿ ቤት ወይም ቁጥጥር ስር ከወጣ/ች ወይም ሕገ ወጥ ስደተኛ መሆንን ያስከትላል የካፋላ ሕግ። ይህ በሰላሙም ግዜ ሆነ ጥቃት ደርሶባትም ቢሆን አይቀየርም።

ታዲያ በባሕረ ሰላጤው አገራት ማለትም በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች፣ ኩዌት፣ ባህሬን፣ ኦማን እና ሳዑዲ አረቢያ ይተገበራበል። እንዲሁም ጆርዳን እና ሊባኖስ ይሄንኑ ሕግ ይተገብራሉ።

በዚህ ሕግ አማካኝነት ሰራተኞቹ መደራጀት አይችሉም። ባጠቃላይ ህይወታቸው በአሰሪያቸው እጅ እንዲወድቅ በማድረጉ ለጥቃት እንዲጋለጡ ማድረጉን የሚያሳዩ በርካታ ጥናቶች ተሰርተዋል።

የካፋላ ሕግ ከሚያስተዳድራቸው ሰራተኞች ውስጥ በርካቶቹ የቤት ውስጥ ስራ ብሎም ለግንባታ ሰራተኝነት የሚመረጡ ናቸው። በቀለም ትምህርት ሰልጥነው ወደነዚህ አገራት የሚሄዱ ሰዎች በዚህ ስም አይጠሩም፣ እናም በዚህ 'ጨቋኝ' ሕግ አይተዳደሩም።

ስደተኛ ሰራተኞች ከመደበኛው የአገራቱ የአሰሪ እና ሰራተኛ ሕግ የተገለሉ ናቸው። ይህ በልማድ ሳይሆን በሕግ የተደነገገ ነው።

ሕጉ የሚፈጥረው ውጤት ለምን ከባርነት ጋር ተነጻጸረ?

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ኢትዮጵያዊያንን ጨምሮ ወደ አረብ አገራት ተጉዘው የቤት ውስጥ ስራን የሚያከናውኑ ሰራተኞች በዚሁ ሕግ አማካኝነት ለከፍተኛ የመብት ጥሰቶች እንደሚጋለጡ ይታመናል።

አምነስቲ ኢንተርናሽናል በሊባኖስ የዚህ ሕግ እንዲሻር በተደጋጋሚ ከሚጠይቁ ተቋማት መካከል ነው። አሰሪዎች ያለ ሰራተኛው ፈቃድ ውላቸውን ማቋረጥ የሚያስችለው ይህ ስርአት ሰራተኞችን ለእስር ብሎም ከአገር ለመባረር ያጋለጠ ነው ሲል ተችቶታል።

የካፋላ ስርአትን አስከፊ ከሚያደርጉት መገለጫዎቹ መካከል የቤት ሰራተኞቹ አገሩን ጥለው መውጣት ቢፈልጉ እንኳን ከአሰሪያቸው የተጻፈ ፍቃድ ሊሰጣቸው ይገባል። ያ ካልሆነ በሕግ ይጠየቃሉ።

ይህ የሰራተኞቹን ሕይወት በአሰሪው እጅ የሚጥለው ሕግ በበርካቶች ዘንድ 'ዘመናዊ ባርነት' በሚል የሚገለጽ ሲሆን በርካቶች እንዲቆም ጥሪያቸውን ሲያቀርቡ ቆይተዋል።

በቅርቡ በሊባኖስ ውስጥ ባሉ ስደተኛ የቤት ውስጥ ሰራተኞች ላይ አተኩሮ በተሰራ ጥናት ላይ ከተሳተፉ ሰዎች ውስጥ 69 በመቶው ቢያንስ አንድ ግዜ ጾታዊ ትንኮሳ አጋጥሟቸዋል። ጥቃቱ ከደረሰባቸው ሰዎች ውስጥ 75 በመቶው ሕጋዊ ሰነድ እንዳልነበራቸው ተናግረዋል።

ጥናቱን ያካሄደው የእኛ ለእኛ በስደት የተሰኘው በሊባኖስ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ስደተኛ የቤት ውስጥ ሰራተኞች ማሕበር ከአሰሪዎቻቸው ቤት በተለያየ መንገድ የወጡ ሰዎች ወደ አገራቸው እንዲገቡ ያመቻቻል። የማሕበሩ መስራች ባንቺ ይመር እንደምትለው ሰራተኞቹ የካፋላ ስርአቱ የሚሰጣቸውን መብት እንኳን አሰሪዎቹ እንደማይሰጡ ትናገራለች።

ጥቃት የደረሰባት ሴት ውሏን የማቐረጥ መብት የካፋላ ስርአቱ ቢሰጥም አሰሪዎቹ ‘ሰርቃኛለች፤ ልጄን ደብድባለች የሚል የሃሰት ክስ ለፖሊስ እንደሚናገሩ ታስረዳለች። ወደ አገር ቤት ለመመለስ መታሰር ይኖርባቸዋል፤ እንደባንቺ ገለጻ። ከ10 አመት በላይ በእስር ቤት የሚገኙ ሰዎች እንደሚገኙም ታስረዳለች።

በካፋላ ስርአት አሰሪዎች የሰራተኞቸቻቸውን ፓስፖርት ወስደው ማስቀመጣቸው የተለመደ ነው። ሰራተኞቹ መንቀሳቀስ ሳይችሉ ይቀራሉ። ሌሎቹ ቪዛቸውን እንዲሁም ውላቸውን ሳያድሱላቸው ይቀራሉ። አንድ ሰራተኛ ከአሰሪዎቿ ቤት ጥላ ከወጣች እና እነርሱም ለመልቀቅ ፈቃደኛ ካልሆኑ ‘ሕገ ወጥ’ ትባላለች፤ ይህም ለእስር ይዳርጋል።

እናም አብዛኞቹ የቤት ውስጥ ጥቃት የደረሰባቸው ሰራተኞች ሕጋዊ ሰነድ ያልነበራቸው ናቸው ማለት ከቁጥጥራቸው ውጪ በሆነ ሁኔታ ውስጥ እንዳሉ መዘንጋት አይገባም።

በሊባኖስ ውስጥ በተሰራው ጥናት ላይ የተሳተፈች አንዲት ግለሰብ የአንድ ታዋቂ የታክሲ ኩባንያ በሚያቀርበው ትራንስፖርት ላይ ተሳፍራ በነበረችበት ወቅት ያጋጠማትን ትናግራለች።

ግለሰቡ ሊወስዳት ከሚገባው መንገድ መውጣቱን ተመልክታ ‘ለምን’ ብትልም ‘ስለምታምሪ እና ደስ ስላልሽኝ ልነካሽ እፈልጋለሁ’ እንዳላት ትናገራለች። መኪናውን እንዲያቆም ብትጠይቀውም ‘አሻፈረኝ’ አለ። በመጨረሻም ከኋላ በር ዘላ እንደምትወጣ በማስፈራራቷ አውርዷት መሄዱን ታስረዳለች።

በርካቶች ከቤት እስከ ገበያ ማዕከላት ጥቃቱ ይከተላቸዋል። ሌሎች በመንገድ ላይ እየተራመዱ ትንኮሳው ይከተላቸዋል።

በርካቶች ወደ ሕግ አይሄዱም። ጥናቱ እንደሚያመላክተው ወንድ አሰሪዎች ዋነኛ አጥቂዎች ናቸው። የአሰሪዎች ዘመዶች በጥቃቱ ይሳተፋሉ፤ እንደጥናቱ። ከአሰሪዎቻቸው ጥቃት አምልጠው ለመሄድ ፓስፖርታቸውን ጨምሮ ሕጋዊ ሰነዳቸው ብዙ ግዜ በአሰሪዎች እጅ ይቀመጣል።

በርግጥ በእጃቸው ላይ ቢሆንም አሰሪዎች ሰራተኛዋ/ው መጥፋቱን ካወቁ ወደ ሕግ ሄደው ውላቸውን ማቋረጣቸውን ያሳውቃሉ።

በዚህ ቅጽበት ተጠቂዋ ሕገ ወጥ ስደተኛ ተብላ በሕግ ትፈለጋለች፤ ለእስር ትዳረጋለች።

ታዲያ ከአሰሪያቸው ቤት ጥለው መጥፋት ለሌሎች ተጨማሪ ጥቃቶች እንደሚዳርግ የሚረዱት ሰራተኞች በዝምታ ይቀመጣሉ። ለተደጋጋሚ ጥቃት እና ጉልበት ብዝበዛ ይዳረጋሉ።

የሚያለቅሱ የቤት ሰራተኞች

የፎቶው ባለመብት, TRT World

ታሪካዊ ዳራው

የካፋላ ስርአት የገልፍ አገራትን በቅኝ ግዛት ይዛ የቆየችው ብሪታኒያ በ20ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ላይ እንደ አዲስ ያስተዋወቀችው ሕግ እንደሆነ ጥናቶች ያመለካታሉ።

ይህም በባሕረ ሰላጤው አገራት የነዳጅ ዘይት መገኘቱን ተከትሎ ይሄንኑ ሕግ በነዳጅ ተቋማት ውስጥ ሊሰሩ ወደ አገራቱ በሚመጡ የሌሎች አገራት ሰራተኞች ላይም እንዲተገበር ማድረጋቸውንም ያክላሉ።

በ 1950ዎቹ በተለይም ከአፍሪካ እና ከእስያ በስደት የሚሄዱ ሰራተኞችን እና አሰሪዎቻቸውን ለማስተዳደር በሚል በሰፊው ጥቅም ላይ መዋል ጀመረ።

ነገር ግን በእስልምና ሕግ ውስጥ በተለያዩ ሁኔታዎች ሌሎች የካፋላ ስርአቶች ነበሩ። ለምሳሌ አንድ ወላጆቹን ያጣ ልጅን ለማሳደግ የሚወስዱ ሰዎች በካፋላ አማካኝነት መብቶችን ያገኛሉ።

ታዲያ እንደ ሌሎች የቅኝ ግዛት ውርሶች ታዲያ የአረብ አገራት ነጻነታቸውን ካገኙ ከ 50 ዓመታት በኋላም የካፋላ ስርአት በአገራቱ ይተገበራል።

ይህንን ሕግ ኳታር እ.ኤ.አ. በ2019 ሽራዋለች። ኳታር ይህንን ሕግ ለማሻሻል ያስገዳደት መጪውን የአለም ዋንጫ ለማዘጋጀት ስታዲየሞችን ለመገንባት የቀጠረቻቸው የጉልበት ሰራተኞች ላይ ይህ የካፋላ ሕግ መተግበሩን ተክተሎ ተቃውሞዎች በበረቱባት ወቅት ነበር።

በአብዛኛው ከ ደቡብ እስያ አገራት የሚመጡት እነዚህ የጉልበት ሰራተኞች በአስከፊ የኑሮ ሁኔታ ውስጥ መቆየታቸውንም በመግለጽ በርካቶች ይህንን ጨቋኝ ሕግ ሲቃወሙት ቆይተዋል።

ምን ይደረግ?

በአረብ ባሕረ ሰላጤ አገራት ብቻ ባጠቃላይ 30 ሚሊዮን የሚሆኑ ስደተኛ ሰራተኞች ይገኛሉ። በየአመቱ በሺዎች የሚቆጠሩት ሕይወታቸው ግልጽ ባልሆነ መልኩ እንደሚያልፍ ብሎም መንግስታቱ ያንን ተከታትለው ባግባቡ እንደማይመረምሩ የመብት ተሟጋች ተቋማት ያብራራሉ።

አለማቀፉ የስራ ድርጅት አይኤልኦ እንዲሁም በርካታ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች የስደተኛ ሰራተኞችን ሰብአዊ መብቶችን የሚያከብር ሕግ እንዲወጣ የተለያዩ ጥረቶችን ያደርጋሉ።

ታዲያ እነዚህ ተቋማት በጋራ ለዚህ ሰብአዊ ቀውስ ያላቸው ብቸኛው ምላሽ ይህንን ስርአት ይወገድ የሚል ብቻ ነው። ከአለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች መርሆዎችን የጣሰ እንደሆነ የሚነገርለትን ይህንን ሕግ ማስወገድ ብቻ ሳይሆንም በቀጣይነት የሕግ ክፍተቶቹ በማሻሻያዎች እንዲሞሉ ብሎም አስፈጻሚ አካላት ያንን እንዲያስፈጽሙም ይመክራሉ።

ባንቺ እንደምትለው ይህንን ከባርነት የማይተናነስ ስርአት ለማስወገድ ቀላል አይደለም። ነገር ግን የአለም አቀፉ ሕብረተሰብ በጋራ ካልሰራ በአገራቱ ያሉ ተሟጋቾች ብቻቸውን ለውጥ ማምጣት አይችሉም። ከዚህ ጭቆና የሚጠቀሙ ሰዎች ክንድ መፈርጠሙ አንደኛው ምክኒያት ነው።

ባንቺ ለአብነት ሊባኖስን በማንሳት አሁን ካለችበት የኢኮኖሚ ቀውስ የተነሳ ሊባኖስ በአለምአቀፉ ህብረተሰብ ድጋፍ ስር እንደምትገኝ ታስታውሳለች። ታዲያ አለማቀፉ ሕብረተሰብ እንዲህ ያለ አስቸጋሪ የሰብአዊ መብት ሁኔታ መኖሩን አገሪቷ እንድታታሻሽል ጫና ማድረግ ይገባዋል ትላለች።

''እስካሁን ድረስ ለተደበደቡ፣ ለተገደሉ ብሎም ለተደፈሩ ሴቶች ፍትህ ተሰጥቶ አያውቅም። ይህንን ሕግ ተገን አድርገው ነው በደል እየፈጸሙ ያሉት'' ስትል ባንቺ ትናገራለች።