በኮቪድ-19 ምክንያት በአሜሪካ በኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን ላይ የተባባሰው ጾታዊ ጥቃት

የፎቶው ባለመብት, Dunia Mekonnen
ዱንያ መኮንን ኑሮዋን በአሜሪካ ያደረገች የሕግ ባለሙያ ናት። በሕግ የመጀመሪያ ዲግሪዋን ያገኘችው ኢትዮጵያ ሲሆን በተባበሩት መንግሥታትና መንግሥታዊ ባልሆኑም ድርጅቶች ውስጥ በሰብዓዊ መብት ባለሙያነቷ አገልግላለች። በሥራ ዓለም ከተሠማራችበት ጊዜ አንስቶ ትኩረቷን በሴቶችና በሕፃናት መብት ጥሰት ዙሪያ ላይ በማድረግ ሠርታለች።
በሴቶች ላይ በሚደረጉ የመብት ጥሰቶች ላይ በኢትዮጵያም ትሠራ እንደነበር የምትናገረው ዱንያ፣ የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማህበር ውስጥ የነፃ ሕግ አገልግሎት ትሰጥ ነበር።
በወቅቱ በአገሪቱ ለሴቶች መብት ጥሰት እምብዛም ትኩረት ስላልነበረና ጥቃቶቹም በብዛትና በተደጋጋሚ ያጋጥሙ ስለነበር በይመለከተኛል ስሜትና የሕግን ሚና በማስተዋል ሥራውን ለመቀላቀል መገፋፋቷን ታስረዳለች።
ዱንያ በተባበሩት መንግሥታት የሴቶች ክፍል ውስጥ በሴቶች ጥቃት ላይ አተኩራ ትሠራ በነበረበት ወቅት በደረሰችባቸው ግኝቶች ምክንያት ሥራው በይበልጥ ትኩረት እንደሚያስፈልገው ተረዳች።
ከዚያም በዚሁ ዘርፍ ነፃ የትምህርት ዕድል አግኝታ በአፍሪካውያን ሴቶች መብት አድቮከሲ ሁለተኛ ዲግሪዋን ከአሜሪካ ጆርጅታውን ዩኒቨርሲቲ በብሔራዊ ደህንነት የተመረቀች ሲሆን፣ አሁንም እዚያው በአሜሪካ በሴቶች መብት ላይ ተቀጥራ እየሠራች ሲሆን የነጻ አገልግሎትም ትሰጣለች።
በአሁን ሰዓት በአሜሪካ ካሉ ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን ሕብረተሰብ ጋር በይበልጥ እየሠራች ያለችው ዱንያ " ያለው ሁኔታ ልክ አገር ቤት እንዳለው ነው። እንደውም፣ እዚህ ያለው የባሰ ነው። የተማረው የሕብረተሰብ ክፍል ከአገር ቤት አንፃር ቢበዛም እንኳን በሴቶች ላይ የሚደርሰው ጥቃት ግን ይበልጥ የከፋ ነው" ትላለች።
በተለይ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ከመጣ አንስቶ ብዙ ጥንዶች ከቤታቸው ሳይወጡ በመቆየታቸው የተነሳ ጥቃቶቹ መባባሳቸውን ትገልፃለች። ከወረርሽኙ በፊት የነበረው የጥቃት መጠን በማህበረሰቡ ውስጥ በጣም ከፍተኛ የነበረ ሲሆን ጭራሽ ወረርሽኙን ተከትሎ ከተደነገገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በኋላ ደግሞ አብሮ ጭንቀት ይዞ በመምጣቱ ብዙ ፆታዊ ጥቃት የደረሰባቸው ሰዎች መኖራቸውን ትጠቁማለች።
"በእንደዚህ ዓይነት ጊዜ በተለይ በትንሽ በትልቁ ሰዎች እየተጋጩ ነው። ምክንያቱም የአብዛኛዎቹ ኑሮ ከእጅ ወደ አፍ በመሆኑ ውጥረትና ጭንቀት ላይ ናቸው። በአሁን ሰዓት አብዛኛው ሕብረተሰባችን ኪራይ መክፈል አቅቶት ነው የሚገኘው። በዚያም ምክንያት ብዙ ጉዳዮች እስከ ፍቺ ደርሰው ወደ ሕግ ቢሮ እየመጡ ይገኛሉ" በማለት ከወረርሽኙ ወዲህ በአሜሪካ ያለውን ሁኔታ ታስረዳለች።
ዱንያ የመሥሪያ ቤታቸውን ደጃፍ የሚጠኑት ጥንዶች ቁጥር ቢበዛም፣ "ቢያንስ እርዳታ የትና እንዴት ማግኘት እንደሚችሉ የሚያውቁት ናቸው ወደኛ የሚመጡት። የሚያሳስበው፣መረጃ የማይደርሳቸው የሕብረተሰባችን ክፍሎች ብዙ መሆናቸው ነው" ትላለች።

የፎቶው ባለመብት, Dunia Mekonnen
በአሁን ሰዓት ዋናው የሥራቸው ትኩረት ዱንያ ከፍ ብሎ የጠቀሰቻቸው የሕብረተሰብ ክፍሎች በመሆናቸው ርዳታው እንዴት እንዲደርሳቸው ማድረግ እንደሚቻል እርሷ እና የሥራ ባልደረቦቿ ጠንቅቀው ማጤን እንደነበረባቸውም ታስረዳለች። " (የአስቸኳይ ጊዜ) አዋጁ ሲወጣ ሁሉም ነገር የተዘጋ የመሰላቸው ሰዎች ነበሩ። አብዛኛው መረጃ በእንግሊዝኛ ወይንም ገፋ ቢል በስፓኒሽ ነው የሚሰጠው። ይህም ደግሞ ከተለያዩ የአገራችን ከተሞች የመጡትን ያካተተ አይሆንም። ስለዚህ እነርሱ በሚረዷቸው ቋንቋዎች መድረሳችን ሙያዊ ግዴታችን ነበር" ትላለች።
ዱንያና ባልደረቦቿ ችግሩን ከተገነዘቡ በኋላ የማህበራዊ ድረ ገፆችን በመጠቀም የውይይትና የመረጃ መስጫ መስመር ከፈቱ። ይህም የተጠቁስት ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን አስፈላጊው መረጃ እንዲደርሳቸው በማሰብ መሆኑንም ጠቅሳለች።
"ሰው እንዲያውቅና እንዲረዳ የምንፈልገው ነገር በአሁን ሰዓት የሕግ አገልግሎት ለሚፈልግ ማንኛውም ግለሰብ የሕግ ባለሙያዎችም ሆንን አግልግሎቱ ክፍት መሆናቸውን ነው። የጥበቃ ጥያቄ፣ ፍቺም ሆነ ማንኛውንም ርዳታ ማግኘት ለሚፈልጉ ወንድም እህቶቻችን በተቻለን መጠን በቋንቋቸው አገልግሎት ለመስጠት ቆርጠን ተነሳን" በማለት በተለያዩ የአሜሪካ ግዛቶች ታፔላ፣ ፓምፍሌቶችና በራሪ ወረቀቶችን በተለያዩ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች መዘጋጀታቸውንም ጭምር ትናገራለች።
በመቀጠልም "ከሁሉም በላይ ለግሪን ካርድ ባሎቻቸው ወይም ሚስቶቻቸው አመልክተውላቸው በመጠበቅ ላይ ያሉት በይበልጥ ለጥቃት ተጋላጭ ሆነው ይገኛሉ። አሜሪካ የሚገኙበት ሁኔታው እርግጠኛ ባለመሆኑ ምክንያት ጥቃቱን በፀጥታ እየተቀበሉ እየተጎዱ የሚኖሩት ብዙ ናቸው" እያለች መኖሪያ ፈቃድ ለሌላቸው እንኳን ሕጉ እንደሚያገለግላቸው ማሳወቅ ግዴታ ነው ትላለች።
"ጥቃት እየደረሰባቸው ያሉት ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን ወደ ሕግ ቢጮኹ በሂደት ላይ ያለው የመኖሪያ ፈቃድ ሰነዳቸው ላይ ምንም ዓይነት እንቅፋት እንዳማይገጥማቸው እንዲያውቁ እንፈልጋለን። ምክንያቱም በ'ቫዮለንስ አጌንስት ዊሜን አክት' ሕግ መሠረት አስፈላጊው 'ፕሮቴክቲቭ ኦርደር' ተወስኖላቸው ተገቢው ጥበቃ ይደረግላቸዋል።"
ዱንያ ሥራው ይጀመር እንጂ ገና ብዙ እንደሚቀራቸው በማስረዳት ኮቪድ-19 በሴቶች ላይ እየደረሰ ያለውን ጥቃት ጭራሽ አባብሶታል ትላለች። መሄጃ የሌላቸው ስለሚምስላቸው በሞት አፋፍ ላይ እያሉም ርዳታ ፍለጋ ወደ ሕግም ሆነ ወደ ዘመድ ጓደኛ ለመምጣት መቸገራቸውን ታስረዳለች።
"ሌላ ጊዜ የሴቶች ጥቃት ቁጥር እጅግ ከፍተኛ ነበር። ቢያንስ ለቡናም ሆነ በምክንያት ከሰዎች ጋር በሚገናኙበት ጊዜ ችግራቸውን የሚያጋሩት ሰው አያጡም ነበር። አሁን ከማንም ጋር እንዳይገናኙ ስለተደረጉ፣ ችግር ላይ መሆናቸውን ራሱ ለማወቅ ተቸግረናል" የምትለው ዱንያ እስካሁን ያለው የጥቃት ቁጥር ባይታወቅም እንኳን እየተባባሰ መሆኑ የማይካድ ነው ትላለች።
"ባለው ፆታዊ ጥቃት ላይ የኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እክሎች ሲደረቡበት ከዚህ ቀደም ተመዝግቦ ከምናውቀውና ከነበሩት የጥቃት ቁጥሮች ወረርሽኙ ሲያበቃ እጥፍ ወይም ከዚያም በላይ ይሆናሉ ብለን እንገምታለን" በማለት ያንን ቀደም ብሎ ለመግታት በማሰብ ከወዲሁ የሚያስፈልገውን መረጃ ለማህበረሰቡ ማደርስን ቅድሚያ መስጠታቸውን ታስረዳለች።
"ማንም ሰው ጥቃትን የኑሮው አካል ሊያደርገው አይገባም። ማንም ሰው ሌላን ሰው ማጥቃት መብት የለውም። አንድ ሰው ጥቃት ከደረሰበት ወንጀል ተፈፅሞብኛል ብሎ ማሰብ አለበት። በዘልማድ ቻይው የሚባለው ነገር አይሠራም ምክንያቱም የሕይወት ህልፈት ሊከሰት ይችላል" በማለት ማንም ሰው የወንጀል ተባባሪ መሆን የለበትም በማለት ምክር ትሰጣለች።

















