በአዲስ አበባ ታስረው የነበሩ አብዛኞቹ ተማሪዎች መለቀቃቸውን ፖሊስ አስታወቀ

የአዲስ አበባ ከተማ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ባለፉት ሳምንታት በአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ከኦሮሚያ ክልል ሰንደቅ አላማ እና መዝሙር ጋር በተያያዘ በተከሰተው ሁከት በቁጥጥር ስር ውለው የነበሩ አብዛኞቹ ተማሪዎች መለቀቃቸውን ፖሊስ አስታወቀ።

በተለያዩ የአዲስ አበባ መንግሥት ትምህርት ቤቶች በተቀሰቀሰው ረብሻ ጋር ምክንያት በርካታ ተማሪዎች በቁጥጥር ስር ውለው የነበረ መሆኑ የተዘገበ ሲሆን፣ አብዛኞቹም “አስፈላጊው ምክር ተሰጥቷቸው ተለቀቅዋል” ብሏል የአዲስ አበባ ፖሊስ ረቡዕ ታኅሣሥ 12/2015 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ።

ተማሪዎቹን “በስሜት በመነዳት እና ባለማወቅ የፀረ ሰላም ኃይሎች መጠቀሚያ” ሆነዋልም ብሏል - ፖሊስ።

አብዛኞቹ ተማሪዎች በምክር ተለቅቅው የመማር ማስተማሩ ሂደት ሰላማዊ በሆነ ሁኔታ መቀጠሉን የገለጸው የአዲስ አበባ ፖሊስ “የታሰሩ ተማሪዎች አልተለቀቁም የሚሉ የተዛቡ መረጃዎች እየተሰራጩ ነው” ብሏል።

ይህንንም መረጃ እያሰራጩ ያሉት “ግጭትን የፖለቲካ ትርፍ ማሳኪያ መንገድ በማድረግ የሕብረተሰቡን አብሮነት የሚሸረሽሩ ተግባራት ላይ የተሰማሩ ፀረ-ሰላም ኃይሎች ናቸው” በማለት ጠቅሷቸዋል።

መግለጫው ምን ያህል ተማሪዎች ታስረው እንደነበር እንዲሁም ተለቀቁ የተባሉ ተማሪዎች ቁጥርን በተመለከተ ያለው ነገር የለም።

በአዲስ አበባ በሚገኙ አንዳንድ የመንግሥት ትምህርት ቤቶች የኦሮሚያ ክልል ሰንደቅ አላማ መውለብለብና መዝሙር ይዘመር እንዲሁም ከመዝሙሩ ይዘት ጋር በተነሳው ውዝግብ ከተማሪዎች በተጨማሪ የባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ አባላት እና መምህራን በቁጥጥር ስር መዋላቸው ይታወሳል።

ከእነዚህ ውዝግቦች ጋር በተያያዘ “ድብቅ አጀንዳቸውን ለማራመድ ሲንቀሳቀሱ” ያላቸውን አካላት ላይ በሕግ አግባብ እርምጃ እየተወሰደ እንደሆነም የአዲስ አበባ ፖሊስ ገልጿል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በትምህርት ቤቶቹ ተከስቶ የነበረውም የፀጥታ ችግር መምህራን፣ ወላጆች እና የትምህርት ቤት አመራሮችን በማወያየት ችግሩን መቅረፍ እንደተቻለም የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታውቋል። ለችግሩ የተሰጠውን መፍትሄ በተመለከተ ግን መግለጫው ያለው ነገር የለም።

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስር በሚገኙ የተለያዩ የመንግሥት ትምህርት ቤቶች ውስጥ በተደጋጋሚ ከኦሮሚያ ክልል ባንዲራ እና መዝሙር ጋር ተያይዞ ሁከቶች ተነስተው የተለያዩ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች መፈጸማቸውን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ ታኅሣሥ 04/2015 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ ማስታወቁ ይታወሳል።

በዚህም በትምህርት ቤቶች ሰላም ማጣት፣ የአካል ጉዳትና ንብረት ውድመት እንዲሁም ሌሎችም ጉዳቶች ደርሷል ብሏል ኢሰመጉ።

“በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስር በሚገኙ የመንግሥት ትምህርት ቤቶች ውስጥ ለሚነሱ ሁከቶች መንግሥት በቂ ትኩረት በመስጠት ጉዳዩ ከቁጥጥር ውጪ ከመውጣቱ በፊት አስቸኳይ ዘላቂ መፍትሔ ይስጥ” ሲልም አሳስቧል።

መንግሥታዊው የሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም በበኩሉ የትምህርት ተቋማት ከማንኛውም ዓይነት የሃይማኖት፣ የፖለቲካ አመለካከት እና ባህላዊ ተፅእኖዎች ነጻ እንደሆኑ በሕግ ተደንግጓል ብሏል።

በዚህም ሁኔታ “የአማራን፣ የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችን፣ የሲዳማን ወይም የሌላ ክልልን ባንዲራ በትምህርት ቤት ማውለብለብ እና ክልላዊ መዝሙር እንዲዘመር ማስገደድ የሕግም ሆነ የሞራል መሠረት አለው ብሎ ተቋማችን አያምንም” ብሏል።

አክሎም “የሌላ ክልል ሰንደቅ አላማ በአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ግቢ ይሰቀል የሚባልበት በቂ ምክንያት የሚኖር ከሆነም የአዲስ አበባ ነዋሪዎችን ፍቃድና ይሁንታ ማግኘት ይገባዋል” በማለት በመግለጫው አስፍሯል።

ይህንን ክስተት በተመለከተ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) እና የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) መግለጫ ያወጡ ሲሆን በአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች የኦሮሚያ ክልል ሰንደቅ አላማ መውለብለቡን እና መዝሙር መዘመሩን ተቃውመዋል።